1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማ/አፍሪቃ ሬፓብሊክና የመ/መንግሥቱ መንሥዔ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 21 2005

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በአልማዝ፡ ወርቅ እና በማዕድኑ ዩሬንየም የታደለችው እና ለገብስ፡ ማኞክ እና ትምባሆ ምርት ተስማሚ የሆነ አየር ፀባይ ያላት ሀገር ናት። ይሁንና፣ በሀገርዋ በጎደለው አለመረጋጋት የተነሳ ሕዝቧ የዚሁ ተፈጥሮአዊ ስጦታ ተጠቃሚ አልሆነም።

https://p.dw.com/p/186ys
ምስል AFP/Getty Images

በተመድ መዘርዝሮች መሠረት፡ ከ 4.5 ሚልዮን ሕዝቧ መካከል ከ 80,000 የሚበልጠው ዘንድሮ የምግብ እጥረት እንደሚያሰጋውና ወደ 13,500 የሚጠጉ ዕድሜአቸው ከአምሥት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትም አሳሳቢ ያልተመጣጠነ አመጋገብ ችግር እንደሚገጥማቸው ተገልጾዋል። ይህችው ሀገር እአአ በ 1960 ዓም ከፈረንሣይ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ከተላቀቀች ወዲህ በተደጋጋሚ የፖለቲካ ቀውስ ገጥሟታል። በሀገሪቱ ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋ ሲነፃፀር የጦር ኃይሉ ያካሄዳቸው ዓማፆች እና ያደረጋቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች በቁጥር ይበልጣሉ። ባለፈው የሣምንት መጨረሻም በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አምሥት ያማፅያን ቡድኖች ጥምረት የሆነው በሚሼል ጆቶጂያ የተመራው የሴሌካ ዓማፅያን ጥምረት በፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ መንግሥት አንፃር ባካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ርዕሰ ከተማይቱን ባንግዊ ተቆጣጥሮዋል። መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ፕሬዚደንቱ ወደ ካሜሩን፡ ዘመዶች እና ታማኝ ባለሥልጣናት ደግሞ ወደ ጎረቤት ኮንጎ ከሸሹ በኋላ በከተማይቱ ሥርዓተ አልባነት እና ዝርፊያ በመስፋፋቱ፣ በወቅቱ የሴሌካ እና የፈረንሣይ ወታደሮች የፀጥታውን ሁኔታ ለማረጋጋት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዚችው ሀገር ብዙም የማይነሳው እና የፀጥታ ችግር የሌለበት ከቻድ እና ከሱዳን ጋ የሚጎራበተው ሰሜን ምሥራቃዊ አካባቢ ቢሆንም፣ የሀገሪቱ ማዕከላይ መንግሥት ለዚሁ አካባቢ ልማት እና በዚያ ለሚኖረው ሕዝብ አስፈላጊው ትኩረት ያልሰጠበት ድርጊት የሴሌካ ዓማፅያን በመንግሥቱ አንፃር እንዲነሱ እንዳደረጋቸው የጥምረቱ መሪ ጆቶጂያ ገልጸዋል። እንደሚታወሰው፡ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መንግሥት አንፃር የተዋጉት ከሰሜን ምሥራቃዊው የሀገሪቱ ከፊል የተንቀሳቀሱት ዓማፅያን ባለፈው ታህሳስ ወር ያካሄዱት ዓመፅ ያበቃው በጋቦን ሸምጋይነት በመዲናይቱ ሊብረቪል ባለፈው ጥር ወር ከመንግሥቱ ጋ የስልጣን መጋራት ውል ከተፈራረሙ በኋላ ነበር።  በዚሁ ውል መሠረት፡ ከዓማፅያኑ፡ ከሲቪል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች እና የፕሬዚደንት ቦዚዜ ታማኞች የተውጣጣ በጠቅላይ ሚንስትር ኒኮላ ቲያንጋይ የሚመራ መንግሥት ተቋቁሞ ነበር። ይሁንና፡ ፕሬዚደንት ቦዚዜ ውሉን አላከበሩም ያሉት ዓማፅያን ትግላቸውን ቀጥለው አሁን መዲናይቱን መቆጣጠር ተሳክቶላቸዋል።
በባንግዊ የሚገኘው የቀድሞው ፕሬዚደንት ቦዚዜ መንግሥት ሰሜን ምሥራቃዊውን ከፊል የመሳሰለ ችላ የተባለ አካባቢ ውሎ አድሮ መሠረታዊ መብቱን ለማስከበር የኃይሉን ተግባር መጀመሩ እንደማይቀር አስቀድሞ መገንዘብ ነበረበት።  መብታቸው ባልተከበረላቸው ሰሜን ምሥራቃዊው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዓመፅ በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል በማዕከላይ አፍሪቃዊቱ ሬፓብሊክ በ 2011 ዓም ፕሬዚደንታዊው ምርጫ በተደረገበት ጊዜ አንዳንድ ታዛቢዎች አስጠንቅቀው ነበር። በሰሜን ምሥራቃዊ ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የሚገኘው የአንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ንቅናቄ ፕሬዚደንት አዶልፍ ንጉዮምቦ እንዳስረዱት፡ ይኸው አካባባ ከልማቱ ሂደት ለተገለለበትና የማዕከላዩን መንግሥት ትኩረት ላላገኘበት ሁኔታ  ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።
« ይኸው ታሪክ ከነፃነት ጀምሮ የቀጠለ ነው። ተፈጥሮአዊ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ። በመጀመሪያ እጅግ በጣም ሩቅ ሲሆን፡ በ2ኛ ደረጃ በዝናቡ ወራት በፍፁም ሊደረስበት የማይቻል አካባቢ ነው። »
ከዚህ በተጨማሪም ብዙም መረጋጋት ከማይታይባቸው ቻድ፡ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ሀገራት መጎራበቱም ሁኔታዎችን ምቹ አላደረገም። ሕገ ወጡ ንግድ የተስፋፋበት ፡ በተለይም፡ በብዛት የጦር መሣሪያ በኮንትሮባንድ የሚዘዋወርበት አካባቢ ነው። በብሔራዊ ደረጃ ሲመለከቱት፡ የሰሜን ምሥራቃዊ አካባቢ ሕዝብ በመንግሥት አስተዳደር፡ በፖለቲካው ዘርፍ ያለው ውክልና በጣም ንዑስ ሲሆን፣ የትምህርቱ እና የጤና ጥበቃውም ዘርፍ እጅግ ኋላ ቀር ነው። በዚሁ አካባቢ በትምህርቱ ዘርፍ ለሚታየው ንዑሱ እንቅስቃሴ በዚያ የተሠማሩት የውጭ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የሚያደርጉት ርዳታ ድርሻ አበርክቶዋል።
በዚሁ ድንበር አካባቢ ከሚገኙት ቻድ፡ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ጋ ባለው ግንኙነት የተነሳ በሕዝቦች መካከል የባህሉ ልውውጥም ተስፋፍቶዋል። ሀይማኖትም የራሱን ሚና ይጫወታል። ይኸው ሁኔታ አሁን በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን አመራር በያዘው በዓማፅያኑ የሴሌካ ጥምረት አመሠራረት ላይ እንደተንፀባረቀ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ንቅናቄ ፕሬዚደንት አዶልፍ ንጉዮምቦ ገልጸዋል።
« በድንበሩ አካባቢ ሕዝቡ ሁለት ቋንቋዎች ይናገራል። በዚሁ አካባቢ ሳንጎ የተባለው ጠቅላላ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሕዝብ የሚጠቀምበት ብሔራዊ ቋንቋ  ብቻ አይደለም የሚነገረው። ሕዝቡ በተጨማሪ ዐረብኛንም እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ይናገራል።  በሚመራው የሴሌካ ቡድን የሚጠቃለሉት ዓማፅያን የተውጣጡት ከዚህ እና ከዚያ ብሎ መናገሩ በአሁኑ ጊዜ አዳጋች ቢሆንም፡ ያካሄድኩት ጥናት ያሳየው ብዙዎቹ የእሥልምና እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ነው። ራሳቸውን አዲሱ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ብለው የሠየሙት ሚሼል ጆቶጂያ ቢራዎ ከተባለው የሰሜን ምራቅ አካባቢ ሲሆኑ፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ግን በመሀል ሀገር ባለው ጉዋም በተባለው አካባቢ ከምትገኘው የቦካ ከተማ ነው። »
ጆቶጂያ ጠቅላይ ሚንስትር ኒኮላ ቲያንጋዬ ይህንኑ ሥልጣናቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ የወሰኑት ቲያንጋይ ትልቅ ተፅኖ ካሳረፈ የሀገሪቱ አካባቢ ባለመምጣታቸው  እና በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ለማስከበር ባደረጉት ጥረት መልካም ስም በማትረፋቸው ሳይሆን እንዳልቀረ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ንቅናቄ ፕሬዚደንት አዶልፍ ንጉዮምቦ ይገምታሉ።

Michel Djotodia
ምስል Getty Images
Abkommen zwischen ZAR-Rebellen und Regierung in Gabun
ምስል dapd
Rebellen Damara Zentralafrikanische Republik Januar 2013
ምስል AFP/Getty Images

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ