1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማስትሪኽት ውል አሥረኛ ዓመት

ሐሙስ፣ ኅዳር 3 1996
https://p.dw.com/p/E0g9
የአውሮጳው ማኅበረሕዝብ አባልሀገራት ርእሳነብሔርና መራህያነመንግሥት ማስትሪኽት በተባለችው የኔደርላንድ ከተማ አ.ጎ.አ. በየካቲት፣ ፲፱፻፺፪ የተፈራረሙት ውል ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ እ.ጎ.አ. በኅዳር አንድ፣ ፲፱፻፺፫ ጽናት አግኝቶ “የማስትሪኽቱ ውል” በመባል ከፍተኛውን የታሪክ ምዕራፍ ይዟል። ፀድቆ ጽናት ካገኘ ወዲህ አሁን ይኸው አሥር ዓመታት አስቆጥሮአል ማለት ነው። የማስትሪኽቱ ውል የአውሮጳው ማኅበረሕዝብ የእድገት ደረጃዎችን ተሸጋግሮ “የአውሮጳው ኅብረት” እንዲሆን ያበቃው ከመሆኑም በላይ፣ ለአውሮጳው የኤኮኖሚና የሸርፍ ኅብረትም መሥፈርቶችን አኖረለት። ይኸው የኤኮኖሚና የሸርፍ ኅብረት በበኩሉ እ.ጎ.አ. በጥር አንድ፣ ፲፱፻፺፱ በመጀመሪያ ፲፩ ሀገሮችን ያጣመረ የጋራ ሸርፍ “ኦይሮ” እንዲፈጠር አስቻለ። ግን ከአሥር ዓመታት በፊት ለኤኮኖሚውና ለጋራው ሸርፍ እርጋታ የተሠመሩት መስፈርቶች(እነዚሁም “የማስትሪኽት መስፈርቶች” ነው የሚባሉት) በአንዳንድ አባላት ዘንድ ሙሉ ክንውን ማግኘት እየተሳናቸው ነው የተገኙት።

በማስትሪኽት የተደረሰው የኤኮኖሚ እና የሸርፍ ኅብረት ውል በአንድ የጋራ ሸርፍ ፈጠራ ጉልላቱን እንዲያገኝ በተፈለገበት ወቅት ጉልህ ጥያቄ ነበር የተደቀነው፥

»» ለመሆኑ የተለያዩ ብሔራዊ ኤኮኖሚዎች፣ የተለያዩ የኤኮኖሚ ሂደቶች፣ የተለያዩ የቀረጥ አሰባሰብና የሥራ ጉዳይ ሕግጋት፣ የተለያዩ የወረት ሽግግር ድንጋጌዎች ባሉባቸው በ፲፭ቱ ሀገሮች ውስጥ እንዴት ነው የጋራው ሸርፍ ግብ የሚደረስበት?«« የሚል ነበር ግዙፉ ጥያቄ።

መልሱም፥ የአዲሱ የጋራ ሸርፍ አባል የሚሆኑት ሀገራት በአንድ የጊዜ ገደብ ውስጥ መፈፀም ያለባቸው ጥብቅ አሣሪ መስፈርቶች እንዲደነገጉ ግዴታ ነው የሚል ነበር።

በእነዚያው መስፈርቶች አማካይነት የአውሮጳ ብሔራዊ ኤኮኖሚዎች ተቀራርበው እንዲጠማመሩ፣ በተቻለ መጠን በያለበት ያልተዘናነፈ፣ አቻ ሂደት ያለው ኤኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲኖር ነበር የተፈለገው። አንድ ጠንካራና ርጉእ ሸርፍ እንዲኖረው የሚፈልገው ወገን፣ አንድ ነፃ ማዕከላይ ባንክ፣ ውዥቀት የሌለበት ጥብቅ የዋጋ ደረጃ፣ ጤናማ የመንግሥት ፊናንስ አውታር፣ የተረጋጋ የምንዛሪ ተመን ሂደት እና ዝቅተኛ የባንክ ወለድ ደረጃ እንዲኖረው ያስፈልጋል ነበር የተባለው። የመንግሥትን ዕዳ ማሳነስና ቁጠባን ማጠናከር ነበር ሌላው ግዴታ። እነዚህ መስፈርቶች ካልተሟሉ ግን፣ ሀገራቱ የሸርፉ ኅብረት አባላት የሚሆኑበት በር የሚዘጋባቸው ይሆናል።

የኋላ ኋላ ታዲያ፣ ራሳቸው ጀርመናውያኑ ነበሩ በግዙፉ የበጀት ጉድለት ምክንያት የኤኮኖሚ ርጋታ መስፈርቶችን ማሟላት እየተሳናቸው የተገኙት። በዚህ አንፃር ደግሞ፣ በንቀት ሲታዩ የነበሩት እስጳኝንና ፖርቱጋልን የመሳሰሉት የደቡብ አውሮጳ ሀገሮች አለቅጥ ከፍተኛ ሆኖባቸው የነበረውን የዋጋውን ግሽበት አስገራሚ ሁኔታ ለማሳነስ፣ የበጀታቸውን ጉድለት በጉልህ ለማሻሻል እና የመንግሥትን ዕዳ ለመቀነስ ችለው ተገኙ። የእነዚያው ተንቀው የነበሩት የደቡብ አውሮጳ ሀገሮች ክንውን ብዙዎቹን ጀርመናውያን የኤኮኖሚ ጠበብት በጣም ነበር ያስገረመው።

ቪስባደን ከተማ ውስጥ የሚገኘው የጀርመን ፈደራዊ መዘርዝር-አቅራቢ ተቋም እ ጎ አ በፀደይ ፲፱፻፺፰ የሰጠው መረጃ ጀርመን ውስጥ ደስታን ፈነጠቀ፥ ይኸውም፣ በመዘርዝሩ መሠረት፣ የጀርመን መንግሥት አዲስ ዕዳ ደርቦ መድፈን ያለበት፣ በወጭውና በገቢው መካከል የነበረው ክፍተት በ፲፱፻፺፯ ፩፻፪ ሚሊያርድ ማርክ--ወይም ከጠቅላላው የጀርመን ኤኮኖሚያዊ ውጤት ፪-ነጥብ-፯ በመቶ ብቻ ሆኖ መገኘቱ ነበር። በዚህ አኳኋን፣ ጀርመን የአውሮጳው የጋራ ሸርፍ ክበብ አባል የምትሆንበትን መንገድ ከዋናው መሰናክል በቀላሉ አድናው ተገኘች። በጋራው ሸርፍ የሚጣመረው እያንዳንዱ አባል-መንግሥት ለበጀቱ ጉድለት መሸፈኛ የሚሸከመው ዕዳ በጠቅላላው ብሔራዊ ውጤት አኳያ ከ፫ በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ነው ዐቢዩ መስፈርት።

የአውሮጳው ኅብረት እ ጎ አ በግንቦት ፫. ፲፱፻፺፰ ብሩክሴል ውስጥ በመሪዎች ደረጃ በከፈተው ልዩ ዐቢይ ጉባኤ ላይ፣ ለጋራው ሸርፍ አባልነት የማስትሪኽቱን መሥፈርት ያሟሉት ሀገሮች የትኞቹ እንደሆኑ በግልጽ ታወቀ። ከ፲፭ቱ የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገሮች መካከል ፲፩ዱ በጋራው ሸርፍ ኦይሮ ሲጣመሩ፣ ሦሥቱ ሀገሮች--ስዊድን፣ ዴንማርክና ብሪታንያ ብቻ ነባር ብሔራዊ ሸርፋቸውን--ማለት ክሮነን እና ፓውንድን እንደያዙ ቆዩ። በዚህ አኳኋን፣ እያንዳንዱ እንቅፋት ተወግዶ፣ የአውሮጳውን የሸርፍ ኅብረት ግብ እውን ለማድረግ ተቻለ።

እ ጎ አ በጥር ፩ ፲፱፻፺፱ የአውሮጳው የሸርፍ ኅብረት ሦሥተኛ እርከን ተከናውኖ፣ የጋራው ሸርፍ ኦይሮ ተፈጠረ። የአዲሱ ገንዘብ የበላይ ጠባቂ ይሆን ዘንድ፣ አዲስ የተመሠረተው የአውሮጳው ማዕከላይ ባንክ ማዕከላዊ መሥሪያቤቱን በጀርመን የንግድ መዲና ፍራክፉርት አድርጎ ሥራውን ጀመረ። ግሪክ በመጀመሪያ የጋራ ሸርፍ አባልነቱን መሥፈርት ማሟላት ተስኗት ብትገኝም፣ እ ጎ አ በ፪ሺ መግቢያ ላይ የሚጠየቅባትን ሁሉ አጠናቅቃ ፲፪ተኛይቱ የኦይሮ ሀገር ለመሆን በቃች።

ይህ እንግዲህ የታሪክ ጉዳይ መሆኑ ነው። ግን ከአሥር ዓመታት በፊት በማስትሪኽት የተደረሱት የአባልነት መሥፈርቶች አሁንም እንደፀኑ ናቸው። የማይዋዥቅ ጥብቅ የዋጋ ደረጃ፣ ጤናማ የመንግሥት በጀት፣ ርጉእ የምንዛሪ ተመን እና ዝቅተኛ የወለድ ደረጃ--እነዚህ ነበሩ ለጋራው ሸርፍ ኦይሮ ተሳትፎ አስፈላጊ የነበሩትና የሆኑትም መሥፈርቶች። ለጀርመናውያን ግን ይህም በቂ ሆኖ አልታየም ነበር። ስለዚህ፣ የቀድሞው ገንዘብ ሚኒስትር ቴዎ ቫይገል ባቀረቡት ማሳሰቢያ መሠረት፣ እ ጎ አ በ፲፱፻፺፮ ደብሊን ውስጥ አንድ የኤኮኖሚ ማረጋጊያና ዕደገት ውል ተደረሰ። በዚህም መሠረት፤ የኦይሮ ተጣማሪዎቹ ሀገሮች የአባልነቱን መሰናክል ከተወጡት በኋላ የበጀቱን ቁጥብነት እያላሉ የጋራውን ሸርፍ ርጉእነት እንዳያፋልሱት ለማድረግ ነበር የተፈለገው።

በአውሮጳው ኮሚሲዮን መመሪያ መሠረት፣ እ ጎ አ እስከ ፪ሺ፬ ድረስ አባላቱ ሀገሮች በተቻለ መጠን የተስተካከለ በጀት ማቅረብ አለባቸው። ይህም ሲሆን የበጀቱ ጉድለት እስክ ነጥብ-፭ በመቶ ሊደርስ እንደሚችልም ነበር የተደነገገው። የአንዲት አባል-ሀገር የበጀት ጉድለት ወደ ፫ በመቶ እየተጠጋ በሚገኝበት ጊዜ ያችው ሀገር ይህንኑ እንድታሰተካክል አንድ ሰማያዊ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይላክላታል። ግን አንዲት ሀገር ያንኑ የ፫ በመቶ ገደብ አልፋው ከተገኘች፣ የበጀቱን ጉድለት የሚመለከት የግሳጼ ሥርዓት ይከፈትባታል። ይኸው የግሳጼ ሥርዓት መቀጫንም ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም፣ በ፫ በመቶ የተገደበውን የበጀት ጉድለት አልፋው የተገኘችው አባል-ሀገር ለምን ይህን እንዳደረገች ተመርምሮ ችግሩዋ ከታወቀላት፣ ከመቀጫው ልትድን የምትችልበትም ሥርዓት ነው የሚሠራበት። አጥፊው መንግሥት የትኛው ድንጋጌ እንደሚተላለፍበት የሚወስኑት የአውሮጳው ኅብረት አባል-ሀገራት ናቸው። ያው በጀት አጉዳዩ መንግሥት ራሱን ማሻሻል እየተሳነው ከተገኘ፣ እንደ ጥፋቱ ክብደት መጠን ከጠቅላላው ብሔራዊ ገቢ ከነጥብ-፪ በመቶ እስከ ነጥብ-፭ በመቶ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ሊወሰንበት ይችላል።

በማስትሪኽት የተመሠረተው የኤኮኖሚና የሸርፍ ኅብረት በጠቅላላው ሲታይ የሥምረት ታሪክ ነው የሚንፀባረቅበት። አዲሱ የጋራ ሸርፍ ኦይሮ በአሜሪካው ዶላር አኳያ ያለው አቅም ርጉእ ሆኖ ነው የቆየው፣ እንዲያውም ብዙ ማዕከላይ ባንኮች ዛሬ አስተማማኙን ኦይሮ ተካባች ጠንካራ ሸርፍ እያደረጉ ይጠቀሙበታል። ይህም ለኦይሮ ቦታ የለቀቀው የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ሸርፍ ዶይቸ-ማርክ ይዞት የነበረው ሚና ነው። ኦይሮ ዛሬ ዓለምአቀፉን እም’ነት ያተረፈ ጠንካራ ሸርፍ ለመሆን በቅቷል። ግን ሁኔታውን ከቅርቡ በትኩረት ሲመረምሩት፣ ሚዛኑ እምብዛም አርኪ አይደለም፥ ይኸውም የኦይሮ ርጉእነትና ጥንካሬ ራሱ ጀርመን ውስጥ የኤኮኖሚውን ዕድገትና ሂደት ሊያነቃቃው አልበቃም። ብዙ ሰዎች በኦይሮ አኳያ የጥርጥር ስሜት ነው የሚጎላባቸው፤ እንዲያውም ይኸው አዲሱ ሸርፍ እ ጎ አ በጥር ፩ ፪ሺ፩ ጥሬ ገንዘብ ሆኖ ለመገበያያ ከቀረበ ወዲህ በጀርመንኛ “ቶይሮ” የተሰኘውን የምሬት ቃል ነው ሕዝቡ የለጠፈበት-- “ቶይሮ” ውድነትን የሚያመለክት ቃል ነው--ኦይሮ ሁሉን ነገር ውድ አደረገው እየተባለ ነው ከሕዝቡ/ማለት ከሸማቹ ሕዝብ ብርቱ የምሬት ስሜት የሚወረወርበት። ሌላው ቀርቶ የጋራው ሸርፍ ከበብ ዐበይት አባላት የሆኑት፣ በዚሁ ዙሪያ እጅግ ግዙፉ ኤኮኖሚ ያላቸው ጀርመን፣ ኢጣሊያ እና ፈረንሳይ እንኳ በበጀት ጉድለት ረገድ በማስትሪኽት የተደነገጉትን መሥፈርቶች ጥሰው በመገኘታቸው አሁን ብዙ ነቀፌታና ግሳፄ ነው የሚቀርብባቸው።

አውሮጳውያኑ በፍራንክፉርት ከተማ አዲስ ማዕከላይ ባንክ ቢፈጥሩም፣ አባላቱ ሀገሮች በበጀት መርሕ ረገድ የየራሳቸውን የውሳኔ ሥልጣን እንደያዙ ነው የቆዩት። “የኦይሮ ርጉእነት ጠባቂ” የሚሰኘው የአውሮጳው ኅብረት ኮሚሲዮን በበጀት ጉድለት ጥፋተኞች አንፃር በቂ የማዕቀብ ሥልጣን የሌላው አካል ሆኖ ነው የሚታየው። የሆነ ሆኖ፣ አሁን የገንዘብ መርሕ ጠበብት እንደሚሉት፣ ኦይሮ በዶላር አኳያ ማለፊያ የምንዛሪ ተመን ያለው መሆኑ ራሱ አርኪ ነው፣ ባሁኑ የኤኮኖሚ ሁኔታ ኦይሮ በዶላር አኳያ ድክመት ቢኖርበት ኖሮ፥ ቀውስ የሚደቀን በሆነም ነበር። ይኽውም፥ ኦይሮ ደካማ--ዶላር ደግሞ ጠንካራ ቢሆን ኖሮ፣ የሸርፉ ኅብረት ከዶላር ግብይት አካባቢ የዋጋን ግሽበት የሚያግበሰብስ በሆነም ነበር ማለት ነው። የአውሮጳውም ማዕከላይ ባንክ መፍትሔ በሌለው ከባድ እክል የሚፋጠጥ ነበር የሚሆነው። የኦይሮ ጥንካሬና ርጉእነት ከዚሁ እክል ለመዳን አስችሏል።