1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመድሃኒት ጥንቃቄና TB

ማክሰኞ፣ መጋቢት 17 2005

በየዓመቱ በTB በሽታ 1,7 ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ያልፋል። በታዳጊ ሀገሮች የሀሰት አለያም ደረጃዉን ያልጠበቀ የTB መድሃኒት ገበያዉን ማጥለቅለቁ በሽታዉ ለሚያስከትለዉ ጉዳት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/184bt
ምስል picture-alliance

በዓለም ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ የTB ህመምተኛ መሆኑን ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም የጤና ድርጅት WHO ያወጣዉ መረጃ ያስረዳል። ከዚህ መካከልም 400 ሺህዎቹ መድሃኒት የተላመደዉ TB ተጠቂዎች ናቸዉ። TB ገዳይ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ከሰዉ ወደሰዉ በአየር አማካኝነት ይተላለፋል። አብዛኛዉን ጊዜ ሳንባን በመጉዳት የሚታወቀዉ ይህ በሽታ አንጎልና ኩላሊትን ጨምሮ ሌሎች የአካል ክፍሎችንም ይጎዳል። በTB በሽታም በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህይወቱን ያጣል። ለበሽታዉ የሚሰጠዉን ህክምና በአግባቡ ባለመከታተልና ተገቢዉን መድሃኒት በሀኪም ትዕዛዝ መሠረት ባለመዉሰድ በሽታዉ ዓይነቱን ቀይሮና አጠናክሮ መድሃኒት ተላምዶ ዛሬ ከፍተኛ እና አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ እየተነገረዉ።

TBC Tuberkulose Impfung Impfstoff Impfstamm BCG
ምስል picture-alliance/dpa

በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተዉ ደረጃዉን ያልጠበቀ ወይም የሀሰት የTB መድሃኒት የአዳጊ ሀገሮችን የTB ታማሚዎች ችግር እያወሳሰበ ነዉ።  በ17 ሀገሮች በ19 ከተሞች ዉስጥ የተካሄደዉ ሙከራና ፍተሻ ያሳያየዉ መድሃኒቶቹ አንድም ተገቢዉ የንጥረ ነገሮች ቅምር ዉጤት አይደሉም፤ አንድም በተገቢዉ ፍጥነት በዉሃ አማካኝነት ዉስጣቸዉ ያለዉ ንጥረነገር አይሰባበርም። ይህ የሀሰት አለያም ደረጃዉን ያልጠበቀ መድሃኒት ተገኘ ከተባለባቸዉ ከተሞች አንዷ አዲስ አበባ ናት፤ ዶክተር አንዳርጋቸዉ ግን ይህ በስህተት የተጠቀሰ ሳይሆን እንዳልቀረ ነዉ የሚናገሩት።

የተሳሳተ መድሃኒት መዉሰድ፤ ወይም የታዘዘ መድሃኒትን በአግባቡ አለመከታተል መድሃኒትን ለሚቋቋመዉ የTB ዓይነት እንደሚያጋልጥ ነዉ የሚገለፀዉ። በዓለም በተለይም በአዳጊ ሀገሮች በመስፋፋት ላይ የሚገኘዉ ይኸዉ መድሃኒት የተላመደ TB ነዉ።

TBC Tuberkulose Frau Patientin Südafrika
ምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images

መድሃኒት የተላመደዉ TB እጅግ የተስፋፋባቸዉ በዓለም 27 ሀገሮች ሲሆኑ አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ዶክተር አንዳርጋቸዉ እንደሚሉት በሽታዉ የሚያስከትለዉን የጤና እክል ለመከላከል ዋነኛ ችግር የሆነዉ መድሃኒቱን ጀምረዉ የሚያቋርጡ ህሙማን መበራከት ነዉ። መድሃኒት የተላመደዉ TBም እንዲሁ በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ ሁኔታዉን ያከብደዋል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በየዓመቱ ወደአንድ መቶ ሃምሳ ሺ ሰዉ በምርመራ የTB ህመምተኛ መሆኑ ይረጋገጣል። ከእነዚህ መካከልም ወደሁለት ተኩል ወይም ሶስት በመቶ ገደማ የሚሆኑት ህክምናቸዉን በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚቋርጡ ባለሙያዉ አመልክተዋል።

መድሃኒት የተላመደዉ TB በአንድ ዓይነት ደረጃ ላይ ብቻ የሚገታ እንዳልሆነ ነዉ ትናንት የዓለም TB ቀን ሲታሰብ ባለሙያዎች ይፋ ያደረጉት። በከፍተኛ ደረጃ የተፈረጀዉ መድሃኒት የተላመደ TB ህመምተኞች የትኛዉም ዓይነት መድሃኒት ቢሰጣቸዉ ዉጤት እንደማያሳይ ነዉ የተገለፀዉ።

እንዲህ ያለዉ TB 82 ሀገሮች ዉስጥ ተገኝቷል። ዓለም ለዚህ ችግር ትኩረት በመስጠት የተሻለ መድሃኒት የሚገኝበትን ምርምር እንዲያበረታታ፤ ፈጣንና ዘመናዊ የምርመራ ስልቶችም እንዲስፋፉ በቂ ገንዘብ መመደብ እንደሚኖርበት ተጠይቋል። በአዉሮጳና በማዕከላዊ እስያ በተካሄደ ምርመራ ከተገኘዉ የTB ህመምተኛ መካከል 30 በመቶዉ ለዚህ መጋለጡ ተረጋግጧል። እሁድ ዕለት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለTB በሽታ ህክምና ትኩረት እንዲሰጥ ሲጠየቅ፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ መስኮት በመክፈት ንፁህ አየር እንዲገኝ በማድረግ የTBን መተላለፍ ለመግታት ምክሩ የሚል መልዕክት አድርሳለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ  መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ