1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሌኒየሙ የልማት ግቦችና ዕርዳታው

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6 2003

የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም የልማት ግቦች ዕውን ለማድረግ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊያበቃ በትክክል በቅርቡ ከምንይዘው አዲስ ዘመን በኋላ አምሥት ዓመታት ብቻ ይቀሩታል።

https://p.dw.com/p/QcE7
ምስል AP

ስምንት ነጥቦችን ያቀፈውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ከተሰጠው ጊዜ ሁለት ሶሥተኛው ማለትም አሥሩ ዓመት በጥቂት ዕርምጃ ተወስኖ ሲያልፍ አዳጊዎቹ አገሮች ከተናጠል ስኬቶች አልፈው ሙሉ በሙሉ ግቦቹን ማሳካታቸው የማይጠበቅ ነገር ነው። ሆኖም በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ቢቀር መለስተኛ የሆኑ ተናጠል ስኬቶች እንደሚኖሩ የሚጠራጠር የለም።                                               
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ዓመት ባለፈው መስከረም የሚሌኒየሙን ግቦች ሁኔታ ሲገመግሙ የደረሱበት ውጤት ብዙም ያረካ አልነበረም። ከዚሁ ሌላ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ ቃላቸውን በሙሉ አሟልተው ያልተገኙ ሲሆን የዓለምአቀፉ ፊናንስና ኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖም ተጨማሪ ችግር መሆኑ አልቀረም። እንግዲህ ድህነትን በከፊል መቀነሱን ዓቢይ ጉዳይ ያደረገውን የሚሌኒየሙን ግቦች የማሳካቱ ጥረት ከቦታ ቦታ የተለያየ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም። ይህ የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንድቲቲዩት ባልደረባ የዶር/ማርኩስ ሉቭም አመለካከት ነው።

“የተለያየ ዕርምጃ እየታየ ነው የመጣው። እንደምታውቀው መሠረታዊ ሰብዓዊ ዕድገትን በተመለከተ ግቡ ከ 1990 እስከ 2015 የተወሰነ ዕርምጃ ማድረግ ይሆናል። ምናልባት የመሳካት ትልቅ ዕድል ያለው በዚህ ጊዜ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች በግማሽ መቀነሱ ነው። የኤይድስን መዛመት መታገልን በተመለከተም የመጀመሪያ ዕርምጃ የሚታይ ይመስለኛል። ሌላው ብዙ አከራካሪ መሆኑ ባይቀርም በዓለም ላይ መላውን ወይም አብዛኛውን ሕጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት ማስጨረሱ የሚቻል ነገር ነው”

ማርኩስ ሉቨ አያይዘው እንደሚሉት ግቡ መላው ሕጻናት እስከ 2015 የተሟላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት እንዲያገኙ ማድረግ ይሆናል። ሁኔታው ይልቁንም የከፋ ሆኖ የሚታየው በጤና ጥበቃው ዘርፍ ነው። የሕጻናትንና የእናቶችን ሞት በመቀነሱ በኩል ብዙም ዕርምጃ አልተደረገም። ቢኖር እንኳ በቂ ሊሆን የማይችል ነው። ረሃብን በመታገሉ ረገድም እስከ አምሥት ዓመታት በፊት ድረስ ውሱን ዕርምጃ ከተደረገ በኋላ አሁን የኋልዮሽ ሂደት ነው ጎልቶ የሚታየው። ስለዚህም የዓለምን ረሃብተኛ ቁጥር በተጣለው የጊዜ ገደብ በግማሽ መቀነሱ በወቅቱ ስሌት ጨርሶ የሚቻል አይሆንም።

የሚሌኒየሙ ግቦች የእስካሁን ሂደት እንግዲህ ውሱን ስኬት ነው የሚታይበት። በሌላ በኩል ዕቅዱ ገቢር እንዲሆን ከተቀመጠው ጊዜ ሁለት-ሶሥተኛው ይንጎድ እንጂ አብዛኞቹ የበለጸጉ መንግሥታት አሁንም የገቡትን የዕርዳታ ቃል አሟልተው አለመገኘታቸው ሁኔታውን ይበልጥ የሚያከብድ ነው። እናም ዶር/ማርኩስ ሉቨ እንደሚያምኑት የወደፊቱ ዕርምጃ በሁለቱም ወገን፤ ማለት በላጋሾችና በአዳጊዎቹ አገሮች የየራስ ጥረት ላይ ጥገኛ ይሆናል።

“ይሄ እርግጥ በብዙ ሁኔታዎች ላይ ጥገኛ የሆነ ነገር ነው። አንዱ ነጥብ ቀደም ሲል እንዳነሳነው የበለጸጉት መንግሥታት ታዳጊዎቹን አገሮች በገንዘብና በምክር ምን ያህል ይደግፋሉ ነው። ሌላው ነጥብ ደግሞ ታዳጊዎቹ አገሮች ራሳቸው ከግባቸው ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ይሆናል። እዚህ ላይ የምንታዘበው በጣሙን የተለያየ ዕርምጃ ነው። አንዳንድ አገሮች ግሩም በሆነ መንገድ በማደግ ላይ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ከሣሃራ በስተደቡብ እንኳ ለዚያውም ብዙ የበለጸገውን ዓለም ዕርዳታ ሳያገኙ በብዙ የሚሌኒየሙ ግቦች ትልቅ ዕርምጃ የሚያደርጉ አልታጡም። ኢትዮጵያን ወይም ቪየትናንምን እንደምሳሌ ለመጥቀስ ደግሞ ሁለቱ አገሮች እርግጥ እንደ ሌሎች ብዙ አይሁን እንጂ ድጋፍ ያገኛሉ። በጥቅሉ በአንድ በኩል በበለጸጉት መንግሥታት ዕርዳታ ጥሩ ዕርምጃ የሚያደርጉ በሌላ በኩል ዕርዳታ ኖሮም ግን ዕድገት የማያሳዩም አሉ”

በባለሙያው ግምት የልማት ዕርዳታው ከአሁን ወዲያ በቀሩት የሚሌኒየም ግቦች አምሥት ዓመታት ውስጥ የማደጉ ተሥፋ የመነመነ ነው። በተለይም ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለው የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ዕርዳታውን ማሳደጉን ቀርቶ ባለበት ማቆየቱን እንኳ ቀላል አያደርገውም። የልማት ዕርዳታው በተገባው ቃል መሠረት ማደጉ ገና የሚያጠያይቅ ሲሆን በሌላ በኩል በበለጸገው ዓለም የልማት ፖሊሲን ባሕርይ የመለወጥ ጥረት መደረጉ ግን አልቀረም። የጀርመን መንግሥት ለምሳሌ የልማት ዕርዳታውን ወደፊት ይበልጥ በትብብር ውጤት ላይ የመሠረተ ለማድረግ ነው የሚፈልገው። ጥያቄው ይህን መሰሉ ተጽዕኖ ከቀድሞ ልምዶች አንጻር በቀላሉ የሚሰራ መሆኑ ላይ ነው።

“ሁኔታውን ለማሻሻል ከዚህ ቀደምም ብዙ ዘዴዎች ተሞክረዋል። ታዲያ በከፊል ተጽዕኖ ለማድረግ ሲቻል በከፊል ደግሞ ከባድ ነገር ሆኖ ነው የተገኘው። ሃሣቡ በተለይ በበጀት ዕርዳታ በኩል ከተወሰኑ ግቦች ላይ መድረስን ዓላማው ያደረገ ነው። ማለት ገንዘቡ በምን ተግባር ላይ ውሏል ሣይሆን ከተወሰነ ግብ መደረሱ ነው ዓላማው። ይህ ነው እንግዲህ የልማት ዕርዳታውን በውጤት ላይ የተመሠረተ የሚያደርገው”

እርግጥ የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲቱት ባለሙያ ማርኩስ ሉቨ አክለው እንደሚሉት እዚህ ላይ ሁለት ሁኔታዎችን ነጣጥሎ መመልከት ይገባል። በአግባብ የሚተዳደሩ፤ በልማት ላይ ያተኮሩ መንግሥታት ባሉባቸው አገሮች ስኬት መታየቱ አልቀረም። እዚህ ላይ ሞዛምቢክን ወይም ሩዋንዳን እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ይቻላል። በሌሎች መጥፎ ወይም አምባገነን አገዛዝ ባለባቸው በልማት ላይ በማያተኩሩ አገሮች እንግዲህ ጥያቄው የተቀመጠውን ግዴታ ካላከበሩ ምን ይከተላል ነው። የልማት ዕርዳታን ማቆም ወይም ሕዝብን ከነችግሩ ጥሎ መሄድ አማራጭ ከሆነ ግንኙነቱ ጨርሶ ነው የሚቋረጠው። ይህ ደግሞ ከውጭ የጥቅም ፖሊሲ ስሌት የተነሣ በለጋሾቹ አይመረጥም። እናም ዕርዳታውን ቀንሶ ባሉበት መቀጠሉ ነው የሚፈለገው።
በሌላ በኩል የልማት ዕርዳታ ጉዳይ ብዙ አከራካሪ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በጉዳዩ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አመለካከቶች ሲንጸባረቁ ነው የቆዩት። አንዱ ወገን የምዕራቡ የልማት ዕርዳታ ለታዳጊው ዓለም ድሃ ሕዝብ ጨርሶ አልበጀም ሲል ሌላው ደግሞ የድሃ ድሃ የተባሉት አዳጊ አገሮች ያለ ልማት ዕርዳታ ሊኖሩ አይችሉም ባይ ነው። የሆነው ሆኖ በሁለቱም በኩል ጎልቶ የሚታይ ዕውነት አልታጣም።

“ሁለቱም አመለካከቶች የተወሰኑ ሃቆችን ያቀፉ ናቸው። ሶሥተኛ እየተባለ በሚጠራው ዓለም በተለይም በደቡብ ምሥራቅና ምሥራቅ እሢያ አገሮች ለምሳሌ ስኬቱ ከየት መጣ? እነዚህ አገሮች በውጭ ዕርዳታ ሣይሆን ከሞላ ጎደል በጥቅሉ በራሳቸው ጥረት ማደጋቸውን መቀበል ያስፈልጋል። እዚህ የልማት ዕርዳታ ጨርሶ አንዳች ሚና አልነበረውም። እንግዲህ የልማት ዕርዳታ አስተዋጽኦ ምንም ወይም ውሱን ነበር ለማለት ይቻላል”

ሉቨ አያይዘው እንደሚያስረዱት በሌላ በኩል ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች በተለይም ከነዚሁ የድሃ ድሃ የሚባሉት ለብቻቸው የማደግ አቅም የላቸውም። ስለዚህም እዚህ የልማት ዕርዳታው በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በጣሙን ነው የጠቀመው። ማሊን እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ ከ 15 ዓመታት በፊት የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ተሳትፎው ከ 30 በመቶ በታች ነበር። ዛሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ወደ 80 በመቶ ከፍ ብሏል። ማሊ ታዲያ ያለ ውጩ ዕርዳታ ከዚህ ባልደረሰች ነበር። በአጠቃላይ የልማት ,ዕርዳታው ለዕድገት አስተዋጽኦ ሲኖረው ራማድ ባሉት አገሮች ግን ተጽዕኖው ውሱን እየሆነ ነው የሚሄደው።

መሥፍን መኮንን                

ሂሩት መለሰ