1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት የማሕበራዊ ድረ-ገፆችን እንዴት ይጠቀማሉ?

ዓርብ፣ ኅዳር 30 2009

በዚህ ሳምንት የብሔር ብሔረሰቦች በዓል፤የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት እንደገና መጀመር እና የዶ/ር መረራ ጉዲና እስር በማሕበራዊ ድረ-ገፆች አነጋጋሪ ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት የማሕበራዊ ድረ-ገፆችን እንዴት ይጠቀማሉ?

https://p.dw.com/p/2U2QR
Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኦሮሞ ማሕበረሰብ የሚከተለዉ የገዳ ባሕላዊ የአስተዳደር እና የሥልጣን ሽግግር ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት (UNESCO) የማይዳደስስ ቅርስነት ተመዝግቧል።

ሐይለሚካኤል ለማ በፌስቡክ ገጹ «የገዳ ሥርዓት እንደሥርዓት እውቅናና ጥበቃ የሚገባው ሀብታችን ነው:: በዓለም ደረጃ ተገቢውን እውቅናና ክብር ያገኘ መሆኑ የሚያኮራ ነው!» ሲል ፅፏል።

ሑንዴ ዱጋሳ  «የገዳ ሥርዓት አገር በቀል አፍሪቃዊ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። ሥርዓቱን ላጠኑ፤ለሰነዱ እና ላስተዋወቁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ እና የምርምር ባልደረቦቻቸው በዚህ ሰዓት ይታሰቡኛል።» ሲል ኃሳቡን አስፍሯል።

ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ የገዳ የአሥተዳደር ሥርዓትን አጥንተው በመሰነድ እና ለሕዝብ በማቅረብ ላቅ ያለሚና መጫወታቸውን የፖለቲካ አቀንቃኙ ገረሱ ቱፋ በፌስ ቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፁ አስፍሯል። ገረሱ የፕሮፌሰሩ መጽሀፍ ተጨማሪ መረጃዎች ተካተውበው በቅርቡ በድጋሚ ለገበያ እንደሚቀርብም ፅፏል። በሰሜን አሜሪካ እና አውሮጳ ጉዞዎች እና ሕዝባዊ ውይይቶች እንደሚኖሩም ጠቁሟል። ይኽ የተሰማው እንግዲህ የገዳ ባሕላዊ የአስተዳደር ሥርዓት በዪኔስኮ በተመዘገበ ማግሥት ነው።

ግርማ ጉተማ በበኩሉ በዚያው በፌስ ቡክ «ዛሬ ላይ ሆነን የኦሮሞ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሳይሆንም እንኳ የገዳን በዩኔስኮ እንደ ታላቅ የሰው ልጆች ቅርስ ሆኖ መመዝገብ በደስታ የምናከብረው በዚህ ምክኒያት ነው። ገዳ የኦሮሞ የወደፊቱ ህልውና መሰረት ነው።» ሲል ኃሳቡን አስፍሯል።

ሙሉውን መሰናዶ ለማድመጥ ማዕቀፉን ይጫኑ