1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምርጫ ሰሞን ትዝብት በጀርመን ከተሞች

ማክሰኞ፣ መስከረም 9 2010

የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ሊከናወን ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀሩታል። ቅድመ-ምርጫ ሒደቱን ለመታዘብ ባልደረባችን ማንተጋፍቶት ስለሺን ጨምሮ 5 የዶይቸቬለ የአፍሪቃው ክፍል ጋዜጠኞች ወደ በርሊንና አካባቢዋ አቅንተው ነበር። ጉዟቸው እስከ ፖላንድ የድንበር ከተማ በመዝለቅ አነስተና መንደሮችንና ከተሞችን ያካተተ ነበር።

https://p.dw.com/p/2kJZk
DW Bus Germany Decides Bundestagswahl 2017
ምስል DW/U.Shehu

የቅድመ-ምርጫ ዘገባ ከበርሊንና አካባቢዋ

ወደ በርሊን ጉዟችን (ICE) በተሰኘው «ከተሞችን አገናኝ ፈጣን ባቡር» ነው። የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ሰሞን ድባብን ለመቃኘት የሚደረግ ጉዞ። ምሥራቃዊ ጀርመን እምብርት ላይ የምትገኘው መዲናይቱ በርሊን ለመድረስ ግን ፈጣኑ ባቡር ከአምስት ሰአት በላይ መምዘግዘግ ይጠበቅበታል። ታዲያ ባቡሩ ለጥ ባለው ሜዳማ ሐዲዱ ላይ እንዲያ ሲከንፍ አንዳች መንገራገጭ አይታይበትም። ምኞት በሚሰጠው ባቡር ውስጥ የዶይቸ ቬለ የአፍሪቃው ክፍል አምስት ጋዜጠኞች ተቀምጠናል። የሐውሳ፣ ኪስዋሂሊ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ ለቀፍሪቃና  የአማርኛ ቋንቋ ክፍል ጋዜጠኞች። ጉዟችንም መጤ ጠል፣ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች በስፋት ወደሚንቀሳቀሱበት ምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ነው። 

እሁድ፤ መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በመላ ጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ይከናወናል። አምስት በመቶ እና ከዚያ በላይ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት በጀርመን ምክር ቤት (Bundestag) መቀመጫ ለማግኘትም የፖለቲከኞቹ ክርክር እና ቅስቀሳ ቀጥሏል። ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች በክፍለ ሃገራዊ ምርጫ ከጀርመን 16 ግዛቶች በ13ቱ መቀመጫ ማግኘታቸው ደግሞ የዘንድሮውን ምርጫ ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል። የጉዟችን የመጀመሪያ መዳረሻችን ቢተርፌልድ የተሰኘችው ከተማ ነበረች።

ዛክሰን አንሐልት ግዛት ውስጥ በምትገኘው በዚህች ቢተርፌልድ በተሰኘችው ከተማ ጎዳናዎች ላይ በተለይ ስደተኞችን እና እስልምናን የሚጠላው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ (AFD) የምርጫ ቅስቀሳ ወረቀቶች በጉልህ ይታያሉ። 

Deutschland Bundestagswahl Reise | Afrikanische Journalisten in Berlin | Jürgen Gewinner
ዮን ጌቪነር በኮተን ከተማ የማዛጋጃ ቤት የግራዎቹ ፓርቲ አባልምስል DW/M. Sileshi Siyoum

በአቅራቢያ በምትገኘው ኮተን በተሰኘችው ሌላኛዋ አነስተኛ ከተማ የግራዎቹ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ጥቂት ደቂቃዎች እንደቀሯቸው የከተማዪቱ ማዛጋጃ ቤት የመረጃ አገልግሎት ሠራተኛ ነገሩን። ዶይቸ ቬለ ለጀርመን ምርጫ ቅኝት ባዘጋጀው ሚኒባስ ስንከንፍ አነስተኛዋ ኮተን ከተማ ደረስን። 

ማግደቡርግ እና ላይፕሲሽ ለተሰኙት ከተሞች አማካይ የሆነችው ኮተን ከተማ እስክንደርስ ድረስም በየመንገዱ የሚታዩት የምርጫ ቅስቀሳዎች በብዛት የAFD ናቸው። ዮን ጌቪነር በኮተን ከተማ የማዛጋጃ ቤት ግራዎቹን ወክለው ይሠራሉ። ኮተን ከተማ ለቢተርፌልድ ቅርብ ብትሆንም መጤ ጠሉ ፓርቲ AFD አያሰጋቸውም።

«ያለነው ኮተን ውስጥ ነው። እዚህ በብዛት SPD፣ CDU እና ግራዎቹ ናቸው የሚመረጡት። በተለይ የግራዎቹ ዋነኛ የምርጫ ስፍራ ናት ኮተን። ቀኝ ዘመሙ AFD እዚህ ብዙም ተቀባይነት የለውም፤ ጠንከር ያለው ቢተርፌልድ ውስጥ ነው። የምንገኘው ቢተርፌድ አንሃልት አውራጃ ውስጥ ቢሆንም ቅሉ ጎላ የምንለው ግን እኛ ነን።»

የማዛጋጃ ቤቱ ሠራተኛ ዮን ጌቪነር የምርጫ ቅስቀሳ ወረቀቶች በየጎዳናው ጎልተው መታየታቸው የፓርቲው ጥንካሬን አያሳይም ሲሉም አክለዋል። ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ ሥርጭት ባለው ቢልድ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ እሁድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓም እንደወጣው ዘገባ ከሆነ መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ (AFD)በቅድመ ምርጫ የድምፅ መለኪያ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ጀርመን ቀኝ ጽንፈኞችን ከምክር ቤት ለማራቅ የአምስት በመቶ የመራጮች ድምጽ ሕግ አላት። በዚህም መሠረት አንድ ፓርቲ ወደ ጀርመን ምክር ቤት ለመግባት አምስት ከመቶ እና ከዚያ በላይ የመራጮች ድምጽ ሊያገኝ ይገባል። የኮተን ከተማ ነዋሪው የ19 ዓመቱ ሊዮን ሊኪያንቾክ የሚደግፈው የግራ ፓርቲ በምክር ቤት 10 በመቶ ድምጽ እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል። «ዐሥር በመቶ የመራጭ ድምጽ እናገኛለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ያን ማግኘት ወሳኝ በመሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ።»

Deutschland Wahlkampf Die Linke in Köten, Sachsen-Anhalt
የኮተን ነዋሪው የ19 ዓመቱ ሊዮን ሊኪያንቾክምስል DW/M. Sileshi Siyoum

ሊዮን ግራዎቹ ፓርቲን የሚመርጠውም ለማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች ጥሩ መልስ አላቸው በሚል ነው። 29, 000 ግድም ነዋሪዎች ያሏት ኮተን ከተማ እስክንደርስ እና ከዚያም ስንወጣ መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት ፓርቲ (CDU) የቅስቀሳ ወረቀቶች አነስተኛ መሆናቸውን ታዝበናል። ወደ ላይፕሲሽ ከተማ ባደረግነው ጉዞ ግን መራኂተ መንግሥቷ የሚወክሉት ፓርቲ ቅስቀሳ ጎላ ብሎ ታይቷል። 

ኢትዮጵያዊው ጀቤሳ ተሾመ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በቢዝነስ አስተዳደር የ3ኛ ዓመት የዶክትሬት ተማሪ ነው። የዕውቀት ሽግግርን ማበልጸግ በሚል ለአንድ ወር ስልጠና ላይፕሲሽ ከተማ መጥቶ ላይፕሲሽ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነው ያገኘሁት። ጀርመን ከመጣ ስምንተኛ ቀኑ ቢሆንም የጀርመን ምርጫ ትዝብቱን ሲገልጥ መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስደተኞችን በተመለከተ የወሰዱት አመራርን በማድነቅ ነው። ጀቤሳ በጀርመን አጭር ቆይታው ያስደመመውን ሌላ ጉዳይ እንዲህ ይገልጣል። 

«ሌላ በጣም የማረከኝ ተሳትፎው ነው። የተሳትፎ ባሕሉ፤ መድረኩን የሚመራው ሰብሳቢ መቆጣጠር እስከሚያቅተው ድረስ ፓርቲዎቹ እርስ በእርሳቸው በጣም እየተጩሃጫኹ  በጣም ተሳትፏቸው ይታይ ነበር።  ተጨቃጭቀው ተሳስመው አብረው ነው የሚሄዱት። እና ይሄ  ባሕል በእኛም በአፍሪቃ በአጠቃላይ ሊለመድ እና መማሪያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ በግሌ።»

በእርግጥም ጀቤሳ ያለውን የፓርቲዎች መቀራረብ ጀርመንን ከፖላንድ ጋር በድልድይ በምታዋስነው የፍራንክፉርት አን ደር ኦደር ከተማ ላይ ታዝበናል። የድንበር ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ አንድ አዳራሽ አምስት ፓርቲዎች ተሰባስበዋል። አዳራሹ ውስጥ የመገናኘታቸው ዋነኛ ምክንያቱ ታዲያ እርስ በእርስ ተቀራርበው ለመወያየት እናም በሚገባ ለመተዋወቅ ነው። 

Alexander Gauland AfD Politiker
የመጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲን (AFD) ከመሠረቱት አንዱ አሌልሳንደር ጋውላንድምስል picture-alliance/dpa/M. Murat

በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት (CDU) ፓርቲ የጥምር መንግሥት አባል የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ (SPD)፣ የግራዎቹ ፓርቲ፣ አረንጓዴዎቹ ፓርቲ፣ እንዲሁም የነጻ ዲሞክራቶች ፓርቲ (FDP) ዕጩ ተወዳዳሪዎች እና አባላት እየተሳሳቁ፤ ከፖለቲካውም ባሻገር ስለ ግል ሕይወታቸው እየተጨዋወቱ በደንብ ለመቀራረብ መሞከራቸው ለአፍሪቃው ክፍል ጋዜጠኞች ያልተለመደ ክስተት ነበር፤ ግን እጅግ አስደማሚ።

በአዳራሹ ውስጥ ፖለቲከኞቹ ለመግባባት ሲጥሩ ማግደቡርግ የተሰኘችው ሌላኛዋ ከተማ ውስጥ ደግሞ መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ (AFD) ሌላ ጽንፍ ይዞ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያከናውን ነበር። «ከአባቶቻችን የወረስነው አባት ሀገር ሲወረስ በዝምታ አናልፈውም፤ሽብር በዛ፤ ድንበር ተበርግዶ እንዲቆይ አንሻም» ያሉት ከAFD መሥራቾች አንዱ የሆኑት አሌክሳንደር ጋውላንድ ናቸው። «አንድ ሚሊዮን ግድም ስደተኞች ወረሩን» በማለት የጋለ ቅስቀሳ ሲያኪያሂዱ ድጋፍ እና ተቃውሞ የገጠማቸው አሌክሳንደር ጋውላንድ ለተቃዋሚዎቻቸው ደንታ እንደሌላቸው በመግለጥ ንግግራቸውን ቀጠሉ። 

«ውድ ወዳጆች በማያሻማ መልኩ ተናግሬያለሁ፤ እስልምና የጀርመን አካል አይደለም። እዚያ ያሉት እንደፈለጉ መጮኽ ይችላሉ። ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ሥርዓት ይኑረን የምንል ከሆነ ግን ያን ጊዜ በዚያ ለመሰቃየት የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሾቹ እኛው ነው የምንሆነው።» 

Deutschland AFD Wahlkampfveranstaltung in Magdeburg
ፖሊስ የቀኝ ዘመሞች የምርጫ ቅስቀሳን በመቃወም የመጡ ሰልፈኞች ፊት ተደርድሮ እየጠበቀምስል DW/M. Sileshi Siyoum

አሌክሳንደር ጋውላንድ ሲናገሩ የተቃውሞ ድምጽና ጩኸት ያሰሙትን በመዝለፍ «ሀገራችሁን እንዳይነጥቁ ከፈለጋችሁ በምርጫው ወቀት ለብቻችሁ በሆናችሁበት ወቅት ድምጻችሁን ለአ ኤፍ ዴ ስጡ» ሲሊ ንግግራቸውን ቋጭተዋል። ለቅስቀሳ ንግግር መድረኩን የተረከቡት የአማራጭ ለጀርመን የአካባቢው ዋነኛ ዕጩ ተወዳዳሪ ማርቲን ራይሻርድ በበኩላቸው የቃላት አጠቃቀማቸው እና የንግግር ዘዬያቸው በብዙዎች ዘንድ ፍጹም ቀኝ ዘመም ናቸው ያስብላቸዋል። ደንገዝገዝ ብሎ ካፊያ የዋጠውን መሰብሰቢያ ስፍራ ድባብ በመጠቀምም ለቅስቀሳ እንዲህ ተጠቅመውበታል። 

«በጋው እያከተመ መኾኑን ሁላችንም የምንገነዘበው ነው። በጀርመን መቀዝቀዙ አይቀርም። ለበርካታ ሰዎች ግን በሀገራችን ቅዝቃዜው ማንዘፍዘፍ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥሯል። ቅዝቃዜው ለጀርመን ሠራተኞች ነው። መንዘፍዘፉ ለጡረተኞች ነው። ለልጆቻችን፤ ለእኛው ለጀርመኖች በሀገራችን ቀዝቅዞናል። በዚህ ሀገራችንን ቆፍኖ በያዘው ቅዝቃዜ ላይ ለሚነሳ ጥያቄ ደግሞ መልሱን ዕናውቀዋለን። የዚህ ቅዝቃዜ ሰበብ አንጌላ ሜርክል እና አስተዳደራቸው ናቸው።»

ማርቲን ራይሻርድ ከደጋፊዎቻቸው በተቃራኒ በፖሊሶች ከታጠረው ሥፍራ ላይ የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰሙትን እንደመሳደብ ሲቃጣቸው ተቃውሞው ይበልጥ ይደራል። ራሳቸውን አርበኛ ሲሉ ይጠራሉ በንግግራቸው። የዝቅተኛው ማኅበረሰብን ችግር በመጠቃቀስ ፓርቲው ከፍተኛ ቅስቀሳ እያደረገ ነው። በእርግጥም በተዘዋወርንባቸው አነስተኛ ከተሞች እና መንደሮች ከሌላው አንጻር መሠረተ ልማቱ ዝቅተኛ ሲሆን ቀድሞ የነበሩ ፋብሪካዎች ዳዋ ወርሷቸው ጣራዎቻቸው ተበታትከው ይታያሉ። በነዚያ ሥፍራዎች የሚገኙ በርካታ መራጮች ልባቸው የሸፈተ ይመስላል። ማንን ትመርጣላችሁ ሲባል በቀጥታ ባይናገሩም ከመልሳቸው በመራኂተ መንግሥት እና በተጣማሪ ፓርቲው የታከቱ ይመስላሉ። 

በርሊን ከተማ ውስጥ ያገኘናቸው ወይዘሮ ቢርጌት ጡረተኛ ናቸው። በምርጫው ቀን ያለማወላወል ትክክለኛ የሚሉትን ፓርቲ እንደሚመርጡ ተናግረዋል። «ማንን መምረጤ ምሥጢር ነው፤ ግን የምመርጠውን አውቃለሁ» ያሉት ጡረተኛ «መምረጥ የዜግነት ግዴታ ነው»ም ብለዋል።

«ሁሉም የየራሱን ሐሳብ የማንጸባረቅ መብት አለው። ያ ደግሞ ምንም አይደለም። በእርግጥ አንዳንድ ፓርቲዎች ቀኝ ዘመሞች ባይመቹኝም።» ብለዋል።
ቀኝ ዘመም ፓርቲ ደጋፊ እንደሆኑ የተናገሩት ፊንላንዳዊው ሀገር ጎብኚ በበኩላቸው ሁሉም ሰው እኩል መታየት አለበት ይላሉ። 

Deutschland Bundestagswahl Reise | Afrikanische Journalisten in Berlin | dänisches Ehepaar in Berlin
የዴንማርኩ አገር ጎብኚ ከባለቤታቸው ጋር በበርሊን ከተማምስል DW/M. Sileshi Siyoum

«መፋጠጥን ማስወገድ የሚገባ ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት እንደምመለከተው ከሆነ ወሮ አንጌላ ሜርክል ይህን መፋጠጥ ያስወግዳሉ ብዬ እገምታለሁ።» እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 61,5 ሚሊዮን ጀርመናውያን አጠቃላይ የጀርመን ምርጫ ላይ በመሳተፍ መምረጥ ይችላሉ። ከዚያ ውስጥ 22 ሚሊዮን ያኽሉ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን ናቸው። እሁድ፤ መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚከናወነው ምርጫ ማን ጎልቶ እንደሚወጣ አይታወቅም። የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት ፓርቲ (CDU)ከተጣማሪው ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ (SPD)በቅድመ ምርጫ ድምጽ መለኪያ መብለጡ ይታወቃል። መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን (AFD)ፓርቲም በሦስተኝነት እየገሰገሰ ነው። ማን ጎልቶ ይወጣል? በቀናት ልዩነት ይወሳናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ