1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሞት ቅጣት እና ናይጀሪያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2007

የሞት ቅጣት በዓለም ዓቀፍ ሕግ ደረጃ ሙሉ በሙሉ አልታገደም። ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደገለፀዉ፤ እንደዉም ይህን ቅጣት የሚወስኑ ሃገራት ቁጥር እየጨመረ፤ የሚተላለፈዉ ዉሳኔም እየበረከተ ሄዷል።

https://p.dw.com/p/1F27Z
Hinrichtungsraum Gefängnis Abu Ghraid Irak
ምስል picture alliance/dpa

ዓለም ዓቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብት ድንጋጌ፤ የሞት ቅጣትን ተግባራዊ ማድረግ የቀጠሉ ሃገራት የየራሳቸዉን ለዚህ የሚያበቃ ደረጃ እንዲያወጡ ጠይቋል። አፍሪቃ ዉስጥ ናይጀሪያና ግብፅ ባለፈዉ ዓመት ያሳለፉት የሞት ቅጣት ዉሳኔ በመላዉ ዓለም ከተላለፈዉ አንድ ሶስተኛዉን እንደሚወስድ የአምነስቲ ዓመታዊ ዘገባ ያስረዳል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 በመላዉ ዓለም የተላለፈዉ የሞት ፍርድ ከዚያ ቀደም ከነበረዉ ዓመት በ28 በመቶ በልጦ እንዳገኘዉ ነዉ የገለፀዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013 ዓ።ም በ22 ሃገራት 607 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ተፈፅሟል። እንደድርጅቱ ዘገባ ባለፈዉ ዓመት 55 ሃገራት 2,466 ሰዎች ላይ ይሙት በቃ ፈርደዋል። ከዚህ መካከል ከ1000 የሚበልጠዉ የተላለፈዉ በናይጀሪያና ግብፅ ነዉ። በተጠቀሰዉ ዓመት የተላለፈዉና የተፈፀመዉ የሞት ቅጣቱ ለመብዛቱ ምክንያት የሆነዉም ሃገራት ላይ የተቃጣ የሽብር ተግባር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ስጋት ነዉ እንደአምነስቲ። ዋና ጽሕፈት ቤቱ ሎንደን ብሪታንያ የሚገኘዉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ እንደሚለዉም የሞት ቅጣቱን ኢራን ወደ289ሰዎች ላይ፤ ሳዑድ አረቢያ 90፤ ኢራቅ 61 እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ 35ቱ ላይ ተፈፃሚ አድርገዋል። ዘገባዉን ያጠናቀረቡ ተቋም የቻይናን አላካተተም፤ ምክንያቱ እዚያ አብዛኛዉ ድርጊት ምሥጢራዊ አፈፃፀም ስላለዉ የሚል ነዉ።

USA Todesstrafe Hinrichtung durch Erschießung in Utah
ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የሞት ቅጣት መፈፀሚያምስል picture-alliance/dpa/T. Nelsen

የሞት ቅጣት የሚበየንባቸዉ ጥፋቶች እንደየሃገራቱ ድንጋጌም ይለያያሉ። ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ዉስጥ ዘማዊነት ያስገድላል፤ ሳዑድ አረቢያ ደግሞ ጠንቋይ በሞት እንዲቀጣ ወስናለች። ፓኪስታንና ኢራን ዉስጥ በፈጣሪ ላይ በመሳለቅና ነብዩ መሐመድ ላይ የስድብ ቃል በመሰንዘር በሞት የሚያስቀጡ ጥፋቶች መሆናቸዉ ተደንግጓል። አደንዛዥ እፅ ማዘዋወርና መቀመም እንዲሁም ሙስናም ለሞት ፍርድ የሚያበቁ ወንጀሎች ናቸዉ። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ኢንዶኔዢያ አንድ ናይጀሪያዊን በእፅ ማዘዋወር ይሙት በቃ ፈርዳበታለች።

ባለፈዉ ጎርጎሪሳዊ ዓመት ናይጀሪያ ዉስጥም ከዚያ በፊት ከነበረዉ በአምስት እጥፍ የሚበልጡ ማለትም ወደ659 የሚሆኑ ሰዎች ይሙት በቃ ተበይኖባቸዋል። ይህ ፍርድ ከተወሰነባቸዉ መካከልም በሀገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ግዛት ከፅንፈኛዉ እስላማዊ ቡድን ቦኮሃራም እንዲፋለሙ የተመደቡት የናይጀሪያ ጦር የሰባተኛዉ ብርጌድ ወታደሮች ይገኙበታል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የናይጀሪያ ጉዳይ ተንታኝ ኦሎዋቶሲን ፓፖላ፤

«በችሎቱ ወቅት ወታደሮቹ በሰጡት የምስክርነት ቃል ቦኮሃራምን ለመዉጋት የተሰማሩበትን ዘመቻ በተሳካ ዉጤት ለማጠናቀቅ ተገቢዉ የጦር መሣሪያ የለንም በማለት ለአዛዦቻቸዉ አቤቱታ ሲያቀርቡ ነበር።»

ይላሉ። ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀዉ ከዚህ ብርጌድ ወታደሮች አንዱ ለዶይቼ ቬለ የሀዉሳ ቋንቋ ክፍል እንደገለፀዉ፤ ወታደሮቹ በወቅቱ ወደጦርነት ሲላኩ በቂ መሣሪያም ሆነ ጥይት አልነበራቸዉም። ያኔ ቦኮሃራም በቦርኖ ግዛት የማይዱጉሪን ከተማ ተቆጣጥሮ ነበር። አብዛኞቹ ወታደሮችም ራስን የማጥፋት ርምጃ ነዉ ሲሉ በተቹት በዚህ ዘመቻ ለመሳተፍ ፈቃደኞች አልነበሩም። ከመካከላቸዉ ሰባዎቹ ወታደሮች በጦር ፍርድ ቤት በተከታታይ በጅምላ በተካሄደዉ የፍርድ ሂደት የሞት ቅጣት ተበይኖባቸዋል። የቀሪዎቹ ጉዳይ በይደር እየታየ ነዉ። አብዛኛዉ ሂደትም በዝግ የተካሄደ ሲሆን ለጋዜጠኞች የተፈቀደዉ ችሎቱ ሲጀመርና ብይን ሲተላለፍ እንደሆነ ያመለከተዉ የዶቼ ቬለዉ አድሪያን ክሪሽ ዉሳኔዉ በብዙዎች አስተያየት ፖለቲካዉ ተፅዕኖ ያረፈበት መሆኑን ይገልፃል።

Karte Sentenças de morte e execuções no mundo, 2014
በ2014የሞት ቅጣት የፈፀሙ ሃገራት

«በርካታ ናይጀሪያዉያን ይህ ጉዳይ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እንዳለዉ ያምናሉ፤ እናም የተከሰሱት ወታደሮች ለዚያ ሽፋን የተሰዉ የጭዳ በግ አይነቶች ናቸዉ።»

እንዲያም ሆኖ የሞት ፍርዱ መቼና እንዴት ተፈፃሚ እንደሚሆን አልተገለፀም። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ኦሉዋቶሲን ፖፖላ ከወትሮዉ በተለየ የናይጀሪያ ባለስልጣናት ይህን አስመልክቶ ያለዉን መረጃ ለማጋራት ፈቃደኝነት አሳይተዋል።

«ላለፉት ጥቂት ዓመታት የሞት ቅጣትን የሚመለከቱ መረጃዎችን ከናይጀሪያ የእስር ቤት አስተዳደርም ሆነ ከብሄራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ከፌደራል ፍትህ ሚኒስቴር ስናገኝ ነበር። ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ግን እንደዚያ አይደለም።»

በሀገሪቱ የተካሄደዉ ታሪካዉ ፕሬዝደንታዊና ብሄራዊ ምርጫ ዉጤት በእነዚህ ወታደሮች የሞት ብይን ላይ የሚያመጣዉ ለዉጥ መኖሩን አሁን መናገር አይቻልም።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ