1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማይነገርላቸው የስደተኛ መጠለያዎች-በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ኅዳር 3 2008

የአውሮጳ አገራት በወቅታዊው የስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ቀውስ አብዝተው ሲያማረሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለአመታት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል።

https://p.dw.com/p/1H5N1
Symbolbild Flüchtlingskatastrophe Mittelmeer
ምስል imago/Anan Sesa

[No title]

«ቤተሰቦቼን ከአንድ አመት በላይ አላየኋቸውም።» ይላል በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት ግቢ ውስጥ የሚገኘው ጄምስ። «የተገደሉ መስሎኝ ነበር። እነሱ ወደ ኬንያ ሲሸሹ ነበር እኔ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። ከዚያ እዚህ ተገናኘን። አሁን አስፈላጊውን ምዝገባ እያደረኩላቸው ነው።» ባለቤቱና ቤተሰቦቹ በህይወት መኖራቸውን ባወቀበት ቅጽበት የተሰማውን ሲጠየቅ የጎሳውን ባህል ከሚያሳዩት የግንባሩ ትልትሎች ስር የሚገኙ አይኖቹ በሰፊው ተከፍተው ሃሳቡን ለመሰብሰብ ወደ ውጪ መተንፈስ ጀመረ።
«የተሰማኝን እፎይታ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል።» ይላል ጄምስ።
20ኛ አመቱን ያስቆጠረው የኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት ግቢ የአፍሪቃውያን መሰብሰቢያ ይመስላል። የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ዜጎች ሁሉ ይገኙበታል። ቅጥር ግቢው የደቡብ ሱዳን፤ ኮንጎ፤ ዩጋንዳ፤ ሶማሊያ፤ ኤርትራ፤የመን፤ ቡሩንዲና ሌሎች ሃገራት ስደተኞችን ያስተናግዳል።
በኢትዮጵያ 680, 000 ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ማዕከሉ እስከ ጥር ወር ድረስ ለ1,7000 ሰዎች ድጋፍ የማቅረብ እቅድ አለው።
በተ.መ.ድ. የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ዘገባ እንደሚያትተው በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ከዓለም ስደተኞች 86% ያስተናግዳሉ። የራሳቸውን ዜጎች ፍላጎት ለማሟት ትግል ላይ የሚገኙት አገራት ታዲያ ለስደተኞቹ የትምህርት፤ ስራና ያለ ገደብ የመንቀሳቀስ መብት ለመፍቀድ ቸልተኞች ናቸው።
«ይህ የትምህርት፤ማህበረሰባዊና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የምናቀርብበት የመቀበያ ማዕከል ነው።» ሲሉ ይናገራሉ የእየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት ኃላፊዋ ሐና ጴጥሮስ። «እዚህ በፖለቲካዊ አመለካከታቸውና ሐይማኖታቸው የጥቃት ሰለባ የሆኑና የተሻለ ገቢ ፍለጋ አገራቸውን ጥለው የሸሹ ስደተኞች ይገኛሉ።» የሚሉት ኃላፊዋ በማዕከሉ ሁሉም አይነት ስደተኞች እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ለአስራ አንድ አመታት የኖረው የ35 አመቱ ጊኒያዊ ጉይላይን ከሌሎች የአገሩ ሰዎች ጋር በመሆን ሰባት አባላት ያሉት የሙዚቃ ቡድን አቋቁሟል። የሙዚቃ ቡድኑ በማዕከሉ ውስጥ በምትገኝ አነስተኛ ክፍል ልምምድ ያደርጋል። ከሁለት አመት በፊት ባለቤቱና ልጁ ወደ አሜሪካ መጓዝ የቻሉ ሲሆን እሱም አንድ ቀን እንደሚቀላቀላቸው ተስፋ ያደርጋል።
«በጣም ቢናፍቁኝም ቆፍጣና መሆን ይኖርብኛል። አብዝቼ ማሰብ አይኖርብኝም።» ሲል ይናገራል -ጉይላይን። «ሙዚቃ ተስፋ ይሰጠኛል። ወደ ልምምድ ክፍሉ ስመጣ ደስተኛ እሆናለሁ። ሰዎች ደስተኛ እየሆኑ ነው። ይህ እንድትረሳ ይረዳሃል።»
የኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች አስተዳደርና በተ.መ.ድ. የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የሰላ ትችት ሲቀርብባቸው ይደመጣል።«የሚጨነቁት ስለ ስደተኞች ሳይሆን ስለበጀታቸው ነው።» የሚለው ኮንጓዊ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደው በአናሳው የባንያሙልንጌ ጎሳ ላይ የሚደርስበትን ጭቆና እና ጦርነት ሽሽት ነበር። «መስራት ባለመቻላችን እንደ ስነ-ልቦናዊ ግድያ ማለት ነው።» ሲል ይጨምራል። «ተስፋ ቢሶች ነን።»

Flüchtlinge im Südsudan
ምስል AFP/Getty Images/C. Lomodong
Äthiopien Flüchtlinge aus Südsudan
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker


የማይዋደዱት ጎረቤታሞች

ኢትዮጵያ ለስደተኞች መጠለያ በመስጠቷ ያገኘችው አድናቆት አናሳ ነው። በዚያ ላይ ከ1990-1992 ዓ.ም. የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ጠባሳ የፈጠረው መቃቃር መፍትሄ አላገኘም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል በሺዎች የሚቆጠሩት ኤርትራውያን ናቸው።
በኤርትራና ሱዳን ድንበር አቅራቢያ የሚገኙት የማይ ዓይኒ፤ አዲ ሐሩሽ እና ሂጻጺ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ኤርትራውያኑ ካሩፉባቸው መካከል ይገኙበታል። ጥቂቶቹ የኤርትራ ስደተኞች አዲስ አበባ መድረስ ችለዋል።
«ቢያንስ እምነቴን በነጻነት ለመከተል ነጻ ነኝ።» የምትለው የ30 አመቷ ሳምራዊት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ስትሆን በኢየሱሳውያን የስደተኞች አገልግሎት ግቢ ለስደተኞች የእንግሊዘኛ ቋንቋ ታስተምራለች። «ለኑሮ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ስለማልችል ግን ይህ ነጻነት ትርጉም የለውም።» ስትል ሳምራዊት ታማርራለች።
ከሰባት አመታት በፊት ሳምራዊት በምሽት የእግር ጉዞ የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አቋረጠች። በእንግሊዘኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ በጋዜጠኝነት እና የድረ-ገጽ ንድፍ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የተከታተለችው ሳምራዊት አሁን የምትገኝበት ማዕከል ትምህርቷን ተግባር ላይ እንድታውል አግዟታል። በስራዋ በምታገኘው ገቢ ራሷንና የስድስት አመት ሴት ልጇን መደጎም የቻለች ሲሆን ባለቤቷን ግን ላለፉት ስድስት አመታት አይታው አታውቅም።
ሌላዋ ወጣት ኤርትራዊት በምሽት ከትውልድ አገሯ ወደ ኢትዮጵያ በአጎቷ እርዳታ ስታቋርጥ አስፈሪ ድምጾች እየሰማች ነበር። የሰማችው ድምጽ ተኩሰው የመግደል ትዕዛዝ የተሰጣቸው የኤርትራ ድንበር ተቆጣጣሪ ወታደሮች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ምህረት ትናገራለች። የህክምና ዶክተሯ ምህረት የኤርትራ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ተስፋቢስ አድርጓታል። በአዲስ አበባ ሁለት አመታት ከቆየች በኋላ ህጋዊ ፈቃድ አግኝታ ወደ አውሮጳ አምርታለች።
ሌሎች ግን እንዲህ እድለኛ አይደሉም። እናም በየዓመቱ በወርሃ የካቲት በሱዳን አድርገው ወደ አውሮጳ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ ይነጉዳሉ። ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በመነሳት ወደ ሊቢያ ለማምራት መጋቢት ሁነኛው ወቅት እንደሆነ በስደተኞቹ ዘንድ ይታመናል። ከክረምቱ ይልቅ በሚያዝያ ደግሞ የሰሐራ በርሃ ቀዝቀዝ፤ የሜድትራኒያን ውሃም ረገብ ይላል።
«ለወጣቶች የራሳቸውን ስራ ለመስራት ምንም አይነት እድል የለም። ለቤተሰቦች ምንም ማድረግ አይቻልም። ሁሉም ነገር አገር ጥለህ እንድትጠፋ ይገፋሃል።» ይላል የ31 አመቱ ሸዊት። ሸዊት ከኤርትራ የወጣው ከአራት አመታት በፊት ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ከመዛወሩ በፊት በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቆይቷል። «ምንም ሰው ለፍትህ ሊታገል አይችልም። ከመጀመርህ በፊት ያስሩሃል። እንዲህ አይነት ጥረቶች ለምንም ነገር ጥሩ አይደሉም።» የኤርትራ መንግስት ሰፊ የስለላ መረብ ዘርግቷል። ሸዊት ለኤርትራ መንግስት አድረው በስለላ መዋቅሩ ለሚሳተፉ የሚራራ ልብ የለውም። ቢሆንም ምክንያታቸውን ይረዳል። «ሁኔታው የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። ቤተሰቦቻቸውን የመመገብ ጥያቄ። ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሰላይ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል።» ሲል በኤርትራ ያለውን ሁኔታ ያስረዳል።

ሸዊትና የ29 አመቱ ጓደኛው ቢያኒያም ከሊቢያ የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ የሞከሩ ኤርትራዊ ጓደኞች አሏቸው። እንደ መታደል ሆኖ የሚያውቁት ሰው አልሞተም። እንደ እርዳታ ድርጅቶች ከሆነ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. በሜድትራኒያን የመስጠም አደጋ ከገጠማቸው 3,000 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኤርትራውያን ናቸው።
የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ በመጠባበቅ ላይ የነበረ የ20 አመት ዘመዱ ሊቢያ ውስጥ መሞቱን ሸዊት ተናግሯል። ምክንያቱን ግን አያውቀውም። ቢኒያምም ወደ ሊቢያ በሚደረገው ጉዞ የታገቱና ገንዘብ የተጠየቁ ዘመዶች አሉኝ ብሏል። ዘመዶቹ ከአጋቾቻቸው የተለቀቁት የተጠየቁት ከተከፈለ በኋላ ነበር። ከሁለት አንዳቸው ከአፍሪቃ ለመውጣት አስጊውን የእግርና የባህር ጉዞ የማድረግ እቅድ ይኖራቸው ይሆን?
«አዎ አስቤበታለሁ።» ይላል ። «እዚህ አራት አመታት ቆይቻለሁ። ከዚህ በላይ ከቆየሁ ወደ ፊት ምን እሆናለሁ?»-ሸዊት

ጄምስ ጄፍሪ/እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Konflikt im Südsudan Flüchtlinge 17.01.2014
ምስል Phil Moore/AFP/Getty Images