1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ አፍሪቃ የስደተኞች ቀዉስ

ዓርብ፣ መስከረም 14 2008

አዲሱ የናይጀርያ መንግሥት በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉን አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራምን ለማጥፋት ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሎአል። በሌላ በኩል ይህ ሽብርተኛ ቡድን ያገታቸዉን ልጃገረዶች ለማስለቀቅ እየተደራደረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GdZF
Nigeria Flüchtlinge wegen der Offensive gegen Boko Haram
ምስል Reuters/A. Sotunde

[No title]

ያም ሆኖ ግን በናይጀርያ፣ እንዲሁም በጎረቤት ኒጀር፣ ካሜሩን እና ቻድ የሚታየው ከፍተኛ የስደተኛ ቀዉስ እንደሚገባው የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ሽፋን አላገኘም። በነዚህ ሃገራት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ ከአሸባሪው ቡድን ጥቃት ለማምለጥ የመኖርያ ቀየዉን እየጣለ ሸሽቶዋል ።

Nigeria Flüchtlinge wegen der Offensive gegen Boko Haram
ምስል Reuters/A. Sotunde

ወጣትዋ እናት ፋቲማታ ከፀሐይ መከላከያ ይሆናት ዘንድ ሁለት እራፊ ጨርቅ ከዛፍ ቅርንጫፍ ጋር አስራ በሰራችዉ የፀሐይ መከላከያ ስር ልጅዋን አቅፋ ተቀምጣለች።

«አሸባሪዉ ቦኮሃራም የምንኖርበትን ገጠር በእሳት አጋየ፣ በቃጠሎዉ ሶስት ሰዎች ሞቱ። ከሟቾቹ መካከል አንዱ ጎረቤቴ ነበሩ። ከዚያ በኋላ ነበር ሌሊት ተነስተን የጠፋነዉ። አሁን ባለቤቴ አካባቢያችን ላይ የቀረ ነገር ካለ ለማትረፍ ወደዚያው ተመልሶ ሄድዋል።»

ከ 2000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቻድ ባህር አጠገብ ከሚገኘዉ ቦታ እየሸሹ ቻድ ወደሚገኙ ጊዜያዊ የመጠለያ ቦታዎች ደርሰዋል። በቻድ የሚገኙ የተመድ ርዳታ አቅራቢዎች ለነዚህ ሰዎች መሠረታዊ ርዳታን ለመስጠት እየሞከሩ ነዉ። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባልደረባ አድል ሳርኮዚ እንደሚሉት ሰዎቹ ቦኮሃራምን እየሸሹ ነዉ መኖርያቸዉን እየጣሉ የወጡት ።

« እነዚህ ሰዎች በወንዙ ላይ የሚገኘዉን የመኖርያ ደሴት ጥለዉ የሸሹት፤ በቦኮሃራም ጥቃት ስለደረሰባቸዉ ነዉ። አሁን እዚህ መጥተዋል፣ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ይበልጥ ድጋፍ ያስፈልገናል።»

ናይጀርያ ከ 2,1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች፤ በጎረቤት ደግሞ ካሜሩን ወደ 200 ሺህ ስደተኞች ይገኛሉ። በኒጀርም ሁኔታዉ አሳሳቢ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት እየገለፀ ነዉ። በደቡብ ኒጀር «ዲፋ» በተሰኘ አካባቢ ወደ 340 ሺህ ስደተኛ እጅግ በከፋ ሁኔታ ነዉ ኑሮዉን የሚገፋዉ። የሰሜናዊ ናይጀርያ ነዋሪዎች ዉጥረት ከሚታይበት አካባቢያቸው የፀጥታው ሁኔታ ምናልባት የተሻለ ነዉ ወደሚሉበት ወደሌላዉ የሃገሪቱ ክልሎች ይፈልሳሉ። ከነዚህ መካከል ከመቶ አስሩ የሚኖሩት በስደተኛ መጠለያ ቦታዎች ሲሆን፣ የተቀሩት በሌሎች ነዋሪዎች ርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው፤ አልያም በግላቸው የመኖርያ ቦታ ይፈልጋሉ። ከቦኮሃራም የሸሹ ስደተኞች በናይጀርያ መዲና አቡጃ ከተማ መዳረሻ የመፀዳጃ ቦታ፤ ኤሌትሪክና የመጠጥ ዉኃ በሌለበት መጠለያ ስፍራ ላይ ይኖራሉ። በአካባቢዉ ለስደተኞች የሚሆን መሠረታዊ ርዳታ ተጓድሎ ነው የሚገኘው። የዓለም አቀፍ ርዳታ ድርጅቶችም ቢሆኑ አስፈላጊውን ርዳታ ሁሉ ማቅረብ አልቻሉም። የናይጀርያ መንግሥት አሸባሪዉን ቡድን ቦኮሃራምን በአንድ ወር ጊዜ እንደሚያስወግደ ባለፈዉ ነሐሴ ወር ከገለፀ በኋላ አሸባሪዎች በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች በሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ጥቃት በመጣል መልስ ሰጥቶአል። ይህም የአሸባሪዎቹ ጥቃት እና በሰበቡ የተፈጠረው የስደተኞች ፍልሰት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጎታል። ይሁንና፣ ይኸው ገሃድ ሁኔታ በአዉሮጳ በወቅቱ የሚታየውን የስደተኞች ቀዉስ ያህል የብዙዎችን ትኩረት አላገኘም።

Kamerun Flüchtlingslager Minawao
ምስል AFP/Getty Images/R. Kaze

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ