1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞስኮዉ ጥቃትና ያስከተለዉ ዉግዘት

ማክሰኞ፣ ጥር 17 2003

«የከባድ ፍንዳታ ድምፅ ሰማሁ።ከዚያ በሕዋላ ምንም መስማት አልቻልኩም።ጭንቃላቴን ጥርቅም አድርጌ ይዤ እንደ ነበር አስታዉሳላሁ።ሁሉም ይሮጥ ነበር።በእዉነት አስደንጋጭ ነበር።»

https://p.dw.com/p/QvDZ
ዶሞዴዶቮ-አዉሮፕላን ማረፊያምስል picture-alliance/dpa

25 01 11

አንድ አጥፍቶ ጠፊ ሞስኮ አዉሮፕላን ማረፊያ ትናንት ባፈነዳዉ ቦምብ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 35 ደረሰ።በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ 170 ሰዎች ቆስለዋል።የሩሲያ የሥለላና የፀጥታ ባለሙያዎች ከአጥፍቶ ጠፊዉ ጋር የተባበሩትን ለመያዝ እያሰሱ ነዉ።ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድሜዴቭ የሩሲያ አዉሮፕላን ማረፊያዎች በሙሉ ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተኛ እንዲደረግባቸዉ አዝዘዋል።የተለያዩ ሐገራትና አለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ጥቃቱን እያወገዙ፥ ከሩሲያ ጎን ለመቆም ቃል እየገቡ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

«በመድረሻዉ ክፍል ነዉ የሆነዉ።ማንም ሰዉ ወደ ዚያ መግባት ይችላል።በልማዱ ከሌላ ቦታ የሚመጡ መንገደኞችን ለመቀበል የየመንገደኛዉ ወዳጅ-ዘመድ፥ ባልደረባ እዚያ ይጠብቃል።መንገደኞች ደግሞ የፓስፖርትና የጉምሩክ ፍተሻዉን እንዳጠናቀቁ ወዲዚያ ክፍል ይገባሉ።»

የአዉሮፕላን ማረፊያዉ ቃል አቀባይ።

ከሁለት እስከ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብ ያጨቀዉ ሰዉዬ-እዚያች ክፍል መቼ እንደገባ አይታወቅም።ግን በተቀባይ-መጪዎች ከተጨናነቀዉ ክፍል ሰተት ብሎ ገባ።አስር-ሰአት ተኩል። የከባድ ቦምቡን ቀለበት ፈለቀቀዉ።

«የከባድ ፍንዳታ ድምፅ ሰማሁ።ከዚያ በሕዋላ ምንም መስማት አልቻልኩም።ጭንቃላቴን ጥርቅም አድርጌ ይዤ እንደ ነበር አስታዉሳላሁ።ሁሉም ይሮጥ ነበር።በእዉነት አስደንጋጭ ነበር።»

እሳቸዉም እዚያ ነበሩ።
«ከባድ ድምታ ሰማሁ።ወለሉ ላይ ተኛን።ወዲያዉ ክፍሉ በጢስ ተጀቦነ።ብዙ የቆሰሉና የሞቱ ነበሩ።በመኪና ተወሰዱ።»

የዶሞዴዶቮ አዉሮፕላን ማረፊያ-መቀበያ ክፍል በጢስ-ንዳጅ ቅርናት ታጠነ።በደም-አስከሬን ጨቀየ። ሞስኮቫይቶች እንደገና ተሸበሩ።ደነገጡ።አብዛኞቹ ሟች ቁስለኞች የሩሲያ ዜጎች ናቸዉ።የሌላ ሐገር ዜጎችም አሉበት።እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ ሁለት የብሪታንያና አንድ የጀርመን ዜጎች መሞታቸዉ ተረጋግጧል።አንድ ሌላ ጀርመናዊ፥ አንድ ፈረንሳዊ፥ አንድ ኢጣሊያዊ ቆስለዋል።

ቦንቡን ያፈነዳዉ ሰዉ ወይም ሰዉዬዉን ያዘመተዉ ወገን ማምነት በዉል አልታወቀም።የሩሲያ መገናኛ ዘዴዎች በስም ያልጠቀሷቸዉን የሐገሪቱን የፀጥታ ባለሥልጣናት ጠቅሰዉ እንደዘገቡት ጥቃቱን ያስጣሉት ወገኖች የሰሜናዊ ካዉካሰስ በጣሙን የቼቺንያ አማፂያን ሳይሆኑ አይቀሩም።

ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ግን ፀጥታ አስከባሪዎቻቸዉን ነዉ-የወቀሱት። ለወደፊቱም ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘዋል።

«አዉሮፕላን ማረፊያዎች በሙሉ ጠንካራ ጥበቃና ቁጥጥር ሊደረግባቸዉ ይገባል።የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የትራንስፖርት ሚንስቴር ከሐገር ዉስጥ የስለላ መስሪያ ቤት ጋር የተቀናጀ ቁጥጥር ክትትል እንዲያደርጉ አዝዢያለሁ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ጥቃቱን ቀድመዉ ካወገዙት ሐገራት መሪዎች አንዱ ናቸዉ።ዉግዘቱን ቃል አቀባያቸዉ አነበቡት።

«በዶሞዴዶቮ አዉሮፕላን ማረፊያ ሩሲያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመዉን ይሕን ጭካኔ የተመላበት የሽብር ጥቃት አጥብቄ አወግዛለሁ።የአሜሪካ ሕዝብ በዚሕ አስቀድሞ በታሰበበትና በሰለማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀመዉ ጥቃት ከተጎዳዉ ከሩሲያ ሕዝብ ጎን እንደሚቆም መግለፅ እፈልጋለሁ።እኔና ሚሼል በሽብሩ ክፉኛ ለተጎዳዉ ለሩሲያ ሕዝብ ጥልቅ ሐዘናችንን እንገልጣለን።»

የሰሜን አትላንቲክ የጋራ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ፀሐፊ አድረስ ፎግሕ ራስሙስን በበኩላቸዉ አደጋዉ «በሁለችንም» ላይ ነዉ-የተፈፀመ ነዉ ባይ ናቸዉ።
«ተመሳሳይ የሽብር አደጋ ነዉ የደረሰብን።እና በጋራ ልንቋቋመዉ ይገባል።ሩሲያና ኔቶ በፀረ-ሽብር ዘመቻዉ ያላቸዉን ትብብር ማጠናከር አለባቸዉ የምንለዉም ለዚሕ ነዉ።

ባለፈዉ ታሕሳስ ማብቂያ ሞስኮ በሚገኝ አንድ ሕንፃ ዉስጥ የፈነዳ ቦምብ አንዲት ሴት ገድሎ ሕንፃዉን አዉድሞት ነበር።የሩሲያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ቦንቡን በስሕተት ያፈነዳችዉ ሟቿ ሴትዮ በጎሮጎሮሳዉያኑ ዘመን መለወጫ ሞስኮን ለማሸበር ከሰሜናዊ ካዉካሰስ ከዘመቱ አሸባሪዎች አንዷ ነበረች።የፀጥታ ባለሥልጣናት እንደሚጠረጥሩት የትናንቱ አጥፍቶ ጠፊም ከሴትዮዋ ጋር ወደ ሞስኮ የገባ ሳይሆን አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዪ ለገሠ