1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማንዴላ ጤናና አስተዋፅኦ

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2005

የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት እና የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ሃኪም ቤት ከገቡ አምስተኛ ቀናቸዉን ይዘዋል። የሕመማቸዉ ይዞታ ቀደም ሲል ከነበረዉ ጠንከር ማለቱ ቢነገርም እስካሁን በተረጋጋ ሁኔታ እንደሚገኙ የደቡብ አፍሪቃ ባለስልጣናት እየገለፁ ነዉ።

https://p.dw.com/p/18oVd
ምስል Getty Images

ልክ የዛሬ 49 ዓመት ነበር ኔልሰን ማንዴላ አገሪቱን በሚመራዉ የጥቂት ነጭ ዘረኛ አገዛዝ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸዉ። ዛሬ ደግሞ ሄድ መለስ እያለ ሲታገላቸዉ በቆየዉ የሳንባ ሕመም ምክንያት ሃኪም ቤት ከገቡ አምስት ቀናት ተቆጠሩ። ያኔ 27ዓመታትን በሮቢን ደሴት በእስራት ሲያሳልፉ ለ13ዓመታት በሃ ድንጋይ ሲጠርቡ መቆየታቸዉ ሳንባቸዉን እንደጎዳ ተገልጿል። ከዚያ ወዲህ ደግሞ ለቲቢ ተጋልጠዋል። እናም የህክምና ባለሙያዎች የቀድሞዉ ጉዳት የነፃነት ትግል አርማ የሆኑትን የ94ዓመቱ አዛዉንት አሁን በተደጋጋሚ ለሚያጠቃቸዉ የሳንባ ችግር እንዳጋለጠ ያምናሉ።

Südafrika Nelson Mandela Genesungswünsche Gebet
ለማንዴላ ጤንነት ጸሎትምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images

ላለፉት ቀናት ያሉበት ሁኔታ ያሰጋቸዉ ባለስልጣናት በበኩላቸዉ ሕዝቡን በመንፈስ ያስተሳሰሩት የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ማንዴላ ተገቢዉን ህክምና እንዲያገኙ እየጣሩ እንደሆነ ገልጸዋል። የፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ ቃል አቀባይ ቱሶ ኩማሎ።

«ፕሬዝደንት ዙማ ፕሬዝደንት ማንዴላ በተቻለ ምርጥ ክብካቤ እየተደረገላቸዉ እንደሆነ በተሰጣቸዉ መግለጫ ረክተዋል። ዶክተሮችም እንዲሁ እንዲሻላቸዉ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነዉ።»

ዛሬ ደግሞ ፕሬዝደንት ዙማ ማንዴላ በሚሰጣቸዉ መድሃኒት ቀና ለዉጥ እያሳዩ እንደሆነ ለምክር ቤታቸዉ ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ማንዴላ አገግመዉ ከሃኪም ቤት የመዉጣታቸዉን ነገር የሚጠራጠሩ አሉ፤ ብዙዎች ግን ለምህረት እየጸለዩላቸዉ ነዉ። በስዋኔ ቴክኒዎሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ፕሮፌሰርና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ የማንዴላ የአሁን ይዞታ የብዙዎችን ስሜት የነካዉ ፖለቲከኛ ሆነዉም ለይቅርባይነት ያሳዩት ፈቃደኝነት ነዉ ይላሉ፤ 

Südafrika Nelson Mandela Genesungswünsche
ምስል picture alliance/AP Photo

ኔልሰን ማንዴላ የANC ዋና ገልጽ መሆናቸዉ ይታወቃል። ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች በሕዝቡ ዘንድ ያላቸዉ ተቀባይነት እየቀነሰ መሄዱ ነዉ የሚነገረዉ። ለሕዝቡ የገቡትን ቃል አልፈፀሙም ሙስናም ተስፋፍቷል በሚል ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ አልተወጡም ተብለዉም ይወቀሳሉ። እንዲህ ባለዉ አመራርም ማንዴላ ለደቡብ አፍሪቃ ያለሙት ራዕይ ከግብ መድረሱ የሚያጠራጥራቸዉ አሉ። ANC አነሳሱ ኩራት፤ ነፃነት በራስ መተማመንና የሚመጣ ኃይልን መቃወም የሚሉትን ተንተርሶ ኢትዮጵያኒዝም በተሰኘ ፍልስፍና መሠረትነት መሆኑን የሚያመለክቱት ፕሮፌሰር ማሞ ግን በዚህ አይስማሙም፤

ከቅዳሜ አንስቶ ሃኪም ቤት የሚገኙትን የአፍሪቃ ጸረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን የቀድሞ ባለቤቶቻቸዉን ጨምሮ ቤተሰቦች እየጎበኙ ነዉ። ፕሬዝደንት ዙማ ደግሞ መርሃግብራቸዉ በፈቀደ ሰዓት ሊያይዋቸዉ እንደሚችሉ ቃል አቀባያቸዉ አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ