1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚዉኒኩ ጉባኤ- ኑክሌር-ኢራን

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2005

ሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ቦምብ መታጠቋ፥ ለዋሽግተኖች ከተስፋ ጋር የሚጠበቅ አሳሳቢ ነዉ።ኢራን ኑክሌር ለመስራት አስባለች በማባሉ ግን የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር እንዳሉት በሐይል ጭምር ሊያስወግዱት የሚገባ ለዓለም ሠላም በጣም አስጊ ነዉ።

https://p.dw.com/p/17Xxr
U.S. Vice President Joe Biden gives a speech at the 49th Conference on Security Policy in Munich February 2, 2013. Senior U.S., Russian and U.N. officials, along with the leader of the Syrian opposition, were all expected in Munich on Saturday, providing a rare opportunity for talks to revive efforts to end the civil war in Syria. REUTERS/Michael Dalder(GERMANY - Tags: MILITARY POLITICS)
ጉባኤተኞችምስል Reuters

ሰሜን ኮሪያ ኒኩሌር ቦምብ ትሠራለች።በቅርቡ የሰራችዉን ለመሞከር ዳግም ፎክራለች።ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን ታስጠነቅቃለች።ሶሪያ ትደቃለች።እስራኤል የደቀቀችዉን ሶሪያን ደብድባለች። ኢራንን ለመድገም ትዝታለች።ኢራን ከሶሪያ ጋር ሆና እስራኤልን ለመበቀል ትፎክራለች።ሚዉንክ-ጀርመን ተሰብስበዉ የነበሩት የእስራኤልና የምዕራባዉያን ሐገራት ባለሥልጣናትን ብዙ ያሰጋዉ ግን የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ሙከራ፥ ፉከራ፥የሶሪያ መደብደብ፥ የሶሪያ ኢራኖች ዉግዘት፥ የአፀፋ በትር ዛቻ-አይደለም።ሥለ ዓለም ፀጥታ ለመነጋገር ከተሰበሰቡት ባለሥልጣናት አብዛኞቹ እንዳሉት ለዓለም ሠላምና ፀጥታ በጣም የሚያሰጋዉ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ነዉ።የስብሰባዉ መነሻ፥ ሥጋቱ ማጣቃሻ፥ የዓለም ሠላም አተረጓጎም እንዴትነት መድረሻችን ነዉ።


በየመቱ-በዚሕ ሰሞን ሙዉኒክ-ጀርመን እንደሚደረገዉ ሁሉ ዘንድሮ-ባለፈዉ ሳምንትም ሥለ ዓለም ፀጥታና ሠላም በመከረዉ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተካፈሉት የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ አኽበር ሳሌሒ እንዳሉት ሁለተኛ ወሩን የያዘዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት ሲሰፋ-ለዓለም፥ ሲጠብ ለሐገራቸዉ ሠላም-ተስፋን ከቀቢፀ ተስፋ የቀየጠ ነዉ።


ቁጥርን ከመጥፎ-ጥሩ ገድ ጋር ለሚያቆራኘዉ ለምዕራባዊዉ የአጓጉል እምነት ተገዢ አስራ-ሰወስት ቁጥር የመጥፎ ሚልኪ መጥፎ-ቁጥር ናት።ኢራናዊዉ ዲፕሎማት ያን አጓጉል ሚልኪ፥ ያቺን- ቁጥርም-አልዘነጉትም።ከስላቅ-ጋር እንዲሕ አሉት፥-

«ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት ዉስጥ ነን።እንደሚመስለኝ በአስራ-ሰወስት ምክንያት፥ አስፈሪ ዓመት ይሆናል።(ግን) በዚሕ ዓመት ጥሩ-ምልክት እንዲኖር እጠብቃለሁ።በጣም በጥንቃቄ-እንዲያዉ በጥቅሉ ጥሩ ተስፋኛነኝ ማለት እችላለሁ።»

ሶሪያን ለሰወስት ቀናት ለመጎብኘት ዛሬ ደማስቆ የገቡት የኢራን የፀጥታ ምክር ቤት ሐላፊ ሳኢድ ጃሊሊ ግን የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ቀቢፀ-ተስፋ እንጂ ከጥንቃቄ ጋር የተናገሩትን በጎ ተስፋ አይጋሩም።ጃሊሊ ባለፈዉ ሳምንት ሶሪያን በአዉሮፕላን ደበደበች ያሏት እስራኤል በቀል እንደማይቀርላት ዝተዋል።አሶስየትድ ፕረስ እንደጠቀሰዉ የኢራኑ ባለሥልጣን እስራኤል በቅርቡ በሶሪያ ላይ «በፈፀመችዉ ወረራ ትፀፀታለች»።ብለዋል።

ባለፈዉ-ሳምንት ለሮብ አጥቢያ።የኩዌይቱ አሚር ሼኽ ሳባሕ ዓል-አሕመድ ዓል-ጀባር ዓ-ሳባሕ በሚያስተናግዱት ጉባኤ የሚያደርጉትን ንግግር መለማመድ፥ የሚቀበሏቸዉን የክብር እንግዶች ዝርዝር መሰረዝ-መደዝ-መቀየሩን አጠናቅቀዉ ተኝተዋል።የዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላሕ-በኩዌቱ ጉባኤ የሚሉ-የሚያደርጉትን አቅደዉ፥ ጨርሰዉ የሚጓዙበትን ሰዓት ወስነዉ ጥሩ እንቅልፍ ላይ ናቸዉ።ሌሎችም ብዙ ብጤዎቻቸዉም እንዲሁ።

የሶሪያዉ ፕሬዝዳት በሽር ዓል-አሰድ በዚያ ማለዳ የሚያደርጉ፥ ያሉበትም አይታወቅም።አሰድን ከስልጣን ለማስወገድ ከሚያዋጉት አማፂያን መሪዎች የተወሰኑት ግን በዚያች ሰዓት አልተኙም።ወይም ሠላም-ፀጥታ የማያዋዉቀዉ የደማስቆ-መዳራሻ በአስደንጋጭ ድምፅ፥ በሚትጎለጎል እሳት፥ ጢስ ጠለስ ሲናጥ-ሲጠቁር ነቅተዋል።ከማለዳዉ አስራ-አንድ ሰዓት አካባቢ «ከባድ ፍንዳታ ሰማሁ» አሉ ከአሰድ ተቃዋሚ አማፂያን የአንዱ ቡድን መሪ።

የእስራኤል የጦር ጄቶች ተልዕኳቸዉን ፈፅመዉ ተመለሱ።ነጋም።የኩዌቱ መሪ ለሶሪያ ስደተኞች መርጃ ገንዘብ ለማዋጣት የተሰበሰቡትን ከስልሳ ሐገራት የተወከሉ እንግዶቻቸዉን ያስተናግዱ ያዙ።በተከታዮቹ ቀናት ኩዌት ላይ የተዋጣዉ የገንዘብ ብዛት አስደናቂነት፥ የደማስቆ እና የቴሕራን ገዢዎች እስራኤልን የመበቀል ዛቻ ምንነት፥ የሞስኮ እና አንካራ መሪዎች ዉግዘት እንዴትነት በሚተነተንበት መሐል-የሙዉኒኩ ጉባኤ ተከፈተ።

የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር ኤሁድ ባራክ ከዋናዎቹ ጉባኤተኞቹ አንዱ ነበሩ።

«ኢራን የኑክሌር ባለቤት እንዳትሆን ለማድረግ ቆርጠናል።ማንኛዉም አማራጭ ከጠረጴዛ ላይ መነሳት የለበትም እንላለን።እኛ የምንለዉን እናደርገዋለን።ሌሎችም የሚሉትን ሲሉ ከምራቸዉ እንዲሆን እንጠብቃለን።»

የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የአስራ-ሰወስት ቁጥርን ገደ ቢስነት ከመጥቀሳቸዉም በፊት ሶሪያ፥ ድፍን መካከለኛዉ ምሥራቅም ሠላም አልነበረም።ከጠቀሱት በሕዋላም ከሠላም-ይልቅ ዉጊያ፥ጦርነት ነዉ-የሚታወጅበት።ከመካከለኛዉ ምሥራቅ-ወደ ሩቅ-ምሥራቅ እስከ አፍቃኒስታን፥ ወደ ደቡብ ምዕራብ እስከ ማሊ እስከ ሊቢያ ያለዉን ዓለም ለቃኘም ዘመኑ-1948 ሆነ-በ1950 ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ፥ ይሁን ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዓለም ሠላም ነች ማለት ያሳስታል።

በ1948 የመካካለኛዉ ምሥራቅን፥ በ1950 የኮሪያ ልሳነ-ምድር የእስኪያዘመን ሠላም ያተራመሰዉ ጦርነት እስከ ዛሬም ሆነ ዛሬ ሰክኗል ማለትም ጅልነት ነዉ።ኢራን በድብቅ የኑክሌር ቦምብ ለመስራት እየጣረች መሆኑ ከተነገረ ደግሞ አስር ዓመት አስቆጠረ።

የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር በቀደም እንዳሉት ደግሞ በምዕራባዉያን የምትደገፈዉ የእስራኤልና የምዕራባዉያን መንግሥታት ኢራንን እያስፈራሩ፥ እየቀጡ ደግሞ በተቃራኒዉ እየተደራደሩ አስር-ዓመት ሲያስቆጠሩ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ መታጠቋን በግልፅ ተናግራለች።በሁለት ሺሕ ስድስትና በሁለት ሺሕ ዘጠኝ ቢያንስ ሁለት የኑክሌር ቦምብ ፈትሻለች።

ባለፈዉ ታሕሳስ ደግሞ የረጅም-ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል ሞክራለች።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሙከራዉን በመቃወም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ቅጣት ለመጣል ሲያስጠነቅቅ ፒዮንግያንጎች ሰወስተኛ የኑክሌር ቦምብ ለመሞከር ዝተዋል።የፒዮንግዮንግ ገዢዎች ዛቻ የዩናይትድ ስቴትሱ ተሰናባች መከላከያ ሚንስትር ሊዮን ፓኔታ እንዳሉት አሳሳቢ ነዉ።

«የሰሜን ኮሪያ የጠብ አጫሪነት ባሕሪ መቀጠሉ አሳስቦናል።ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘረዉን ማንኛዉንም አይነት ነገር ፍለጋ ለመቋቋም ምን ጊዜም ዝግጁ ነን።ይሁንና በስተመጨረሻዉ (ሰሜን ኮሪያዎች) የዓለም ዓቀፉ ቤተሰብ አባል ለመሆን ይወስናሉ የሚል ተስፋ አለኝ።»

ሰሜን ኮሪያ ኑክሌር ቦምብ መታጠቋ፥ ለዋሽግተኖች ከተስፋ ጋር የሚጠበቅ አሳሳቢ ነዉ።ኢራን ኑክሌር ለመስራት አስባለች በማባሉ ግን የእስራኤሉ መከላከያ ሚንስትር እንዳሉት በሐይል ጭምር ሊያስወግዱት የሚገባ ለዓለም ሠላም በጣም አስጊ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳት ጆ ባይደንም ፒዮንግያንጎች ከታጠቁት ኑክሌር ይልቅ ቴሕራኖች ኑክሌር ለመታጠቅ አስበዋል መባሉ ነዉ-ለአሜሪካም ለዓለም ሰላምም-አስጊዉ።

«ፕሬዝዳት ኦባማ ግልፅ እንዳደረጉት መርሐችን ኢራን ያለትን እንዳታስፋፋ መከላከል አይደለም። የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጨርሶ እንዳይኖራት ማድረግ እንጂ።የኢራን መሪዎች ሕዝባቸዉን በምጣኔ ሐብት እና ከዓለም በማግለል መቅጣት እንደማያስፈልጋቸዉም ግልፅ አድርገናል።አሁንም በጫና ለሚደገፍ ዲፕሎማሲ ጊዜና ሥፍራ አለ።ኳሷ በኢራን መንግሥት ሜዳ ናት።እና ኢራን ከአምስት ሲደመር አንድ (ቡድን) ጋር ለመደራደር በጥሩ እምነት የምትቀርብበት ሥልት የምትቀይስበት ጊዜ እያለፈ ነዉ።»

ከተሠራዉ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ይልቅ ገና ሊሠራ ታቅዷል የተባለዉ ለዓለም ሠላም ማስጋቱ በርግጥ ግራ ነዉ።የዓለም ሠላም ብያኔ፥ ሠላምን ለማስከበር የሚወሰደዉ እርምጃ አተረጓጎም አጠያያቂ። ያም ሆኖ ከማሳሰብ አልፎ-የሚያሰጋዉን ዕቅድ ለማስወገድ ባይደን እንዳሉት ሐያሉ ዓለም ቅጣትን እንደ ማስገደጂያ፥ ድርድርን እንደአማራጭ ለመከተል መወሰኑ የእስራኤል-ኢራኖችን የጦርነት-ዛቻ ፉከራ ለማብረድ በዉጤቱም ለሰላም ተስፋ ጠቃሚ ነዉ።

የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ አኽበር ሳሌሒም መንግሥታቸዉ አሜሪካኖች ቃላቸዉን እንደሚያከብሩ እርግጠኛ ከሆነ ለመደራደር ዝግጁ ነዉ።

«ይሕ ድርድር የሚጀመረዉ ዩናይትድ ስቴትስ አሁን ለመደራደር ከልብ ዝግጁ መሆኗን ካረጋገጥን ብቻ ነዉ።ምክንያቱም እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን ያለን ልምድ የዚሕ ተቃራኒ ነዉ።»

ምዕራባዉያን መንግሥታት ኢራንን በማዕቀብ መቅጣት፥ ማዉገዝ፥ እንደገና ደግሞ ከኢራን ጋር መደራደሩን ዘንድሮም መቀጠላቸዉ አይቀረም።ኢራንም በምዕራባዉያን ከምትደገፈዉ ከእስራኤል ጋር እየተዛዛተች፥ ከምዕራባዉያኑ ጋር የተወዛገበች፥ በምዕራባዉያን እየተቀጣች-እየተወገዘችም ከመደራደር ባለፍ ሌላ አማራጭ አይኖራትም።

የጀርመኑ መከላከያ ሚንስት ቶማስ ደሚዜየር እንዳሉት ግን የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዩናይትድ ስቴትስን መጠርጠራቸዉ ተገቢ አይደለም።እንዲያዉም ደ ሚዜየር እንዳሉት ኢራን ጊዜ ለመግዛት በጊዜ መጨዋቷን ማቆም አለበት።

«ኢራን በጊዜ መጫወት አትችልም።ይሕን ሁሉም ተደራዳሪዎች (ተሳታፊዎች) ያዉቁታል።ኢራንም ጭምር።ሥለዚሕ ድርድሩን መጠቀም አለብን።ብዙ ዉጤት ይገኛል ብሎ መጠብቅ ግን የለብንም።»

ከድርድሩ በርግጥ ብዙ አይጠበቅም።ብዙ እንዲጠበቅ-ወይም የሚጠበቀዉ ትንሽ፥ በጊዜ ሒደት ብዙ እንዲሆን ተደራዳሪዎች መጠራጠርን፥ በመተማመን፥ እብሪትን፥ በአርቆ አስተዋይነት፥ መወጋገዝ-መፋጠጥን በትዕግስት ለመለወጥ ከዘየዱ ብቻ ነዉ።

ድርድሩ መቀጠል-አለመቀጠሉ ገና ሳይለየለት የቴል አቪቭ ቴሕራኖች ዛቻ-ፉከራ መናሩ፥ ባለፈዉ ሳምንት ሶሪያ ላይ እንደሆነዉ የእጅ አዙር ትንኮሳና ግጭታቸዉ መጠናከሩ፥ የሶሪያ አማፂያን፥ የፍልስጤም እና የሊባኖስ ደፈጣ ተዋጊዎችን በመሳሪያነት የመጠቀሙ ሽኩቻ መጋሙ የሚፈለገዉን ድርድር በሚፈራዉ ጦርነት እንዳይቀረዉ ማስጋቱ ግን አልቀረም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Bildgalerie Minister Thomas de Maiziere Kanzleramt
ቶማስ ደሚዝየርምስል dpa
Iranian Foreign Minister Ali Akbar Salehi arrives at the 49th Conference on Security Policy in Munich February 3, 2013. Senior politicians along with the leader of the Syrian opposition are in Munich providing a rare opportunity for talks to revive efforts to end the civil war in Syria. REUTERS/Michael Dalder (GERMANY - Tags: MILITARY POLITICS)
ዓሊ አኽበር ሳሌሒምስል Reuters
U.S. Vice President Joe Biden waves to the media while arriving to the Munich Conference on Security Policy, Sicherheitskonferenz, at the hotel "Bayerischer Hof" in Munich , southern Germany, Saturday, Feb. 7 , 2009. Many notable leaders participate in the 45th annual Munich Security Conference. (AP Photo/Diether Endlicher) * Eds note: German spelling of Munich is Muenchen *
ጆ ባይደንምስል AP
Israeli Defence Minister Ehud Barak arrives at the 49th Conference on Security Policy in Munich February 3, 2013. Senior politicians along with the leader of the Syrian opposition are in Munich providing a rare opportunity for talks to revive efforts to end the civil war in Syria. REUTERS/Michael Dalder(GERMANY - Tags: MILITARY POLITICS)
ኤሁድ ባራክምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ






ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ