1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቀሌው የእግር ኳስ ግጭት

ሰኞ፣ ግንቦት 7 2009

ቅዳሜ ዕለት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም በመቀሌ ከነማ እና በባህርዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድን የተካሄደው የብሔራዊ ሊግ መደበኛ ግጥሚያ በተፈጠረ ግጭት ተቋርጧል። ጨዋታው ዛሬ ጠዋት በድጋሚ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይካሄድ ቀርቷል።

https://p.dw.com/p/2d0Od
Äthiopien Stadt Mekelle
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

Fussball fans Streit in Mekelle follow up - MP3-Stereo

ከትናንት በስትያ በመቀሌ  ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም ግጭት የተቀሰቀሰው ግጥሚያው በመካሄድ ላይ እያለ እንደነበር የአይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። የአይን እማኞቹ ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ የገባው ፖሊስ አስለቃሽ ጪስ መተኮሱን እና ተመልካቾችም መደብደባቸውን ገልጸውልናል። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የቆሰሉ ሰዎችን የሚያሳዩ ምስሎች ይታያሉ። 
 ቅዳሜ ዕለት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም ሥለተፈጠረዉ ግጭት የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ እንዲሰጠን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር መንግሥት አረጋዊን በሥልክ ለማነጋገር ሞክረን  ነበር። ኮማንደር አረጋዊ ግን ዶይቸ ቬለ «በሠላም ጊዜ አልመጣም» በማለት ሥለግጭቱ መናገር አልፈለጉም። 
የግጭቱን መንስኤ ለማወቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናትንም ለማነጋገር ሞክረናል። ይሁንና ፌዴሬሽኑ የቅዳሜውን ግጥሚያ አስመልክቶ ዝርዝር ዘገባ እየጠበቀ እንደሆነ ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላየው የገለፁልን። እሳቸውም ጨዋታው ዛሬ ጠዋት በድጋሚ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይካሄድ መቅረቱን ገልጸውልናል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ