1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማርሻል እቅድ ለአፍሪቃ

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 2009

የብሩንዲ ዜጋ ኒሙቦና ክርስቲያን ሌሎች ለአፍሪቃውያን የሚያስቡበት ምክንያት ምንድነው ሲል ጠይቋል ። ናይጀሪያዊው ያፌት ኦሞጁዋ የአፍሪቃ ችግር እና ለክፍለ ዓለሙ የሚታቀደው ሁሌም አይገናኝም ሲሉ ይተቻሉ ።

https://p.dw.com/p/2SkDD
Gerd Müller
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

Deutschlands Africa Marshallplan - MP3-Stereo

የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር በአፍሪቃ ድህነትን ለመዋጋት ይረዳል ያሉትን  እቅድ አውጥተዋል። ምዩለር፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ  አውሮጳ ከደረሰባት ጥፋት እንደገና እንድታገግም ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ምንዛሬ የ120 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ የሰጠችበት የማርሻል እቅድ ዓይነት በአፍሪቃ ተግባራዊ ለማድረግ አስበዋል ። ይሁንና በያኔው የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆርጅ ማርሻል የተሰየመው ይህን መሰል የገንዘብ እርዳታ የታሰበውን ውጤት ማምጣቱ አጠራጥሯል ይላል የዶቼቬለው የፊሊፕ ዛንድነር ዘገባ ። 
«ክለብ ኦፍ ሮም» የተባለው አንድ የጥናት ተቋም  «ዜናት ዴር ቪርትሻፍት»‘Senate der Wirtschaft‘ የሚባለው የኤኮኖሚ ጉዳዮች አጥኚ ድርጅት በጋራ ያወጡት አዲስ ጥናት  ጀርመን ለአፍሪቃ ኤኮኖሚ እድገት ከእስካሁኑ የበለጠ መሥራት እንደሚኖርባት ጠቁሟል ።በዚሁ መሠረት  እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 ድረስ ጀርመን ፣120 ቢሊዮን ዩሮ የእርዳታ ገንዘብ መስጠት ይጠበቅባታል ።የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለርም ለአፍሪቃ ይበጃል ያሉትን እና ራሳቸው ያፈለቁትን የማርሻል እቅድ የተባለውን ሀሳብ ፣ በመጪዎቹ ሳምንታት ይፋ ሊያደርጉ አስበዋል ። እስካሁን ግን ከመሥሪያ ቤታቸው ስለ ጉዳዩ የተባለ ተጨባጭ ነገር ቢኖር ጥቂት ነው ። ሆኖም ምዩለር ጉዳዩን አሁን የሚያነሱት  ስደተኞች በብዛት አውሮጳ በገቡበት በዚህ ወቅት ላይ ችግሩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው ። ከዚሁ ጋር ሰዎች በትውልድ ሀገራቸው መጻኤ እድላቸው እንዲመቻችላቸውም ጥሪ አቅርበዋል ። ባለፈው አርብ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የቀረበው የ«ክለብ ኦፍ ሮም» እና የ«ዜናት ዴር ቪርትሻፍት» ጥናት፣ካለወላጅ ተሰደው ለሚመጡ ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች ጀርመን በየዓመቱ 60 ሺህ ዩሮ ወጪ እንደምታደርግ  ያመለክታል ። ይህ እያንዳንዱ የአፍሪቃ ዜጋ በቀን ያገኛል ከሚባለው 2 ዩሮ ጋር ሲነፃጸር እጅግ ብዙ ገንዘብ ነው ።
ለመሆኑ ለአፍሪቃ የማርሻል እቅድ በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ትርጉም ይሰጥ ይሆን? የኒዠር የሥራ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ያሁሳ ሳዲሶ የሀሳቡ አድናቂ ናቸው ። ሳዲሶ ባለፈው አርብ እንዳሉት ለአፍሪቃ የታሰበው የማርሻል እቅድ በክፍለ ዓለሙ እንደ ወረርሽኝ ለተስፋፋው ፍልሰት ቀውስ እና ድህነት መፍትሄ ነው ። 
«ወጣቶች ሀገራቸው እንዲቆዩ ይረዳል ። የንግድ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ ያግዛል።በአጠቃላይ የህዝቡ መጻኤ እድል እንዲመቻች ያደርጋል ።»
ይሁን እና ለአፍሪቃ የታሰበውን ማርሻል ዕቅድ የሁሉም ድጋፍ አለው ማለት አይደለም ። የጀርመን እና የአፍሪቃ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኢንጎ ባዶሬክ ፣ እቅዱን በተለየ መንገድ ነው የሚያዩት 
«በመጀመሪያ ብዙ ሰዎች «ማርሻል ፕላን» የሚለውን አገላለጽ ለመረዳት ይቸገራሉ ።ምክንያቱም የአሁንዋ አፍሪቃ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከነበረችው ጀርመን ጋር ልትነጻጸር አትችልም ። በፓሪሱ አጀንዳ መሠረት የአፍሪቃ ባለቤትነት እንዲጨምር ነው የምንፈልገው ። ማርሻል ፕላን የሚለው ቃል ግን ለአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ማስገረሙ አይቀርም ። »
ባዶሬክ ፣አፍሪቃ የታሰበላት ማርሻል ፕላን ከሚጠቁመው በላይ ፣  የጉዳዩ አንቀሳቃሽ እና ይበልጡንም በመፍትሄው የምትሳተፍ መሆን አለባት ። በዶቼቬለ የፌስ ቡክ ገፅ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት አንዱ የብሩንዲ ዜጋ ኒሙቦና ክርስቲያን ሌሎች ለአፍሪቃውያን የሚያስቡበት ምክንያት ምንድነው ሲል ጠይቋል ። ናይጀሪያዊው ያፌት ኦሞጁዋ የአፍሪቃ ችግር እና ለክፍለ ዓለሙ የሚታቀደው ሁሌም አይገናኝም ሲሉ ይተቻሉ ። 
« «ከአፍሪቃ ጋር አታቅድም ። የልማት አጋሮች ከሰሯቸው ስህተቶች በመዛኙ ባለፉት 50 ዓመታት አፍሪቃ አላት ስለሚባሉት ችግሮች ፣ ያካሄዷቸውን አስቂኝ ምርምሮች መሠረት አድርገው በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ጠረጴዛዎች መቀመጣቸው ነው ።ሆኖም በመጀመሪያ ክፍለ ዓለሙን በማዳመጥ አፍሪቃ ምን እንደምትፈልግ ማወቅ አለባቸው ።የአፍሪቃ ችግር የልማት እርዳታ አይመስለኝም ። ይህ አለመሥራቱን ለዓመታት አይተናል ። በመጪዎቹ ዓመታትም አይሠራም ። ከአሁን በኋላ ስለነዚህ ጉዳዮች በተለየ መንገድ ነው ማሰብ ያለብን ።»
ፊሊፕ ዛንድነር

Ruanda Bundesentwicklungsminister Gerd Müller in Kigali
ምስል picture-alliance/dpa/U. Grabowsky
Flüchtlinge auf Mittelmeer
ምስል picture-alliance/Bundeswehr/S. Hoder

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ