1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመከካለኛዉ ምሥራቅ እልቂት

ሰኞ፣ ሰኔ 23 2006

የዩናይድት ስቴትስና የብሪታንያ መሪዎች የባግዳድ ገዢዎችን በሐስት ወንጅለዉ ኢራቅ ላይ የለኮሱት እሳት ያቺን ሐገር-ሰወስትም አንድም እንዳትሆን ፖለቲከኞችዋን በሐይማኖት ሐራጥቃ ሰነጣጥቆ ሕዝቧን ያስፈጃል።

https://p.dw.com/p/1CSwg
ምስል Reuters

ኃያሉ-ዓለም «የመጀመሪያዉ» እና «የዓለም» ያለዉ ጦርነት የጫረበትን አንድ-መቶኛ ዓመት ባለፈዉ ቅዳሜ አከበረ።ኢራቅን ይዞ፤ ሶሪያን፤ እስራኤል-ፍልስጤምን ፤ ዩክሬን፤ አፍቃኒስታንን ይዞ፤ ከደቡብ ሱዳን፤ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ከናጄሪያ እስከ ሶማሊያ የሚገኘዉ ዓለም የዚያን ጦርነት ዘግኛኝነት ማሰብ ከቻለ፤ ወይም ማሰብ የሚችሉት ሲያስቡ ካየ በጦርነት እያለቀ፤ ወይም ከእልቂት ለማምለጥ እየተሰደደ ነዉ።የዘግኛኙን ጦርነት መቶኛ ዓመት የዘከረዉ የኃያሉ ዓለም ትኩረትም፤የእልቂት ፍጁቱ ብዛትም ሰሞኑን ኢራቅ ላይ-ጠጠር፤ ሶሪያ ላይ ባስ፤ እስራኤል-ፍልስጤም ደገምገም ብሏል።የእልቂት ፍጅቱን ደረጃ እየጠቃቀስን-እንደገና መካከለኛዉ ምሥራቅ እንበል።

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት-ከመጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ የደረሰበት የኖርማንዲ ዘመቻ-ወይም ዲ-ዴይ ሰባኛ ዓመት-በተከበረ በኻያ-ሁለተኛ ቀኑ የመጀመሪያዉን የዓለም ጦርነትን ያቀጣጠለችዉ ጥይት የተተኮሰችበት መቶኛ ዓመት ተዘክሯል።ጎራ ለይተዉ ሲዋጉ የነበሩት ኃያላን መሪዎች በየጦርነቶቹ መታሰቢያ ሥፍራ የየጦርነቶቹን አስከፊ ዉጤት መዘርዘራቸዉ፤ለየጦርነቱ ተጠያቂ የተባሉ ኃይላትን ዳግም ማዉገዝ-መርገማቸዉ አልቀረም።

እርግጥ ነዉ-ዛሬ አዉሮጳና አሜሪካን የሚያነድ ጦርነት የለም።ካለም-ምሥራቅ አዉሮጳ በጣሙን ምሥራቅ ዩክሬን ላይ የታጠረ ነዉ።አፍሪቃ ግን ኃያሉ ዓለም የመጀመሪያዉ ይበለዉ ሁለተኛዉ በየዘመኑ፤በየጦርነቶቹ እንደነደደች ሁሉ ዛሬ ብዙ ሥፍራዋ-ከጦርነት አልተላቀቀም።እስያ-ካለፍ አገደም ዉጊያ ና ሥጋት አልተለየችም።የመካከለኛዉ ምሥራቅ ከሁሉም የባሰ ነዉ።

የግብፅ-አዉሮጶች-እስራኤል ጦርነት፤የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት፤ የአረብ-ፋርሶች ጦርነት፤የፍልስጤም-እስራኤሎች ጦርነት፤የአሜሪካ-ኢራቆች ጦርነት እየተባለ ለዘመነ-ዘመናት ያን ምድር የሚያነደዉ ጦርነት ዛሬም-አዲስ ሰበብ-ምክንያት ተሰጥቶት፤ ባዲስ ሥም-እንደቀጠለ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ኃላፊ ወይዘሮ ቫለሪ አሞስ ባለፈዉ ሳምንት ለፀጥታዉ ምክር ቤት እንደነገሩት የሶሪያ ሰብአዊ ድቀት በጣም ያሳስባቸዋል።

Bildergalerie Irak Regionalkonflikt ISIS Kämpfer Januar 2014
ምስል picture-alliance/AP Photo

«ሁኔታዉ በጣም ይሻሻላል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር።ይሁንና ሁሉም ተፋላሚ ሐይላት በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፅሙት ጥቃት፤ የሚያደርሱት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጥፋት ምንም ሳይቀንስ መቀጠሉን ለምክር ቤቱ ስናገር እያዘንኩ ነዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ የሶሪያዉ ጦርነት ከተጀመረ ከ2011 ጀምሮ-(ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከአንድ መቶ ሐምሳ ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ተሰዷል።

የሶሪያ ጦርነት ያን ያሕል ሕዝብ-መጨረስ፤ ማሰራብ-ማሰደዱ አሞስ እንዳሉት በርግጥ አሳዛኝ ነዉ።በጦርነቱ ከተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች መሐል-ግን 684ቱ ፍልስጤማዉያን ስደተኞች እንደነበሩ ብዙም የሚናገር የለም። ከተሰደዱት ከ60 ሺሕ የሚበልጡት ፍልስጤማዉያን ስደተኞች ናቸዉ።ከሁለት መቶ ሺሕ የሚበልጡ ፍልስጤማዉያን ዳግም መሰደጃ አጥተዉ፤ ግን ከየመጠለያ ጣቢያቸዉ ተበትነዉ እየተሰቃዩ ነዉ።

አሞስ፤ ድርጅታቸዉ ይሁን የድርጅታቸዉ መስራች፤ መሪዎች ለሶሪያዉያን መሞት መሰደድ የሚጨነቁትን ያክል-እኒያን ከ1948 ጀምሮ-ከስደት፤ ረሀብ፣ እርዛት ልመና ላልወጡት ፍልስጤማዉያን አለመቆርቆራቸዉ ሊያጠያይቅ በተገባ ነበር።

የዓለም የስደተኞች ቀን ባለፈዉ ሳምንት ሲከበር ዓለም አቀፉ ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ታይቶ የማይታወቅ ሕዝብ ተሰድዷል።ከሐምሳ-ሚሊዮን በላይ።ሁለት ሚሊዮኑ ሶሪያዊ፤ ከሰወስት ሚሊዮን የሚበልጠዉ ኢራቃዊ ነዉ።አምስት ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ፍልስጤማዉያን ናቸዉ።

Syrien Allepo Flugzeugangriff Ruinen
ምስል Reuters

ሰኔ 281914 የኦስትሮ-ሐንጋሪዉን አልጋ-ወራሽ ከነባለቤታቸዉ በመግደሉ የመጀመሪያዉን የዓለም ጦርነት የለኮሰዉ ጋቭሪሎ ፕሪንስፕ-ለሟች ወገኖች አሸባሪ ነዉ።ለሰርቦች ግን በስሙ መንገድ-የተሰየሙለት፤ በመልኩ ሐዉልት የቀረፀለት ጀግናቸዉ ነዉ።

ባለንበት ዘመንም ከፍልስጤም-እስከ ኢራቅ-እስከ ሶሪያ ሚሊዮኖችን ለፈጀና ለሚፈጀዉ፤ ብዙ ሚሊዮችን ላሰደደና ለሚያሰድደዉ ጦርነት፤ ግጭት ተፋላሚዎች አንዱ ሌላዉን መወንጀል-ማዉገዛቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።የየተፋላሚዎቹ ደጋፊዎችም የየሚደግፉትን ወገን ርምጃ-ሕጋዊ የየሚቃወሙትን ሐይል አሸባሪ፤ ሰብአዊ መብት ረጋጭ እያሉ ማሳጣት የዘመኑ ፈሊጥ ነዉ።

«ከጋዛ ወደ እስራኤል የተተኮሰዉን ለመበቀል፤ በሳምንቱ ማብቂያ የእስራኤል መከላከያ ሐይል በርካታ ኢላማዎችን ደብድቧል።እርምጃችንን ሁኔታዉ በጠየቀዉ መሠረት እንደየአስፈላጊነቱ እናስፋፋለን።የሐማስ አሸባሪ ቡድን ያለበት የፍልስጤም የአንድነት መስተዳድር ከተመሠረተ ወዲሕ የፍልስጤም ራስ-ገዝ መስተዳድር እስራኤል ላይ የሚቃጡ ተኩሶችን ለመከላከል በገቢር ሐላፊነቱን የወሰደ መሆኑን ለሁሉም ማስታወስ እወዳለሁ። (ማሕሙድ አባስ) ሠላም የሚያራምዱበት አንድ መንገድ ብቻ አላቸዉ።ይሕም ከሐማስ ጋር ያደረጉትን ስምምነት ማፍረስ ብቻ ነዉ»

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።ትናንት።ኔታንያሁ-1996 እስከ 1999 የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።ከ2009 ጀምሮ እስካሁንም የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ናቸዉ።ኔታንያሁ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከያዙበት-2009 ሐማስ የፍልስጤም ራስ-ገዝ መስተዳድር አባል እስከሆነበት እስካለፈዉ ግንቦት ድረስ-አምስት ዓመት ተቆጥሯል።አባስ ሠላም እንዳያራምዱ እንቅፋቱ ከሐማስ ጋር መስማማታቸዉ ከሆነ፤ከሐማስ ጋር ባልተስማሙበት 5 ዓመታት ዉስጥ ኔታንያሁ-ከአባስ ጋር ሠላም ያለወረዱበት ምክንያት ምን-ይሆን?ብቻ-ፍልስጤም እስራኤል-ጥንትም፤ ድሮም እንደዚያ ነበሩ። ቀጠሉም፤ መገዳደል፤መወነጃጀል።ያ ምድር ለፍጅት-ሥደቱ፤ ለመወነጃጀል መጠፋፋቱ ድምቀት የዛሬ አስር-ዓመት ኢራቅ ተጨመረለት።

Syrien Protest in Marea Allepo
ምስል picture-alliance/dpa

የዩናይድት ስቴትስና የብሪታንያ መሪዎች የባግዳድ ገዢዎችን በሐስት ወንጅለዉ ኢራቅ ላይ የለኮሱት እሳት ያቺን ሐገር-ሰወስትም አንድም እንዳትሆን ፖለቲከኞችዋን በሐይማኖት ሐራጥቃ ሰነጣጥቆ ሕዝቧን ያስፈጃል። ያሰድዳልም። የጀርመኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የመካከለኛዉ ምሥራቅ ባለሙያ ጉይዶ ሽታይንበርግ እንደሚሉት አሜሪካኖች የባግዳድ ቤተ-መንግሥትን ያሥረከቧቸዉ የኢራቅ ፖለቲከኞች ከአሜሪካኖች ይልቅ የአምሪካ ጠላቶች ታማኝ መሆናቸዉ ነዉ ጉዱ።-የኢራን።

«ኢራን የኢራቅን ፖለቲካ በዘዴና በግልፅ ለመቆጣጠር እየሞከረች ነዉ።ይሕ የ2003ቱ የአሜሪካኖች ወረራ ካስከተላቸዉ በጣም መጥፎ ነገሮች አንዱ ነዉ።የኢራቅ ማዕከላዊ መንግሥት በጣም በመዳከሙ በጠንካራ ጎረቤቱ ተፅዕኖ ስር በቀላሉ ወድቋል።ተጽዕኖዉ እየጠነከረ ነዉ።ምክንያቱም የኢራን ጥገኛ የሆኑ የሺዓ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢራቅ ዉስጥ በጣም እየተጠናከሩ ናቸዉና።(ጠቅላይ ሚንስር ኑሪ) አል-መሊኪን ለሥልጣን ካበቋቸዉ ሰወስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያንስ ሁለቱ የኢራን ጥገኞች ናቸዉ»

Luftangriffe auf den Gazastreifen
ምስል Reuters

በየዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ሁለንተናዊ ድጋፍ በ1992 ሰሜናዊ ኢራቅ ላይ ነፃ መንግሥት ያክል አስተዳደር ያቆሙት የኢራቅ ኩርዶች የዋሽንግተኖችን ትዕዛዝ እንቢኝ ብለዉ ነፃነታቸዉን ለማወጅ-ቀን እየቆጠሩ፤ ብልሐት እያሰላሰሉ ነዉ።የዋሽግተን-ለንደን መሪዎች ግን ለኢራቅ-ድቀት፤ ለሕዝቧ ሞት-ስደት ድሮ-ሳዳም ሁሴንን፤ በመሐሉ አል-ቃኢዳን ሲያወግዙ እንደኖሩት ሁሉ ዘንድሮም የሚያወግዙ-የሚወነጅሉት አላጡም።የኢራቅና የሻም እስላማዊ መንግሥት-ISIS በምሕፃሩ።ዋሽንግተን-ለንደኖች ኢራቅን ከወረሩበት ይኽ ቡድን ሞሱልን እስከተቆጣጠረበት እስከ ያዝነዉ ወር ድረስ-አስር ዓመት ተቆጥሯል።በዚሕ ሁሉ ዘመን ኢራቅ ላይ ሠላም ያልሰፈነበት-ሰበብ ምክንያት በርግጥ ሊያጠያይቅ-ይገባል።

ሶሪያ ኢራቅን ከተቀየጠች ሰወስተኛ ዓመቷን አጠናቀቀች።ካደባባይ የተቃዉሞ ሠልፍ፤ ወደ እርስ በርሥ-ግጭት፤ ከርስ በርስ ግጭት የዓለም-ሐያል ሐብታሞችን ወዳሠለፈ ጦርነት ባጭር ጊዜ የተሸጋገረዉ ጦርነት መቶ ሺዎችን አርግፏል።ሚሊዮኖችን አሰድዷል።ጦርነቱን ከሪያድ-እስከ ዶሐ የሚገኙ ቱጃሮች፤ ከቴሕራን እስከ ቤይሩት ያሉ አያቱላሆች፤ከዋሽግተን እስከ ብራስልስ፤ከሞስኮ እስከ ቤጂንግ ያሉ ሐያላን እንደሚዘዉሩት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግልፅ ነዉ።ሞሱልን ከተቆጣጠረ ወዲሕ መጥፎ-ሥም ዝናዉ የናኘዉ ISIS በምዕራባዉያንን በአርብ ቱጃሮች ከሚረዱት አማፂያን ጎን ሆኖ የደማስቆ ገዢዎችን እንደሚወጋም የጦርነቱን ሒደት የሚከታተሉ ሁሉ በተደጋጋሚ አስታዉቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን አስከፊዉ ጦርነት በድርድር የሚፈታበትን ብልሐት እንዲፈልጉ በተከታታይ የሾሟቸዉ የዓለም ምርጥ ዲፕሎማቶች ተልዕኳቸዉን በበቃኝ ለማቆማቸዉ የሰጡት ምክንያትም-ጦርነቱን የሚቆሰቁሱት ሐያላን ለድርድሩ ሒደት ባለመተባበራቸዉ መሆኑን በየተራ ግን በግልፅ ተናግረዋል።

ፓን ግን የሶሪያ ተፋላሚዎችን የሚስታጥቁ መንግሥታትን ከእርምጃዉ እንዲታቀቡ ለመማፀን-ሁለት ዲፕሎማቶቻቸዉ እስኪሰናበቱ፤ ጦርነቱ መቶ ሺዎችን እስኪያረግፉ፤ ወይም ISIS ኢራቅ ተሻግሮ ሞሱሉን እስኪቆጣጠር የጠበቁበት ምክንያት በርግጥ ግራ ነዉ።ግን አሉ።

«ሶሪያ ዉስጥ ግፍ ለሚፈፅሙ፤ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መርሆችንና ዓለም ሕግጋትን ለሚጥሱ ወገኖች የዉጪ ሐይላትና ቡድናት ወታደራዊ ድጋፍ መስጠታቸዉ ሐላፊነት የጎደለዉ ነገር ነዉ።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጥል እጠይቃለሁ።በምክር ቤቱ ዉስጥ ያለዉ ክፍፍል እንዲሕ አይነቱን እርምጃ የሚያዉክ ከሆነ ሐገራት በተናጥል እርምጃ እንዲወስዱ አሳስባለሁ»

Gaza-Offensive Israelische Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa

ዋና ፀፊዉ የፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት በጋራ ወይም በተናጥል በሶሪያ ተፋላሚ ሐይላት ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጥሉ ባሳሰቡ በሳምንቱ ዩናትድ ስቴትስ ለሶሪያ አማፂያን የምትሰጠዉ ወታደራዉ ድጋፍ ወደ 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ምክር ቤታቸዉን ጠየቁ።የባግዳድ መንግሥት ከዩናይትድ ስቴትስ የተሰጠዉና የገዛዉ ጦር መሳሪያ አልበቃ ብሎት ከሩሲያ ዘመናይ ተዋጊ ጄቶች መግዛቱን አስታወቀ።የእስራ-ፍልስጤሞች መገአዲስ አይደለም። የተጨማሪ ጦርነት-ድጋፍ፤ የቀጣይ እልቂት ዝግጅት----መካከለኛዉ ምሥራቅ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ