1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ፤ ግብፅና ተጓዳኞቿ

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2007

ቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ከተወገዱ ከ አራት ዓመት ወዲህ ግብፅ እንደገና በውጭ አመራር ረገድ ስሟ ይጠራ ጀምሯል። አሁን በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በተለይም በየመን ብርቱ ውዝግብ ካጋጠመ ወዲህ፤ ግብፅ በዐረቡ ዓለም ፤ ፀጥታ የማስከበር ግንባር ቀደም ኀላፊነት ያለባት ሀገር ሆና በምዕራቡ ዓለም ዘንድ መታየት ጀምራለች።

https://p.dw.com/p/1F2AA
zur Meldung - Arabische Liga beschließt Gründung gemeinsamer Eingreiftruppe
ምስል Reuters/Egyptian Presidency

በቅርቡ፣ መጋቢት 22 ,2007 የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ እንዳስታወቁት የጦር መሣሪያው ማዕቀብ ተነስቶ ግብፅ 1,3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎች ፣ F-16 በሚል መለያ የታወቁ የጦር አይሮፕላኖች ፣ «ሃርፑን» ሮኬቶችና ታንኮች ይቀርቡላታል። ስለሆነም በመካከለኛው ምሥራቅ ፤ የዐረቡ ዓለም ፣ እንደገና ፣ ከስዑዲ ዐረቢያ ጎን ግብፅ ዋናይቱ የዩናይትድ ስቴትስ ተጓዳኝ ትሆናለች።
እ ጎ አ በሐምሌ ወር መግቢያ ላይ 2013 ዓ ም፣ የያኔው ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ከሥልጣን ሲወገዱ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከግብፅ ጦር ኃይሎች ጋር የነበራትን ትሥሥር ፤ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን በጉልበት ማስወገድ የዴሞክራሲን ወግ የሚጻረር ተግባር ፈጽመዋል በማለት ያኔ ርዳታ እንዲቋረጥ ማድረጓ ይታወሳል። ዖባማ፤ እ ጎ አ በ 2009 ካይሮ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ስለዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ደርዝ ያለው ዲስኩር አሰምተው ስለነበረም ነው ከግብፅ ጦር ኃይሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ቀዝቀዝ እንዲል ያበቁት። ፕሬዚዳንት ኧል ሲሲ፣ በተቃዋሚዎችና ሐያስያን ላይ ጥብቅ ርምጃ በመውሰዳቸው፤ ከ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (AI) እና ከድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF) በኩል ከባድ ነቀፌታ ነበረ የተሠነዘረባቸው።


ከዐረቡ ዓለም የሕዝብ መነሣሣት በኋላ የተከሠተው አለመረጋጋት፤ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎቹም ሃገራት ፣ የአካባቢውን የፖለቲካ ይዞታ በአዲስ መልክ እንዲገመግሙ ሳያስገድዳቸው አልቀረም። ኧል ዐረቢ ኧል ጀዲድ የተሰኘው ጋዜጣ በዓምዱ ላይ ፤
« በቅርቡ የዐረቦች ታሪክ፤ በአጠቃላይ በዐረቡ ዓለምም ሆነ በተጠጠል በተለያዩ የአካባቢው ሀገራት እንዲህ ስፋት ያለው ውዝግብ አጋጥሞ ኣ,ያውቅም ነበር። ይህ በፊናው በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረንን ተሰሚነት ሸርሽሮታል። ከሀገሮቻችን መካከል አንዳንዶቹም፤ መንግሥት የለሽ ወይም ሥርዓት አልበኝነት የነገሠባቸው ሊባሉ የሚችሉ ሆነዋልና! » ሲል አሥፍሯል። ከመካከለኛው ምሥራቅ የዐረብ ሀገራት በውጭ ፖለቲካዋም ቢሆን የተረጋጋ አቋም ያላት ግብፅ ናት ፤ ሊቢያ ቀውስ ውስጥ ናት ፤ ሶሪያ በእርስ በርስ ውጊያ እንደተጠመደች ናት፤ ኢራቅ በሽብር ከመናጥ ያልተገላገለች ሀገር ሆናለች። ስለሆነም ለዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን ለስዑዲ ዐረቢያም ስልታዊ አቋም ያላት ተጓዳኝ ግብፅ ናት። አሁን በየመን ከተፈጠረው ብርቱ ውዝግብ አኳያ፤ የኢራን ተጻራሪ ስዑዲ ዐረቢያ ባፋጣኝ ነው ጠንካራ ተጓዳኝ የምትሻው። የመን ውስጥ ስዑዲ ዐረቢያና ተጓዳኞቿ፣ ግብፅ፤ ዮርዳኖስ፤ ክዌትና ባሕሬይን፣ በሪያድ መሪነት፣ በሁቲ አማጽያን ላይ ወታደራዊ ርምጃ መወሰዳቸውን ኢራን አጥብቃ ከመቃወሟም፤ ለአማጽያኑ የጦር አማካሪዎች እንደምትልክ ነው ያስታወቀች።የቀድሞው የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ካናኒ ሞግሃዳም---
«ስዑዲ ዐረቢያና ተጓዳኞቿ ግብፅ ፤ ዮርዳኖስ፤ ቐጠር፣ ክዌትና ባሕሬይን፣ የጠብ ቻሪነት ርምጃቸውን ከቀጠሉና የየመንን አብዮት ለመቀልበስ እስከተነሣሱ ድረስ ፤ ኢራን፤ በሶሪያና በኢራቅ እንዳደረገችው ሁሉ፤ ወደ የመንም፤ ወታደራዊ አማካሪዎችን ከመላክ አትቦዝንም»
ስዑዲ ዐረቢያ፤ የኧል ሲሲን መንግሥት ከመጀመሪያው አንስቶ የደገፈች ስትሆን ባሁኑ የየመን ውዝግብ የግብፅ ከጎኗ መቆም እርካታን አስገኝቶላታል። ስዑዲ ሌላም ምክንያት አላት።የግብፅ የሕግ ባለሙያ የሆኑት የዐረብ መንግሥታት ማሕበር ዋና ጸሐፊ ናቢል ኧል ዐረቢ እንዲህ ይላሉ።

Stadtansicht Kairo
ምስል El-Shahed/AFP/Getty Images


«በዐረብ ሕዝብ ላይ አሥጊ ሁኔታ በመደቀኑ ባልተለመደ ሁኔታ አሸባሪ ድርጅቶች ብርቱ አደጋ በመደቀናቸው ፣ የመንግሥታቱ ውሳኔ ጠቀሚ ነው።»
የሪያድ አገዛዝ፤ የሙስሊም ወንድማማችነት ማሕበር፣ አደገኛ እስላማዊ የሶሺያል አብዮት በመሆኑ ወደ ዐረብ ደሴት አከል ምድር ከተሸጋገረ አስፈሪ ሁኔታዎች ይከተላሉ ባይ ነው። የኧል ሲሲ መንግሥት ከሙስሊም ወንድማማችነት ማሕበር ጋር ትሥሥር ባለው በፍልስጤማውያኑ ሐማስ ላይ ተጻራሪ አቋም መያዙንም ስዑዲ ዐረቢያ በበጎ ዕይን ሆኗል የምትመለከተው። ሙርሲ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፤ ስዑዲ ዐረቢያና የብህረ ሰላጤው አዋሳኝ ንዑሳን የዐረብ ሀገራት፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ርዳታ ነው ለግብፅ ወታደራዊ መንግሥት የለገሡት። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስዑዲ ዐረቢያ፤ ኩዌትና የተባበሩት የዐረብ አሚሮች መንግሥት፣ ለግብጭ እንደገና 12 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። ሪያድን ባለፈው የካቲት ወር ማለቂያ ላይ የጎበኙት ኧል ሲሲ፣ እስካሁን የቀረበውን ርዳታ በተመለከተ «የግብፅ ሕዝብ ከቶ አይረሳውም » ማለታቸው የሚታወስ ነው። ግብፅ እንደ ባሕረ ሰላጤው አገሮች፤ «ጂሃዲዝም»ን በጥብቅ ትታገላለች። በሲና ልሣነ ምድር፤ ሱኒዎቹ ጂሃዲስቶች፤ በሶሪያና ኢራቅ ለሚንቀሳቀሰው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ለሚለው አክራሪ ታጣቂ ኃይል ታማኝነታቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።የሊቢያ ሥርዓት-አልበኝነት፤ በዚያ የሚገኙ የ IS የሽብር ተግባር ተባባሪዎች፤ 21 ቅብጣውያን ክርስቲያኖችን አንገት በመቅላት መግደላቸው የግብፅን ሕዝብ ክርስትያኑንና ሙስሊሙን ሁሉ ያስቆጣና ያስተባበረ ጉዳይ ያስተባበረ ጉዳይ መሆኑም ነው የሚነገረው። አሁን መካከለኛው ምሥራቅ በገጠመው ዐቢይ ተግዳሮት ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የዐረብ መንግሥታት በመተባበር መፍትኄ ለማግኘት ተነሳስተዋል።አሁንም ነቢል ኧል ዐረቢ--
«እጅግ ዐቢይና አጣዳፊም መልስ የሚያሻው፣ መላው ዓለምም በአክብሮት ሊከታተለው የሚገባ ጉዳይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የዐረብ መንግሥታት በመላ፣ ሥጋቱ ገብቷቸው በጋራ አጸፋ መልስ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።ይህ በራሱ ዐቢይ ቁም ነገር ነው።»

Gipfeltreffen der arabischen Liga in Ägypten
ምስል Getty Images/AFP/M.El-Shahed

ክሪስተን ክኒፕ/ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ