1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  የሜርክል ጉብኝት በሰሜን አፍሪቃ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ የካቲት 23 2009

የጄኔራል አልሲሲ መንግሥት አሸባሪነትን መዋጋት በሚል ሰበብ ተቃዋሚዎቹን ይገድላል።ያስራል።የኮፕቲክ ክርስቲያኖች መብት ተገድቧል።የአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ ጀርመን  የአካባቢዉን  ፀጥታን ለማስከበር በሚል ከግብፅ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት፤ ፓዉል እንደሚሉት፤ ለግብፅም ሆነ ለአካባቢዉ አስተማማኝ ሠላማ አያሰፍንም። 

https://p.dw.com/p/2YWO1
China G20 Gipfel in Hangzhou - Merkel & al-Sisi
ምስል picture-alliance/dpa/B.v. Jutrczenka

NM RAW - MP3-Stereo

የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግብፅንና ቱኒዚያን ለሁለት ቀናት ለመጎብኘት ዛሬ ወደ ካይሮ ሔደዋል።ሜርክል ከሑለቱ ሐገራት መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ዉይይት ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይገቡ ለማገድ የስደተኞች ማከማቻ ሰፈር ለማቋቋም የሚረዳ ስምምነት ለመፈራረም አቅደዋል ተብሎ ይጠበቃል።ሜርክል ዛሬና ነገ ከሰሜን አፍሪቃ መንግሥታት ጋር ያደርጉታል የተባለዉ ሥምምነት በዉል ባይታወቅም፤ ካሁኑ እየተተቸ ነዉ።ሽቴፋኒ ሆፕነር የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የጉዟቸዉ ዓላማ ሊቢያን ማረጋጋት፤ ቱኒዚያን ማጠናከር፤ የንግድና ምጣኔ ሐብት ግንኙነት- - - እያለ ሲዘረዘር ብዙ፤ «ሥደተኞች አዉሮጳ እንዳገቡ ማገድ» ተብሎ ሲጠቃለል ግን አንድ ነዉ።ብዙም-አንድም።ዛሬ ከግብፁ መሪ አብዱልፈታሕ አል ሲሲ ጋር ሲነጋገሩ ሊቢያ የምትረጋጋባትን ሥልት ያስቀድማሉ-ነዉ የተባለዉ።
በየዕለቱ በሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች የሜድትራኒያን ባሕር ተሻግረዉ አዉሮጳ የሚገቡት ወይም ለመሻገር ሲሞክሩ ባሕር ዉስጥ የሚሰምጡት ከሊቢያ እየተሳፈሩ ነዉ።ሊቢያ ጠንካራ መንግስት ከሌላት ስደተኞችንና አሸጋጋሪዎችን መቆጣጠር አይቻልም።
 ጀርመን ዉስጥ ደግሞ በመጪዉ መስከረም  ምርጫ አለ።ከጀርመን በፊት ፈረንሳዮች እና ሆላንዶች ይመርጣሉ።ፀረ ስደተኛና ፀረ-አዉሮጳ ሕብረት አቋም ያላቸዉ ቀኝ ፅንፈኞቹ ፖለቲከኞች ማሪን ለ ፔን ፈረንሳይ፤ጌርት ቪልደርስ ሆላንድ ላይ ሳይቀድሟቸዉ ለመቅደም ሜርክልና ብጤዎቻቸዉ መጣደፍ አለባቸዉ።
                     
«የጀርመን መንግስት እና የአዉሮጳ ሕብረት፤ መስከረም ከሚደረገዉ የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ በፊት እንዲሁም ፈረንሳይና ኔዘርላንድስ ዉስጥ ከሚደረጉት ምርጫዎች በፊት ለስደተኞች ጉዳይ ሁነኛ መፍትሔ ለማግኘት እየሞከሩ ነዉ።»
ይላሉ በቱኒዚያ የሐይንሪሽ ቦል ጥናት ተቋም ኃላፊ ዮአኺም ፓዉል።«ከሁነኛዉ መፍትሔ» አንዱ ወደ አዉሮጳ ለመግባት የሚፈልጉ ስደተኞች የሚከማቹበት ሰፈር ሰሜን አፍሪቃ ምናልባትም ግብፅ ላይ ማቆም ነዉ።«ግብፅ የተመሰቃቀለዉን አካባቢ ለማረጋጋት ጠቃሚ ናት» ብለዉ ነበር ሜርክል በቅርቡ።ሜርክል ከ«ተረጋጋችዉ» ሐገር የ«ተረጋጉ» ጄኔራል መሪ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት የስደተኞች ማከማቺያ ጣቢያ ለመመስረት ሳይስማሙ አይቀርም ተብሎ ተገምቷል።የመብት ተሟጋቾች ግን ሜርክል ለአልሲሲ ያላቸዉን ግምት፤ ዓላማንም አይቀበሉትም።የአልሲሲ መንግስት ለመብት ተቆርቋሪዎች በግብፅ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አቻ የማይገኝለት ሰብአዊ መብት ረጋጭ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ዮአኺም ፓዉልም የመብት ተሟጋቾቹን አስተያየት ይጋራሉ።
                                    
«በግብፅ ዘመናይ ታሪክ አቻ የማይገኝለት የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚፈፅም መንግሥት በምትገዛ ሐገር ፤ ሁዩማን ራትስ ዋች እንደገለፀዉ፤ እንዲሕ ዓይነት የስደተኞች ማከማቻ ሠፈር ለማቋቋም መሞከርን ለመቀበል ያዳግታል።በግብፅ በኩል ሐሳቡ ተቀባይነት ማግኘቱን እጠራጠራለሁ።ከሆነ ግን ዝቅተኛዉ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እንኳን አይኖርም ማለት ነዉ።»
የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ጄኔራል አልሲሲ መንግሥት አሸባሪነትን መዋጋት በሚል ሰበብ ተቃዋሚዎቹን ይገድላል።ያስራል።የሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማትን ዘግቷል።የኮፕቲክ ክርስቲያኖች መብት ተገድቧል።የአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ ጀርመን  የአካባቢዉን  ፀጥታን ለማስከበር በሚል ከግብፅ መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያደርጉት ጥረት፤ ፓዉል እንደሚሉት፤ ለግብፅም ሆነ ለአካባቢዉ አስተማማኝ ሠላማ አያሰፍንም። 
                              
«ፀጥታን በተመለከተ የአዉሮጳ ሕብረትና ጀርመን ግብፅ ላይ ትልቅ ፍላጎት አላቸዉ።ይሕቺ ሐገር አለመረጋጋት በሚያዉከዉ አካባቢ መረጋጋት ታመጣለች ለማለት፤ ሶሪያ፤የመን እና ሊቢያን ማየት በቂ ነዉ።ተመሳሳይ ነገር ቢደርስ ግብፅ ዉስጥ ሊፈጠር የሚችለዉን መገመት አያዳግትም።ይሕ ስርዓት፤ በኚሕ ፕሬዝደንት የሚመራዉ መንግስት የምጣኔ ሐብትና የፀጥታ መረጋጋት ማስፈኑን እጠራጠራለሁ።»
ሁለተኛዋ ቱኒዚያ ናት።ቱኒዚያ በሕዝባዊ ዓመፅ የመንግስት ለዉጥ ከተደገባቸዉ ሐገራት ሁሉ የለዉጥ ፈላጊዉ ሕዝብ ፍላጎት ከሞላ ጎደል ገቢር የሆነባት ሐገር ናት።ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የምትፍጨረጨር ግን ብዙ ፈተናዎች ያሉባት ሐገር ናት።ሜርክል በጉብኝታቸዉ ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐገር የስደተኞች መከማቻ ሰፈር እንድትገነባ ለመጠየቅ-ማሰብ-አለማሰባቸዉ በዉል አይታወቅም።
የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዩሱፍ ቻሐድ ከሁለት ሳምንት በፊት ጀርመንን ሲጎበኙ እንዳሉት ግን ስደተኛ ማከማቻ ሰፈር ቱኒዚያ ዉስጥ ይገንባ የሚለዉን ሐሳብ አይቀበሉትም።የቱኒዚያና የጀርመን ማሕበረብ ፕሬዝደንት ረዑፍ ኻማሲም ቱኒዚያ ዉስጥ የስደተኛ ሰፈር ይገንባ ማለት ለቱኒዚያ ጅምር ዴሞክራሲ አደገኛ ነዉ።
ይሁንና በቅርቡ ቱኒዚያዊዉ ስደተኛ አኒስ አሚሩ በርሊን ዉስጥ በአስር የሚቆጠሩ ሰዎችን በጭነት መኪና ደልፍልቆ ከገደለ በኋላ ጀርመን ዉስጥ የስደተኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ ቱኒዚያዉያንን የቱኒስ መንግስት እንዲቀበል ከፍተኛ ግፊት እየተደረገበት ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትር ቻሐድ መንግስት ይሕን የማይቀበልበት ምክንያት የለም።«ይላሉ ፓዉል።

Tunesien Demonstration in Tunis
ምስል Reuters/Z. Souissi
Ägypten Migranten Polizeistation in Rosetta
ምስል picture-alliance/dpa/M. Elhorsy

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ