1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞት ቅጣትና የጄኔቩ ጉባኤ

ዓርብ፣ የካቲት 19 2002

የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ አለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችና ተቋማት የሞት ቅጣት በሕግ በተደነገጋባቸዉ ሐገራት ለሚንቀሳቀሱ የፀረ-ሞት ቅጣት ሐገር በቀል ድርጅቶች ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ተስማሙ።

https://p.dw.com/p/MDL5
ምስል idt
ጄኔቭ-ሲዊትሰርላንድ በተሰየመዉ በአራተኛዉ የፀረ-ሞት ቅጣት አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የመብት ተሟጋቾችና ባለሙያዎች የሞት ቅጣትን በሕጋቸዉ የደገጉ መንግሥታት ሕጉን እንዲሰርዙ ጠይቀዋልም።የሞት ቅጣትን ለማስቀረት ባለፉት ሰላሳ አመታት የተደረገዉ ትግል ጥሩ ዉጤት ቢያመጣም አሁንም ብዙ መንግሥታት ቅጣቱን ከየሕጋቸዉ አልሠረዙትም።ነጋሽ መሐመድ ከዜና መልዕክቶችንና ከአንድርያስ ዙማሕ ዘገባ የሚከተለዉን አጠናክሯል። የሞት ቅጣት እንዲቀር፥ ቅጣቱን ለማስቀረት የሚደረገዉ ትግል እንዲጠናከር በአለም አቀፍ ጉባኤ ሲመከር፥ የአዋቂዎች ምክር-አስተያየት ሲቀርብበት ባለፈዉ ሮብ የተጀመረዉ አራተኛዉ ነዉ። ፅንሠ-ሐሳቡ ካጎነቆለ ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢጣሊያዋ አምባሳደር ላዉራ ሚራቺያን ለጉባኤተኞች እንደነገሩት ከሁለት መቶ አመት በፊት ነበር። «ኢጣሊያ የሞት ቅጣትን አሉታዊነት በማሳየት የረጅም ጊዜ ልምድና ሥር የሰደደ ባሕል አላት።ከ18ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ጀምሮ።ታስከኒ የሞት ቅጣትን በማስቀረት ከአለም የመጀመሪያዉ መንግሥት በሆነበት ወቅት።እንደሚመስለኝ በ1786 ነበር።» ዘመናይቱ ኢጣሊያ ግን እስከ 1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ድረስ ጅምሩን ከግብ አላደረሰችም ነበር።በዚያዉ አመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አጠቃላይ የሰብአዊ መብት ደንብን አፀደቀ።ደንቡ የሞት ቅጣት እንዲቀር የሚጠይቅ አንቀፅ የለዉም።ይሁንና የደንቡ አንቀፅ-ሰወስት የሰዉ የመኖር መብት እንዲከበር እና ማንም ሰዉ የሚያሰቃይ ቅጣት እንዳይበየንበት መደንገጉ የሞት ቅጣት እንዲነሳ ለሚደረገዉ ጥረት መሠረት ሆነ። ደንቡ ከፀደቀ-አለም አቀፉ ድርጅት በ1966 የሰብአዊ መብት ዉልን እስካወጣበት ድረስ በተቆጠሩት አመታት-በ1949 ባዲስ መልክ ከተመሠረተችዉ ከጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ መስተቀር የሞት ቅጣትን ያስቀረ ሐገር አልነበረም።ከዚያ በሕዋላም ኢጣሊያዊዉ የመብት ተሟጋች ማሪዮ ሞራሲቲ እንዳሉት የሞት ቅጣትን የሰረዙት ሐገራት ጥቂት ነበሩ። «እስከ 1970ዎቹ ድረስ የሞት ቅጣትን የሠረዙት የአለም ሐገራት ሃያ-ሰወስት ብቻ ነበሩ።» ከ1980ዎቹ በሕዋላ ግን ሐሳቡ እየደረጀ የብዙዎችን ተቀባይነት አገኘ። «ባለፉት ሰላሳ አመታት ይሕንን ታላቅ ለዉጥ አይተናል።አዉሮጳ ከአለም የሞት ቅጣት የሌለባት የመጀመሪያዋ ክፍለ-አለም ሆናለች።» ባሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ ዘጠና ሁለቱ የአለም ሐገራት አንድ መቶ አርባ አንዱ የሞት ቅጣትን ከየሕጋቸዉ ሰርዘዋል።የተቀሩት ሐምሳ አንዱ ሐገራትና አምስት ግዛቶች ግን አሁንም ሰዉን በሞት ይቀጣሉ።በ2008 ብቻ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደ ዘገበዉ1290 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ የተገደሉት ቻይና፥ኢራን፥ ሳዑዲ አረቢያ፥ ሰሜን ኮሪያና ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ነዉ።ከአንድ ሺሕ የሚበልጡ የመብት ተሟጋቾችንና ባለሙያዎችን ያሰባሰበዉ የአራተኛዉ አለም ጉባኤ ዋና አለማ የሞት ቅጣትን ከየሕጋቸዉ ያልዘረዙት ሐገራት ሲሆን እንዲሰርዙ ይሕ ቢቀር ለተወሰነ ጊዜ ቅጣቱን እንዳፈፅሙ መጠየቅ ነዉ። ተሰብሳቢዎቹ የሞት ቅጣት ባለባቸዉ ሐገራት የሚንቀሳቀሱ የፀረ-ሞት ቅጣት ተቋማትና ድርጅቶችን ለማጠናከርም ተስማምተዋል። Ips,Agenturen ነጋሽ መሀመድ ሂሩት መለሰ