1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2009

የብሪታንያው ቢቢሲ ዓለም አቀፍ ማሠራጪያ ጣቢያ በኢትዮጵያ ሦስት ቋንቋዎች ስርጭት ሊጀምር መኾኑ በማስመልከት ያሰፈረው እና ቆየት ብሎ ያስተካከለው አጠር ያለ ገለጣ ብዙዎችን አነጋግሯል።  ድረ-ገጽ ጸሐፊው በፍቃዱ ኃይሉ ዳግም መታሰርም መነጋገሪያ ኾኖ ዘልቋል።

https://p.dw.com/p/2SvAw
Soziale Netzwerke
ምስል imago/Schöning

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በዚህ ሳምንት በኢንተርኔቱ ዓለም መነጋገሪያ ኾነው ከዘለቁ ርእሰ-ጉዳዮች መካከል የዞን ዘጠኝ ድረ-ገጽ ጸሐፊው በፍቃዱ ኃይሉ ዳግም መታሰር ዋነኛው ነበር። ከባለፈው ሳምንት አንስቶ የዚህ ሳምንትም መነጋገሪያ ኾኗል። የብሪታንያው ዓለም አቀፍ የመገናኛ አውታር  ቢቢሲ በተለያዩ የአፍሪቃ እና የእስያ ቋንቋዎች ተጨማሪ ሥርጭት በመጀመር አድማሱን ለማስፋት ማቀዱን የገለጠበት ማብራሪያ ብዙዎችን አነጋግሯል። ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ እና በትግሪኛ ሥርጭት እንደሚጀምር ገልጦ ያሰፈረው ማብራሪያ በተለይ የአማርኛው እና የኦሮሚኛው እጅግ አወዛግቧል። ቢቢሲ ወዲያውኑ ማስተካከያ ቢያደርግም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ግን የመነጋገሪያ ርእስነቱ ቀጥሏል።

የዞን ዘጠኝ ድረ-ገጽ ጸሐፍት ከሆኑት አምደኞች መካከል በፍቃዱ ኃይሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ዳግም ለእስር መዳረጉ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በርካቶችን አስቆጥቷል። ዮሐንስ ሞላ በፌስ ቡክ ገጹ፦ «በጣም የምወደውና የማከብረው፣ ብሩሁ እና ልበ ብርቱው ወዳጄ፥ የዞን ዘጠኙ ጦማሪ እና ጸሐፊ፣ በፍቃዱ ኃይሉ “ኮማንድ ፖስቱ ይፈልግሃል” ተብሎ ታስሯል። የእስሩ ምክንያትም ከቪኦኤ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ መሆኑ ተገልጿል። ሰላምህ ይብዛ፣ ፈጣሪ ካንተ ጋር ይሁን በፍቄ!»  ሲል ጽፏል።

«በሌላ ዜና» ሲል ጽሑፉን የሚቀጥለው ዮሐንስ «መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በ1 ወር ውስጥ 11 ሺህ 607 ሰዎችን ማሰሩን ገልጿል። በጣም ብዙ ነው። እንግዲህ ይህን ያህል ቁጥር ያመኑት ከሆነ፥ ያላመኑትንም መገመት ነው። የተገደለውንስ በምን ያህል ቁጥር ሪፖርት ያደርጉ ይሆን?» አገሩ ታሰረ፣ እስር ቤት መቀለስ እንደ ድሮው ቀረ (ግርማ ተስፋው)» ሲል ጽሑፉን ደምድሟል።

በላይ ማናዬ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው አጠር ያለ የእንግሊዝኛ ጽሑፉ፦ «አንዱ እና ብቸኛው በፍቃዱ ኃይሉ! ትክክል ነው ብሎ የሚያምንበትን በመናገሩ በድጋሚ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል» ብሏል። በላይ ማናዬ ሀሽ ታግ በመጠቀም በፍቃዱ ከእስር ነጻ እንዲወጣ ጠይቋል።  

በፍቃዱ የታሰረው ለአሜሪካ ድምጽ በሰጠው ቃለ ምልልስ መኾኑ ተገልጧል። ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር በላይ  አብሮት ታስሮ የነበረው ባልደረባዬ ተስፋለም ወልደየስ ግን እስሩ የማይቀር መኾኑን በፍቃዱ አስቀድሞ አውቆታል ይላል። ለዚያ ደግሞ በፍቃዱ ከመታሰሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፎ ድረ-ገጽ ላይ ያሰፈረውን ዘለግ ያለ ጽሑፍ ይጠቅሳል። 

የአሜሪካ ድምጽ በፌስ ቡክ ገጹ «ለበፍቃዱ እስር ምክንያት ለአሜሪካ ድምጽ የሰጠው ቃለምልልስ ነው ተባለ» የሚል ዜና አስነብቧል። «ለበፍቃዱ እስር ምክንያት ነው የተባለው ቃለ ምልልስ» በሚል ሐረግ ስር «ለጥያቄዎ መልስ ውይይት» የሚል ርእስ የተሰጠው የፌስቡክ መልእክት ይነበባል። «የኢንተርኔት አምደኛው በፍቃዱ ኃይሉና የተቃዋሚው አረና ትግራይ ፓርቲ አባሉ አብርሃ ደስታ ጋር የተደረግ ውይይት» የሚል ጽሑፍም አለው። የድምጽ ማዕቀፍም ተያይዟል። አብራሃ ደስታ በትዊተር ገጹ፦ «ጓደኛዬ በፍቃዱ ኃይሉ ዛሬ በድጋሚ ታሰረ። በጣም ያሳዝናል» የሚል ጽሑፍ አስፍሯል። 

ከበፍቃዱ ኃይሉ ውጪ በእስር ላይ ስለሚገኙ ጋዜጠኞች የሚያወሱ ጽሑፎችም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተነበዋል። ያልተነገሩ ታሪኮችን የሚያቀርበው Untold Stories   በፌስቡክ ባስነበበው ጽሑፉ አብዲ ገዳ ከአዳማ ማለትም ናዝሬት ከተማ መሰወሩን የሚገልጥ ጽሑፍ አውጥቷል። «የኦሮሚያ ማሰራጪያ አገልግሎት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ አብዲ ገዳ አዳማ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ረቡዕ ተሰውሯል። የት እንደሚገኝ አይታወቅም። ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ እና ወዳጆቹ ማእከላዊ እና ዝዋይን ጨምሮ በየእስር ቤቶቹ እና ማጎሪያዎቹ አስፈልገውታል።

Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

በሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች የተሰወሩ እና ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ በመሆናቸው ጋዜጠኛ አብዲ ገዳም በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይላት እንደታፈነ አብዛኞቹ ቤተሰቦቹ እና፤ ጓደኞቹ ብሎም ወዳጆቹ ያምናሉ። ጋዜጠኛ አብዲ ገዳ በ2014  ከኦሮሚያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በአንድ ጀምበር ከተባረሩት 20 ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር» ሲል ጽሑፉ ይጠናቀቃል።

«ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ከ1940 ወዲህ እጅግ መስፋፋቱን አስታወቀ» በሚል ርእስ የወጣው ዜና ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የደስታ ዜና ይዞ የመምጣቱን ያኽል መወዛገቢያም ኾኗል። ጣቢያው ከአንድ ወር በኋላ በሚጠባው የጎርጎሮሳዊው 2017 ዓመት ውስጥ  ስርጭት ሊጀምርባቸው ያቀደባቸውን 11 ቋንቋዎች ይፋ አድርጓል። ከሕንድ ከናይጀሪያ እና ከኢትዮጵያ ሦስት ቋንቋዎች እንዲሁም የኮሪያ ቋንቋ ይገኙባቸዋል። ጣቢያው ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ሊያሰራጭባቸው የመረጣቸው ቋንቋዎች አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ እና ትግሪኛ እንደሆኑ ገልጧል። 

ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ  በፌስቡክ ገጹ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባሰፈረው ጽሑፉ፦  «ቢቢሲ ወደፊት ስለሚጀምራቸው ቋንቋዎች የሚከተለውን ዝርዝር አትሞ ነበር» በማለት ይንደረደራል። ጽሑፉ ቢቢሲ  ቀደም ሲል በኢንተርኔት ይፋ አድርጎት ወዲያው ኢንተርኔት ላይ ማስተካከያ ያደረገበት የመጀመሪያ ዝርዝር በፎቶ መልክ ተካቶበታል። የአርጋው ጽሑፍ፦ «አማርኛ እንደ ቤተክርሥቲያን ቋንቋ ነው የተገለጠው  (ትክክል አይደለም) አማርኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ነው (ገላጭ ቃል አያስፈልግም)  አፋን ኦሮሞ ግብጽ ውስጥ ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም (ልክ ነው?)» ሲል ያጠይቅና «ከዚያ ውጪ ግን ይኽ የቢቢሲ ታላቅ እመርታ ነው። አመሰግናለሁ» በማለት ያጠቃልላል። 

አርጋው በፎቶ መልክ አያይዞ ያቀረበው የቢቢሲ ማብራሪያ «የት ነው የሚነገሩት? የአፍሪቃ ቋንቋዎች» በሚል ርእስ ስር ነው የሚጀምረው። የቢቢሲ ዝርዝር አፋን ኦሮሞ በማለት ይጀምራል። በስፋት በኢትዮጵያ እንዲሁም በከፊል ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ግብጽ ውስጥ ይነገራል ይላል። አማርኛ ይልና ደግሞ፦ የኢትዮጵያ ሌላኛው ዋና ልሣን እንዲሁም የመንግስት እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይፋዊ ቋንቋ ሲል ይገልጠዋል። ትግሪኛን ሲያብራራ ደግሞ ከዓረቢኛ ጋር የኤርትራ ዋነኛ የሥራ ቋንቋ፤ በከፊል በኢትዮጵያም ይነገራል ሲል ገልጦታል።  
ገረሱ ቱፋ በፌስቡክ ገጹ፦ «በስተመጨረሻ ቢቢሲ በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ እንዲሁም በትግሪኛ ሊያሰራጭ ነው» ሲል አስነብቧል።

BBC Logo


ብርሃነመስቀል አበበ ሰጊ  ዘለግ ባለው የፌስቡክ የእንግሊዝኛ ጽሑፉ የሚከተለውን አስፍሯል። «ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ መርሐግብር አሁን ዕውን ነው!  ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ራዲዮ መርሐግብር ለመጀመር መወሰኑን በመስማቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። አፋን ኦሮሞ ራዲዮ መርሐግብር ለመጀመር በመወሰናችሁ በአፋን ኦሮሞ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ስም ከልብ የመነጨ «ምስጋናችንን» ለቢቢሲ ትረስት፣ ለቢቢሲ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ፣ እና ለቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ለብሪታንያ መንግሥት ቢቢሲ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ» በማለት ዝርዝር ጽሑፉ ይዘልቃል። የአፋን ኦሮሞ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ 10 አባላትን ዝርዝር በማስፈርም  «ኢትዮጵያ የሚገኙ የኮሚቴው አባላትን ስም ለደኅንነታቸው ሲባል አልገለጥኩም» ይላል። 
 
ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ  በፌስ ቡክ ገጹ ቀጣዩን ጽሁፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍሯል። «ኢትዮጵያን በተመለከተ ከቢቢሲ ስህተቶች አናዳጅ ኾኖ ያገኘሁት አማርኛ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋንቋ እንደሆነ እንዲሁም አፋን ኦሮሞ በግብጽ የሚነገር ነው ማለቱ  ላይ ያለው ኅጸጽ አይደለም። እንዲህ አይነት ስህተት ሊከሰትም ሊስተካከልም ይችላል።  ውድ ቢቢሲ  ለግልጽነት ሲባል ይኽ ስህተት እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ትነግሩን?  መነሻ ምንጫችሁ ምን እና ማን ነበር?ምንጫችሁ አላዋቂ አለያም የፖለቲካ አራማጅ ቢሆንስ? እናስ እንዲህ ያለ ምንጭ አዲስ በሚከፈቱት አገልግሎቶች ሁለቱ ቋንቋዎች ትስስር ላይ ተጽዕኖው እንዴት ያለ ነው?» የሚል ጥያቄ አኑሯል። መስፍን ጽሑፉን ባሰፈረበት ወቅት ቢቢሲ ቀደም ሲል ቅሬታ የቀረበበትን ጽሑፍ ማስተካከሉንም ጠቁሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ