1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምሥራቁ መናፈቅ-መልሶ የማየት ጉጉት

ሐሙስ፣ መስከረም 20 2008

ጀርመንን ለሁለት የከፈለዉ የበርሊኒ ግንብ ከፈረሰና ጀርመን ከተዋሐደ በኋላ ምሥራቅ ጀርመን ዉስጥ የነበረዉን ሕይወት መናፈቅ እየጠነከረ መጥቶአል። በተለይ በምሥራቅ ጀርመን ይመረቱ የነበሩ መኪኖች፤ እንዲሁም ይዘወተሩ የነበሩት የምግብ ዓይነቶች የምሥራቅ ጀርመንን ትዝታ ዳግም እየቀሰቀሱ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1Gh7J
Deutschland Gedenkstätte Deutsche Teilung DDR-Uniformen
ምስል picture-alliance/dpa/P. Förster

[No title]

የዶቼ ቬለዉ ቮልፍጋንግ ዲክ ከዚህ ናፍቆትና ትዝታ ባሻገር ግን ስዉር የፖለቲካ መልክት ይኖር ይሆን? ሲል ይጠይቃል።
ዛሬ የምሥራቅ ጀርመንን ሕይወት በቅርበት ዉሎና አድሮ ለማስታወስ የሚያስችል አንድ ሆቴል ጀርመን መዲና በርሊን ላይ ማግኘት ይቻላል። ፍሪድሪሽሻይን በተባለዉ በበርሊን ክፍለ ከተማ የሚገኘዉ የዚህ ሆቴል ስም «ኦስቲል» ይሰኛል። የሆቴሉ መስራች ዳንኤል ሄልቢግ ልክ እንደ ቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ጊዜ እንደነበረዉ ምንጣፍና ሶፋ ሌሎችም ቁሳቁሶችን አድርገዉ ይህን ስድሳ ክፍሎችን የያዘ ሆቴል እስኪያቋቁሙና እስኪከፍቱ በጣም ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። እንድያም ሆኖ ዛሬ ሆቴሉና የማደርያ ክፍሎቹ ሁሌም ሙሉ በመሆናቸዉ የዚህ የንግድ ፅንሰ ኃሳብ መፍለቅና የሆቴሉ መከፈት ትልቅ ጥቅም ነዉ ያስገኘላቸዉ። የሆቴሉ ባለቤት ዳንኤል ሄልቢግ እንደሚሉት ሰዎች ወደ ሆቴሉ የሚመጡት በምስራቅ ጀርመን ምን ዓይነት ሕይወት እንደነበር ማየት መቅመስ፤ ብሎም ማስታወስ ስለሚፈልጉ ነዉ።

« ባለፉት ጊዜያት በጥቂቱም ቢሆን ኑሮ ረጋ ያለ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። እንደ አሁኑ ጊዜ ሰዉ ብዙ ነገሮችን ማየትና መስማት የለበትም ነበር ። ማለት ቀደም ሲል ኮንፒዩተር፤ ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ አልያም የፋክስ መላክያ የሚባል ነገር አልነበረም። ኑሮ ትንሽ ለቀቅ ያለ ነበር። ጊዜዉ የፍቅር ስለነበርም፤ በጥቂትም ቢሆን ሰዉ ያለፈዉን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብሎ ማየትን ይወዳል።»
የቀድሞዉን የምሥራቅ ጀርመን ሶሻሊስት መንግሥት 25 ዓመታት ሕይወት ከቀመሱት ወደ 16 ሚሊዮን ከሚጠጉት ነዋሪዎች መካከል ከ 10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት ማኅበረሰቦች አሁንም እንደድሮዉ የምሥራቅ ጀርመን ሕይወትን መኖር ይሻሉ። ይህን መረጃ ያረጋገጠዉ የጀርመን የምርምር ተቋም ባደረገዉ የጥያቄ መዘርዝር ነዉ። በመዘርዝሩም መሠረት አብዛኛዉ ነዋሪ ከምስራቅ ጀርመኑ ዓይነት ኑሮ ይልቅ ዛሬ ተዋሕዳ ባለችዉ ጀርመን በድሎትና በነጻነት መኖርን ይመርጣል።
ሲልከ ሩዲገር በኢንተርኔት አማካኝነት ባለዉ የፖስታ አገልግሎት የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ከፍተኛ ገበያን አግኝተዋል። እነዚህ የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን ጊዜ የነበሩ የምግብ ምርቶች በአሁኑ ጊዜ የሚመረቱት በጥቂት ፋብሪካዎች ዉስጥ ብቻ ነዉ። ለሽያጭ ከሚቀርቡት ቁሶች ዉስጥ ልብስ፤ ሙዚቃ፤ ፊልም ፤ የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን መገበያያ ገንዘብ እንዲሁም ሜዳልያዎች ሁሉ ይገኙበታል። ለምሳሌ 100 የምሥራቅ ጀርመን ማርክ በአሁኑ ጊዜ 25 ይሮ ይሸጣል። የምሥራቅ ጀርመን መንግስት መሪ ሄሪክ ሆኒከር ለታታሪ ሠራተኞች ይሸልሙት የነበረዉ ሜዳልያ አሁን ወደ 350 ይሮ ያወጣል። በኢንተርኔት መገበያያ መረብ ላይ በብዛት ገበያ ያላቸዉ ነገሮች ግን በምሥራቅ ጀርመን ጊዜ ይመረቱ የነበሩት ዓይነት የምግብ ሸቀጦች ናቸዉ። እንደ ሲልከ ሩዲገር ሰዎች ምሥራቅ ጀርመን ተነጥላ በቆየችበት ጊዜ የነበረ ነገርን በማግኘት የቀድሞዉን ሕይወታቸዉን መለስ ብለዉ ማስታወስ ይፈልጋሉ ።

« የሚፈልጉበት ምክንያት ጥሩ ምርት ስለሆነ እና ምዕራብ ጀርመን ዉስጥ የተወለዱ አብዛኞች ሰዎችም ምንነቱን ለማወቅ ስለሚፈልጉ ነዉ። ምንድነዉ? እስኪ ልሞክረዉ እያሉም ምርቶቹን ማግኘት፤ መሞከርም ይፈልጋሉ። ከዚያም ጥሩ መሆኑን ይረዳሉ። በቋሚነትም ሊያገኙት ይፈልጋሉ። የምሥራቁን ነገር የማግኘት ጉጉት የሚጠፋ፤ የሚሻር አይነት አልሆነም።»
በማግደቡርግ ጀርመን አካባቢ በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ጊዜ የነበሩ ከ 20 ሺህ በላይ የቤት ቁሳቁሶችን ቤተ መዘክር በማቋቋም በዓዉደ ርዕይነት ለተመልካች ያቀረቡት ዲርክ ግሩነር እንደሚሉት ሰዎች የምሥራቅ ጀርመኑን ጊዜ ነገሮች የሚናፍቁት የፖለቲካዉን ሁኔታ በመፈልግ ሳይሆን በዉስጣቸዉ የተቀበረዉን የናፍቆት ስሜትን ለማርካት ነዉ። እንደ ግሩነር ሰዎች ድሮ ሲጠቀሙባቸዉ የነበሩ ቁሳቁሶችን በማየታቸዉ እንኳ ሲረኩ ይታያል።
በርካታ የቀድሞ ምሥራቅ ጀርመን ዜጎች በተዋሐደችዉ በዛሬዋ ጀርመን ዉስጥ ሀገር አልባነት እና እንግድነት ይሰማቸዋል። በበርሊን ፍራይ ዩንቨርስቲ የማኅበረሰብና የፖለቲካ ጉዳይ ምሁሩ ክላዉስ ሽሮደር ይህን ምሥራቁን የመናፈቅ ነገር በተመለከተ፤ እንደሚሉት በምሥራቅ ጀርመን የነበረዉ ሕይወት ቀላልና ያልተወሳሰበ ነበር። ከዉሕደቱ በኋላ በመጣዉ የነፃ ገበያ ምክንያት በርካታ የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ብዙ የደከሙበትና ሲገነቡት የነበረዉ ሥራ ሁሉ ዉድቅ ሆኖባቸዋል።

«አብዛኞች በይፋ ሀገር አልባነት ይሰማቸዋል። በተዋሐደችዉ ጀርመን አሁንም ባዕድ እንደሆኑ ነዉ የሚሰማቸዉ። ለዚህም ነዉ አብዛኞቹ ከቀድሞ የሆነ ነገር ፈልገዉ እዝያ ላይ መጣበቅን የሚሹት። ይህ ደግሞ ምንም አይነት አደጋ የለዉም። አደጋ ሊሆን የሚችለዉ ነጻነትና ዲሞክራሲን በማመዛዘን ለወቅታዊዉ የፖለቲካ ሁኔታ ግዴለሽ ሲኮን ነዉ። እዚያ ላይ መጠንቀቅ ይኖርብናል።»
በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ጀርመን ማለትም DDR ከተመረቱት ተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኞቹ ከተጣሉ በኋላ በአሁኑ ወቅት በዚያን ጊዜ የነበሩት ተሽከርካሪዎች ዳግም ብቅ እያሉ ነዉ። አፍሪቃ ዉስጥ በሚደረጉ የመኪና ሽቅድድሞችሽ ላይ የምሥራቅ ጀርመን መኪኖች ለመወዳደርያ ቀርበዉም ታይተዋል። ያኔ ምሥራቅ ጀርመን ዉስጥ አንድ መኪና መግዛት የሚፈልግ ሰዉ አስር ዓመት መጠበቅ እንደነበረበት ይታወሳል። እነዚህ መኪኖች አሁን ለሰርግ ወይም ለመዝናኛ በኪራይ ይቀርባሉ። ሰዎች እነዚህን መኪኖች ተከራይተዉ ሲጠቀሙባቸዉ ታድያ በምሥራቅ ጀርመን የነበረዉን የመተባበርና የአብሮነት ጊዜ ያስታዉሳሉ።

Deutschland Mauer an der Bernauer Straße
ምስል picture-alliance/dpa/Keussler
Musikabteilung im HO-Warenhaus in Erfurt 1957
ምስል picture-alliance/ZB/R. Hirschberger
Deutschland Trabant mit Blumen (Symbolbild)
ምስል gemeinfrei
Deutschland Logo der SED
ምስል picture-alliance/dpa/ Zentralbild Wittig


አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ