1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2009

ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከኾኑ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ነጥቦች መካከል ሁለት ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል። የአንድነት ኃይሎች እና የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች የወደፊት የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ በሚል በውጭ ሃገራት በተናጠል ያደረጓቸው ውይይቶች ቀዳሚው ነው። እጅግ አናጋጋሪ ኾኖ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/2SAvj
Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተደነገገ ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ጥቅምት 12 እና 13 ነበር በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የአንድነት እና የዘውጋዊ ፖለቲካ አቀንቃኞች በተናጠል ለውይይት ጥሪ ያስተላለፉት። የሀገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ ለማመላከት በሚል የተጠራው ስብሰባ በተመሳሳይ ቀናት ግን ደግሞ በተለያዩ የፖለቲካ ርእዮተ-ዓለም አራማጆች፤ በተለያዩ ቦታዎች ለንደን እና ዋሽንግተን ውስጥ ነበር የተከናወኑት።

በውይይቶቹ ላይ የተነሱ ሐሳቦች በተለይ የለንደኑ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሰፊ መወያያ ርእስ ኾኖ ቆይቷል። በለንደኑ ውይይት ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ ከተንጸባረቁ ሐሳቦች መካከል በአማርኛ የተተረጎሙ የሁለት ሰዎች ንግግሮች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በስፋት ተሰራጭተዋል፤ እጅግም አነጋግረዋል።

ከሐሳቦቹ መካከል የኦሮሞ መብትን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን መበታተን ያስፈልጋል የሚል ጠንከር ያለ አመለካከትም ተንጸባርቋል። በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችን በቅርበት ለተከታተለው ተስፋለም ወልደየስ ስብሰባዎቹ የተለያየ ስሜት ፈጥረዋል። 

እነዚህን ስብሰባዎች በተመለከተ ኤፍሬም አደባባይ በትዊተር ገጹ የሚከተለውን  አስነብቧል። «ከኢትዮጵያ መፍረስ በፊት የእኔን መፍረስ የማስቀድም - ኩሩ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ።» 

እሸቱ ሆማ ቄኖ ደግሞ፦ «የትግሉ መሪም ሆነ ባለቤት መሬት ላይ ደሙን አጥንቱንና ሕይወቱን እየገበረ ያለው ምርጥ የኦሮሞ ልጅ እንጂ ለንደን ላይ ተቀምጦ የሚጮህ ተስፈኛ አይደለም። የኦሮሞን መፃኢ እድል የሚወስነው ደግሞ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ነው። አለቀ።» ሲል በፌስ ቡክ አስፍሯል። 

Twitter Logo
ምስል Reuters/K. Pempel

መርጋ ዮናስ ከለንደኑ ጉባኤ ተቆንጽለው የቀረቡት አጠር ያሉ የቪዲዮ ምስሎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጎልተው በመውጣት ተራግበዋል፤ ሙሉ ውይይቱን ተከታትየዋለሁ፥ መንፈሱም ሌላ ነው ብሏል።

የአዲሱ ካቢኔ አባላት ሹመትን በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ከቀረቡ አስተያየቶች የተወሰኑትን እንመልከት። አምደ-መረብ ጸሐፊው ዳንኤል ብርሃኔ «እንኳን ከዘመነ ሲቪል ሰርቪስ ወደ ዘመነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም አሸጋገራችሁ» ሲል ጽፏል። 

የዞን ዘጠኝ ጦማሪ፣ በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ ፍትኅ ማዕከል ተመራማሪው ዘላለም ክብረት በትዊተር ገጹ፦ ገዢው ፓርቲ ባለፉት ስድስት ዓመታት አራተኛውን የካቢኔ ሹም ሽር እንዳደረገ በመግለጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፎ ቀጣዩን ስላቅም አያይዞ አስነብቧል። «ያሳማ ኮሚቴ፣ የጅብ ሊቀመንበር፣ የጦጣ ጸሐፊ፣ ኧረ ተይ አንች ቀን፣ ቶሎ ቶሎ እለፊ።" ይላል ገበሬ ሲጨንቀው» ሲል አስፍሯል። 

በፌስቡክ ገጹ ላይ በእንግሊዘኛ እና በአፋን ኦሮሞ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፉ ጸጋዬ አራርሳ ደግሞ እንዲህ የሚል አስተያየት አቅርቧል። «ለፖለቲካዊ ችግር ቴክኒካዊ መፍትኄዎች፤ አይሠራም።»

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

አብራሃ ደስታ በፌስቡክ ገጹ፦ «አዲስ ስርዓት እንጂ አዲስ ካቢኔ መፍትሔ አይሆንም!» በሚል ርእስ ዝርዝር ጽሑፍ አስነብቧል። ጽሑፉንም ሲያጠቃልል «የምንፈልገው የስርዐት ለውጥ እንጂ የካቢኔ ለውጥ አይደለም» ብሏል። 

የዞን ዘጠኝ ጦማሪ፣ ጸሐፊ እና አራማጅ በፍቃዱ ኃይሉ በትዊተር ገጹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፏል፦ «ጥያቄ ኾኖ ሊቆይ የሚችለው፥ አዲሱ ካቢኔ እኛን የሚወክል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይኖረው የምንፈልጋትን አዲስ ኢትዮጵያ መገንባት ይችል ይኾን የሚለው ነው።» ሲል አስነብቧል። 

የኢንተርኔት አገልግሎት መገደቡ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የነቃ ተሳትፎ የነበራቸው በርካታ ጸሐፍት አንድም ከመድረኩ እንዲርቁ አንድም በተገኘችው ቀዳዳ ብቅ ጥልቅ እንዲሉ ብቻ አስገድዷቸዋል። ሌላው ሰሞኑን ጎልቶ የወጣ ነጥብ ነው።

ለወትሮው በፌስቡክ ገጻቸው በርካታ ጽሑፎችን ያስነብቡ የነበሩት የቀድሞው ብቸኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ድንገት የኢንተርኔቱ ዓለም ላይ ብቅ ብለው አጠር ያለ ጽሑፍ አስነብበዋል። «ጎበዝ ጠፉው ምን ላድርግ የቢሮም የሞባይልም ኢንተርኔት በማጣቴ ነው:: ለማነኘውም "የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብርቅ ነው?" በሚል እከስታለሁ....» የሚል ጽሑፍ ከነጠብጣብ ምልክት ጋር አስፍረዋል።  

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዳንድ ከውጭ ሃገራት ሥርጭታቸውን የሚያስተላልፉ የመገናኛ አውታሮች መከታተል፣ ማስተላለፍና ሪፖርት ማድረግን አግዷል። የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቢሲ ግን ተከልክለዋል ካላቸው ጣቢያዎች ምስሎችን ሲያሳይ የታዘቡ  ጸሐፍት ሕጉ አንዱ ላይ የሚጸና ሌላውን በጎን የሚመለከት ነው ሲሉ ተችተዋል። 

Facebook Symbol
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Rourke

አንዳንድ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው አካላት እና ግለሰቦችም መንግሥት እንደከለከላቸው ካስነገረባቸው ማሰራጪያ ጣቢያዎች በድፍረት ሲጠቃቅሱ፣ ጽሑፎችንም ከመገናኛ አውታሮቹ እየቀነጨቡ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ሲያቀርቡ ይታያል። ይኽ መንግሥት አወጣኹት ካለው ሕግ ጋር እርስ በእርሱ ከመጋጨቱም ባሻገር አተገባበሩ ለቤት ልጅ እና ለባዳ  ለየቅል አስብሏል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በእጅ ስልክ መቋረጥ አለያም መገደብ የፈጠረው መሰናከል ከኢትዮጵያውያንም አልፎ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የውጭ ተቋማት ላይ መሰናክል መፍጠሩ ተነቧል። የኢንተርኔት መቋረጡ ከኢትዮጵያ ይወጡ የነበሩ ወቅታዊ ጉዳዮች እንደቀድሞው በስፋት እና በተደጋጋሚ እንዳይወጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን  የአሜሪካ ኤምባሲ ላይም ጫናውን አሳርፏል። ኤምባሲው ድረ-ገጹ ላይ ባስነበበው ጽሑፉ፦ የኢንተርኔት ገደቡ ቀደም ሲል ከነበሩት አገልግሎቶች እንደ ዲቪ ሎተሪ እና አሜሪካን ሀገር ሊያስኬድ የሚችሉ የትምህርት ዕድሎች ላይ መሰናከል እንደፈጠረበት አስታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ