1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሹልዝ ተጽእኖዎች

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2009

ምንም እንኳን በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ሹልስ ያገኙት ድጋፍ ቢጨምርም ብዙ ጀርመናውያን ሹልትስ ሜርክልን ያሸንፋሉ የሚል እምነት የላቸውም ።የኤስ ፔ ዴው እጩ ማርቲን ሹልዝ የምርጫ ዘመቻቸውን የጀመሩ ሲሆን ተፎካካሪያቸው የሴዴኡ እና የሴ ኤስ ኡ እጩ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግን አድፍጠው የሚከላከሉ ነው የሚመስለው ።

https://p.dw.com/p/2YOjN
Deutschland Martin Schulz in Lübeck
ምስል picture alliance/dpa/M. Scholz

የሶሻል ዴሞክራቶቹ  እጩ የሹልትስ ተጽእኖዎች

ውጤቱ በጉጉት የሚጠበቀው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ሊካሄድ ከሰባት ወራት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው ። በአሁኑ ወቅትም በምርጫው የሚካፈሉ ፓርቲዎች በየአቅጣጫው የሚያደርጉትን ዝግጅት አጠናክረው ቀጥለዋል ። በዚህ ሂደት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህፃሩ SPD በቅርቡ የሰየማቸው የፓርቲው እጩ መራሄ መንግሥት እና ሊቀመንበር ማርቲን ሹልትስ ፓርቲውን ማነቃቃታቸው እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደራቸው ትኩረት ስቧል ።  የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን የሚያስቃኘን ጉዳይ ነው ። ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ ።

ለጀርመኑ አገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄደው ዝግጅት በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የተጣማሪው መንግሥት አካል አንጋፋው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ ኤስ ፔዴ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ትኩረት ስበው ከርመዋል ። ፓርቲው የቀድሞውን የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ ፕሬዝዳንት ማርቲን ሹልትስን እጩ መራሄ መንግሥት እና መሪው አድርጎ ከሰየመበት ከዛሬ አንድ ወር ወዲህ ከፓርቲው በኩል በአመዛኙ የሚሰማው መልካም ዜና ነው ። በነዚህ ጊዜያት ፓርቲው ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ማግኘት ከመቻሉም በላይ ከ6500 በላይ አዳዲስ አባላትን ማግኘቱ ነው የተገለፀው። በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች መሠረት በዚህ አንድ ወር ውስጥ ፓርቲው ያገኘው ድጋፍ እየጨመረ ከተፎካካሪዎቹ ከእህትማማቾቹ  ከክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ሴዴኡ እና  ከክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ ሴ ኤስ ኡ ጋር ከመስተካከል አልፎ የበለጠበትም ጊዜ ነበር ።  የፖለቲካ ሳይንስ እና የህግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ያገኘውን ውጤት እንደ ብዙዎች አገላለጽ የሹልትስ ተጽእኖ ነው የሚሉት ። ይሁን እና ዋና ጥያቄ አሁን የተገኘው ድጋፍ እስከ መጨረሻው ይዘልቃል ወይስ አይዘልቅም ነው በርሳቸው አስተያየት ።

Frankreich Angela Merkel und Martin Schulz in Verdun
ምስል Getty Images/S. Gallup

በዚሁ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አር ዴ የተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ዛሬ የመራሄ መንግሥት ምርጫ ቢካሄድ ከሜርክል እና ከሹልትስ ማንን ትመርጣላችሁ ብሎ ባሰባሰበው አንድ አስተያየት መመዘኛ ደግሞ 50 በመቶው ሹልትስን 34 በመቶው ደግሞ ሜርክልን ብለዋል ።  በመመዘኛው ከተሳተፉት ግማሹ መጪው መንግሥት በሶሻል ዴሞክራቶች እንዲመራ እንደሚፈልጉ ሲያሳውቁ 39 በመቶው ደግሞ እህትማማቾቹን  ሴ ዴ ኡን እና ሴ ኤስ ኡንፓርቲዎችን እንደሚመርጡ ገልጸዋል ። የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ቀድሞ የበለጠ ድጋፍ ከነበራቸው ከነዚህ ፓርቲዎች የላቀ ድጋፍ እንዲያገኝ ካበቁት ምክንያቶች  አንዱ በእህትማማቾቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው አለመግባባት ነው እንደ ዶክተር ለማ ። ለውጤቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችንም  ዘርዝረዋል ።

Deutschland SPD Gerhard Schröder & Martin Schulz 2014
ምስል Getty Images/A. Berry

የህዝብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ የምርጫ ዘመቻ ላይ የሚገኙት ሹልስ ቢመረጡ ተግባራዊ አደርጋቸዋለሁ ያሏቸውን እቅዶቻቸውንም ከወዲሁ እያስተዋወቁ ነው ። ከመካከላቸው ፣አጀንዳ 2010  ከተባለው ከቀድሞው መራሄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር የማህበራዊ ድጎማ  እና የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት ማሻሻያ ውስጥ አንዳንዶቹን አሻሽዬ ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለታቸው እያነጋገረ ነው ። ይህ እቅዳቸውም ከተቀናቃኞቻቸው በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል ። በአሁኑ ጊዜ በማነጋገር  ላይ ስላለው የሹልትስ እቅድ ምንነት ዶክተር ለማ ማብራሪያ አላቸው ።

የኤስ ፔ ዴው እጩ ማርቲን ሹልዝ በዚህ ዓይነት መንገድ የምርጫ ዘመቻቸውን የጀመሩ ሲሆን ተፎካካሪያቸው የሴዴኡ እና የሴ ኤስ ኡ እጩ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግን በዶክተር ለማ አባባል አድፍጠው የሚከላከሉ ነው የሚመስለው  ።

ምንም እንኳን በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ሹልስ ያገኙት ድጋፍ ቢጨምርም ብዙ ጀርመናውያን ሹልትስ ሜርክልን ያሸንፋሉ የሚል እምነት የላቸውም ። በዚህ ረገድ በተሰባሰበ አስተያየት 50 በመቶው ሹልትስ መራሄ መንግሥት መሆናቸውን ይጠራጠራሉ ። 36 በመቶው ደግሞ አይሳካላቸውም የሚል እምነት ነው ያላቸው ። ይሁን እና  ዶክተር ለማ እንዳሉት በጎርጎሮሳዊው መስከረም 24 ፣ 2017 ዓም በሚካሄደው ምርጫ ነው የአሸናፊው ማንነት የሚታወቀው ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ