1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሜድትራኒያን የሞት መንጋጋ

ሰኞ፣ ነሐሴ 4 2007

የጣሊያን ባህር ሃይል ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ1,000 በላይ ሰዎችን ከሜድትራኒያን ባህር መታደጉን አስታወቀ። በዚህ አመት ከሶርያ፤አፍጋኒስታን እና ኢራቅ ወደ ግሪክ የተጓዙ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ቁጥርም በ750 በመቶ መጨመሩን የተ.መ. ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1GCvB
Griechenland Ankunft syrischer Flüchtlinge auf Kos
ምስል Reuters/Y. Behrakis

[No title]

ባለፈው ሳምንት ከሊቢያ በአሳ ማስገርሪያ ጀልባ ተሳፍረው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ በገጠማቸው አደጋ በሜድትራኒያን ባህር የጠፉት ከ200 በላይ ስደተኞች እጣ ፈንታ ዛሬም ድረስ አልታወቀም። የሜድትራኒያን ባህር የተሻለ የስራና የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ አሊያም ያገራቸውን ጦርነት እና የርስ በርስ ግጭት ሸሽተው አውሮጳ ለመድረስ ለሚያልሙ የአፍሪቃ፤መካከለኛው ምስራቅና የእስያ ሃገራት ዜጎች መቃብር መሆኑን ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት የደረሱበት ያልታወቀውን 200 ሰዎች ሳይጨምር በዚህ አመት ብቻ ከ2100 በላይ ሰዎች ወደ አውሮጳ በመጓዝ ላይ ሳሉ ህይወታቸው አጥተዋል።

ካለሙት አውሮጳ ለመድረስ ከሞት ጋር የሚጋፈጡት ሰዎች ቁጥር ግን አሁንም እየጨመረ ነው። ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ 1,000 በላይ ስደተኞች የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ በነፍስ አድን ሰራተኞች ከሞት መትረፋቸውን የጣልያን ባህር ኃይል አስታውቋል። ስደተኞቹ የተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ከአቅማቸው በላይ በመጫናቸው የከፋ አደጋ ሊከሰት ይችል ነበር ተብሏል። እናቶች እና አባቶች ከነልጆቻቸው ወደ ጣልያን የሬጂዮ ዲ ካላብሪያ ግዛት እየደረሱ ነው። ይህ ስደተኞቹን ለሚቀበሉት የቀይ መስቀል ሰራተኛ ሉቺያና ኩዞክሬያ ትልቅ እፎይታ ነው።

Griechenland Ankunft syrischer Flüchtlinge auf Kos
ምስል Reuters/Y. Behrakis

«ልጆቹ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በፈገግታ ነው ከመረከቡ የወረዱት። ቤተሰቦቻቸውም ደስተኞች ናቸው። በዚያ ስሆን የራሴን ልጆች አስባለሁ። በጤና ሲደርሱ ደስተኛ ነኝ። ዛሬ በሰራነው ስራ ደስተኛ ነኝ።»

ሉቺያና ኩዞክሬያ ከአፍሪቃ፤መካከለኛው ምስራቅና እስያ ወደ አውሮጳ የሚጎርፉትን ስደተኞች ሲቀበሉ በርካታ ነገሮችን ታዝበዋል። የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሜድትራኒያንን ሞት የሚጋፈጡት ስደተኞች ሁኔታ ግን ለእሳቸው ሁልጊዜም አዲስ ነው።

«የእነሱን መምጣት ለምጀዋለሁ። ከመጡ በኋላ የምናየውን ግን አልለመድኩትም። ያለፉበትን ሁኔታ ስንመለከት ልብ ይነካል። ምናልባት ሳምንታት ሙሉ የተጓዙትን ህጻናትን ፊት ስትመለከት፣ ይህ ዓይነቱን ሁኔታ አትለምደውም። የአንድ እናት፣ ልጇን የማጣት ፈተና ተጋርጦባት እዚህ ድረስ ተጉዛ የደረሰች ነፍሰጡር እናትን ስቃይ፣ በፍጹም አይለመድም።»

በዚህ አመት ብቻ 224,000 ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ መሻገራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ሳምንት አስታውቋል። ይህ ቁጥር ባለፈው አመት 219,000 ነበር።የአውሮጳ ህብረትና አባል አገራት ስደተኞቹን ለመታደግ የያሳዩት ተነሳሽነት አነስተኛ ነው እየተባሉ ይወቀሳሉ። የአውሮጳ ህብረት የስደተኞች፤ዜግነትና አገር ውስጥ ጉዳይ ኮሚሽነር ዲሚጥሪስ አቭራምፖሎስ አባል አገራቱ ችግሩን ለመፍታት በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ኮሚሽነሩ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ተገን ጠያቂዎች በህጋዊ መንገድ መቀበል የሚቻልበት ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ሰራተኛ የሆኑት ባርባራ ሞሊናሪዮም ይህን አሳብ ይጋራሉ።

Flüchtlinge im Mittelmeer (Symbolbild)
ምስል picture-alliance/dpa/Bundeswehr/Hptm Kleemann

«በሜድትራኒያን እየተፈጠረ ያለው የስደተኞች ቀውስ ነው። ትልቁ ቀውስ ግን ሰዎች እየሞቱ በዚህ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመምጣት መገደዳቸው ነው። አስፈላጊውና የተ.መ. የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እየጠየቀ ያለው ጉዳይ የአውሮጳ መንግሥታት ለእነዚህ ሰዎች ወደ ጀልባዎቹ እንዳይሳፈሩ የሚያደርጓቸው ህጋዊ አማራጮችእንዲያቀርቡ ነው። የሰብዓዊ እርዳታ የጉዞ ፈቃድ ወይም ብዙዎቹ ስደተኞች በአውሮጳ የሚኖሩ ዘመዶች ስላሏቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚቀላቀሉበትን ዓይነት ፈቃድ መስጠት ማለታችን ነው።»

አስቸኳይ የህክምና እርዳታ፤የመጠጥ ውሃና ምግብ የሚፈልጉ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎችም ወደ ግሪክ ትናንሽ ደሴቶች እየጎረፉ ነው። በዚህ አመት እስከ ሐምሌ ወር ብቻ 124,000 ሰዎች ወደ ከግሪክ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። ይህም ካለፈው አመት በ750 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ባለፈው ወር ብቻ ከግሪክ 50,000 ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ደረሰዋል ተብሏል። አብዛኞቹ የሶርያ፤አፍጋኒስታን እና ኢራቅ ስደተኞች ናቸው።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ