1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት የገጠመዉ ፈተና

ሐሙስ፣ የካቲት 5 2007

ሰሜን አዉሮጳዉቱ ሐገር ፊንላንድ- የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይዛለች።ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ኤርትራ ደግሞ አምናም እንደ ሐቻምናዉ ኡራ ወጥታለች።ከአንድ መቶ ሰማንያ ሐገራት አንድ መቶ ሰማንያኛ።አጠቃላዩ የፕረስ ነፃነት ይዞታ ግን ድርጅቱ እንደሚለዉ በአምስቱም ክፍለ-ዓለማት አምና ክፉኛ እሽቆልቁሏል::

https://p.dw.com/p/1EaGw
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

የፕሬስ ነፃነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሆኑን ዓለም አቀፉ የመገናኛ ዘዴዎችና የጋዜጠኞች መብት ተማጓች ድርጅት አስታወቀ።ዋና መቀመጫዉን ፓሪስ-ፈረንሳይ ያደረገዉ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ዛሬ ይፋ ባደረገዉ ዓመታዊ ዘገባዉ እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ዓመት 2014 የፕረስ ነፃነት በመላዉ ዓለም አሽቆልቁሏል።በድርጅቱ ዘገባ መሠረት የመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ የዩክሬንና የአፍሪቃ ግጭትና ጦርነት መባባስ ወትሮም በየምክንያቱ የሚረገጠዉን የፕሬስ ነፃነት ይበልጥ ለአደጋ አጋልጦታል። በድርጅቱ ጥናታዊ መዘርዝር ከ180 ሃገራት ፊንላንድ የፕሬስ ነፃነትን በማክበር መጀመሪያ ደረጃ ላይ ስትገኝ ኤርትራ የመጨረሻዉን ደረጃ ይዛለች።

2014ቱ የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የደረጃ መዘርዝር በአቀማመጥ ቅደም ተከተል ከ2013ቱ ብዙም ለዉጥ የለዉም።ሰሜን አዉሮጳዉቱ ሐገር ፊንላንድ- የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይዛለች።ምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ኤርትራ ደግሞ አምናም እንደ ሐቻምናዉ ኡራ ወጥታለች።ከአንድ መቶ ሰማንያ ሐገራት አንድ መቶ ሰማንያኛ።

Symbolbild Pressefreiheit
ምስል picture-alliance/dpa

አጠቃላዩ የፕረስ ነፃነት ይዞታ ግን ድርጅቱ እንደሚለዉ በአምስቱም ክፍለ-ዓለማት አምና ክፉኛ እሽቆልቁሏል።ሐቻምና የተሻለ ደረጃ ላይ ከነበሩት ሐገራት በሁለት ሰወስተኛዉ ፕሬስ ይበልጥ ክፍኛ ተደፍልቋል።ምክንያቶቹ ብዙ ናቸዉ።ዋንኞቹ ግን---የድርጅቱ የአፍሪቃ ተጠሪ ክሌ ካን ስሪበሪ፤-

«እርግጥ ነዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ የዩክሬንና የአንዳድ የአፍሪቃ አካባቢዎች ሁከት ለፕሬስ ነፃነት ክፉኛ ማሽቆልቆል አስተዋፅኦ አድርገዋል።ይሁንና በሌሎች አካባቢዎችም መንግሥታት የሚያወጧቸዉ የፀጥታ ሕግጋት፤ መረጃ በማግኘት ነፃነት ላይ የሚያደርሱት ጫና እና በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃትም ባለፈዉ ዓመት ሲበዛ ተጠናክሯል።»

የኤርትራ መንግሥት አስሯቸዉ ከነበሩ ጋዜጠኞች ስድስቱን ባለፈዉ ወር ለቅቋል።ኤርትራ ግን አሁንም የፕሬስ ነፃነትን በማክበር የመጨረሻ ሐገር ሆናለች።ለምን?-ካን ስሪበር መልስ አላቸዉ።«አንደኛ ጥናቱ የ2014 ነዉ።ጋዜጠኞቹ የተለቀቁት ግን ዘንድሮ ነዉ» የሚል፤ ሁለተኛ ይቀጥላሉ፤-

«ስድስቱ ጋዜጠኞች ላለፉት ስድስት ዓመታት ታስረዉ የነበረዉ ያለምንም የፍርድ ቤት ሒደት ነዉ።የተለቀቁትም በተያዙበት መንገድ ነዉ።ለምን እንደተለቀቁ አልተነገራቸዉም።አሁንም ባይነ ቁራኛ እየተጠበቁ ነዉ።ሥለዚሕ የፕሬስ ነፃነት የመከበሩን ምልክት የሚያሳየን ምንም ነገር የለም።ኤርትራ ዉስጥ አሁንም ምንም የግል ፕሬስ የለም።ጋዜጠኞችም፤ሌሎች የሐገሪቱ ዜጎችም በገፍ እየተሰደዱ ነዉ።ሥለዚሕ የጋዜጠኞቹ መለቀቅ ለፕሬስ ነፃነት አወንታዊ ጅምር እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ግን የሚሆነዉን ጊዜ ሰጥተን እንይ።»

ኢትዮጵያ ዉስጥ ወትሮም የሚያጣጥረዉ የፕሬስ ነፃነት በ2014 ብዙዎች እንደሚሉት ጨርሶ ባይገደል እንኳ ሕልቅቱ የተፈጠረቀበት ዓመት ነዉ።በርካታ ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ ሌሎች ተሰደዋል።የመገናኛ ዘዴዎች ወይም ሕትመቶች ተዘግተዋል።በካን ስሪበር አገላለፅ «ሁኔታዉ ብሷል»

Symbolbild Pressefreiheit / Tag der Pressefreiheit
ምስል picture-alliance/dpa

«የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ በመሠረቱ በ2014 ብሷል።ብዙ ጋዜጠኞች ታሰረዋል፤ በግልፅ የሚታየዉ ዞን ዘጠኝ የተባሉት ብሎገሮችና የሰወስት ጋዜጠኞች የፍርድ ሒደት ነዉ።ክሱ፤ እስራቱም ሆነ፤ ማሰደዱ በረጅም ጊዜ ሒደቱ ጋዘጠኞችን የማሸማቀቅ፤ እና መገናኛ ዘዴዎች ለመዝጋት ያለመ ሥልት ነዉ።የግሉን ፕረስ የማፅዳት እርምጃ እየወሰደ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት በፊልሞችና በሌሎች መንገዶች የግል መገናኛ ዘዴዎችን ጨርሶ ለማዘጋትና ጋዜጠኞችን ለማሰር ወይም ለማሰደድ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻ ከፍቷል።»

በዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከአንድ መቶ ሰማንያዎቹ ሐገራት አንድ መቶ አርባ-ሁለተኛ ናት።የኤርትራ፤ የኢትዮጵያን ይሁን በሌላዉ ዓለም የሚታየዉን የፕሬስ አፈና ለማሰወገድ መንግሥታት አብከረዉ እንዲጥሩ በተለይም ለጋሽ ሐገራት ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ባለሥልጣን ጠይቀዋል።

ነጋሽ መሀመድ

ተክሌ የኋላ

 

 

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ