1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሣምንቱ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 19 2004

ሃይሌ ገ/ሥላሴ አስደናቂ የስፖርት ታሪኩን በኦሎምፒክ የማራቶን ድል ለማጠቃለል ያለው ሕልም ከትናንቱ የቶኪዮ ማራቶን ውጤት በኋላ ከንቱ የመሆን ብርቱ አድጋ ላይ ወድቋል።

https://p.dw.com/p/14AvK
ምስል dapd

ሃይሌ ገ/ሥላሴ አስደናቂ የስፖርት ታሪኩን በኦሎምፒክ የማራቶን ድል ለማጠቃለል ያለው ሕልም ከትናንቱ የቶኪዮ ማራቶን ውጤት በኋላ ከንቱ የመሆን ብርቱ አድጋ ላይ ወድቋል። ሃይሌ በቶኪዮው ማራቶን በሁለት ሰዓት ክስምንት ደቂቃ 17 ሤኮንድ በሆነ ጊዜ አራተኛ ሲወጣ በለንደኑ ኦሎምፒክ በዚህ ርቀት መሳተፍ ከሚችሉት ሶሥት የኢትዮጵያ አትሌቶች አንዱ ለመሆን መብቃቱ ብዙ የሚያጠራጥር እየሆነ ነው። ቢቀር አየለ አብሸሮን፣ ዲኖ ከማልንና ማርቆስ ገነቴን የመሳሰሉት ከሁለት ሰዓት አምሥት ደቂቃ በታች ጊዜ ያስመዘገቡት ሌሎቹ የኢትዮጵያ ሯጮች በውቅቱ ይዞታ ቅድሚያ የሚኖራቸው ናቸው።

የቶኪዮው ማራቶን አሸናፊ በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከ 37 ሤኮንድ ጊዜ ኬንያዊው ማይክል ኪፕየጎ ሲሆን አራታ ፉጂዋራ ከጃፓን ሁለተኛ፤ እንዲሁም የኡጋንዳው ስቴፈን ኪፕሮቲች ሃይሌን በማስከተል ሶሥተኛ ወጥቷል። ሃይሌ ገ/ሥላሴ እስክ 35ኛው ኪሎሜትር ድረስ በጥሩ ሁኔታ ሲሮጥ በተቀረው ቁልቁለት መንገድ ላይ ግን የወገብ ሕመም እንዳስቸገረው ነው የገለጸው።

ቢሆንም የሁለት ጊዜው የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚና በዚሁ ርቀት አራቴ የዓለም ሻምፒዮን የነበረው ሃይሌ ጨርሶ ተሥፋ አልቆረጠም። ደህና ነኝ፤ ድካም የለብኝም፤ ከሁለት ሣምንት በኋላ ሌላ ማራቶን ልሮጥ እችላለሁ ነው ያለው። በሌላ በኩል የ 38 ዓመቱ ታላቅ አትሌት በሰውልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች ጊዜ ባስመዘገበባት በበርሊን ያለፈውን መስከርም ማራቶን ሩጫ ትንፋሽ አጥሮት ማቋረጡ ሲታወስና የትናንቱም ሁኔታ ሲታሰብ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ይመለሳል ብሎ ማመኑ በጣሙን የሚያዳግት ነው።

Flash-Galerie Haile Gebrselassie
ምስል AP

የሆነው ሆኖ ግን የለንደን ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለመሆን የሚያደርገው ቅጣይ ጥረት እንዲሳካለት እንመኝለታለን። በቶኪዮው ማራቶን ትናንት ሃይሌ ያሰበው ባይሆንለትም በሌላ በኩል በሴቶች አጸደ ሃብታሙና የሺ ኢሣኢያስ አንደኛና ሁለተኛ በመውጣት ታላቅ ውጤት አስመዝግበዋል። አጸደ ያሸነፈችው ግሩም በሆነ ሁለት ሰዓት ከ 25 ደቂቃ 28 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። ኬናያዊቱ ሄለና ኪሮፕ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነነት ስትፈጽም ሌላዋ አትዮጵያዊት ኢየሩሣሌም ኩማም ሰባተኛ ውጥታለች።

በሌላ ትናንት አሜሪካ-ኒው ሜክሢኮ ውስጥ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር የቀድሞዋ የ 400 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሣኒያ ሪቻርድስ-ሮስ በዚሁ ርቀት የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ 27ኛ ዓመት ልደቷን በደስታ አክብራለች። የ 27 ዓመቷ አሜሪካዊት ሩጫውን የፈጸመችው በ 50,71 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። የኬንያው ተውላጅ አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ደግሞ በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ በፍጹም የበላይንት ሲያሸንፍ በመጪው ውር የዓለም ሻምፒዮና መልሶ ባልድል እንደሚሆን ተናግሯል። ላጋት በዚህ ርቀት ሁለቴ የወርቅ መዳሊያ አሸናፊ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ጀኒፈር ሲምሰን አሸናፊ ሆናለች። በነገራችን ላይ በአዳራሹ ዝግጅት እስክ 1,500 ሜትር ርቀት ሩጫና የዝላይ ውድድሮችም ሲካሄዱ በያንዳንዱ ዲሲፕሊን አንደኛና ሁለተኛ የወጡት ስፖርተኞች በፊታችን መጋቢት ቱርክ-ኢስታምቡል ላይ በሚካሄደው ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ያሳተፋሉ። በዚህ በጀርመን የአሎሎ ውርወራው የዓለም ሻምፒዮን ዳቪድ ሽቱርል በካርልስሩኸ ውድድር አዲስ በሄራዊ ክብረ-ወሰን በማስመዘገብ ለመጪው ወር የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና ራሱን አሟሙቋል።

የ 21 ዓመቱ ወጣት አትሌት ሽቱርል አሎሎውን 21,78 ሜትር ሲወረውር ይህም ባለፈው ነሐሴ የዴጉ የዓለም ሽምፒዮና ከጣለው በ 38 ሤንቲሜትር የበለጠ መሆኑ ነው። የዓለም የአዳራሽ ውስጥ ክብረ-ወሰን በለቤት ከ 23 ዓመታት በፊት 22,66 ሜትር የጣለው አሜሪካዊ ራንዲይ ባርንስ መሆኑ ይታወቃል። ጀርመንን ካነሣን የአገሪቱ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሰንበቱን እንዳስታወቀው በርሊን የ 2018 የአውሮፓ ሻምፒዮናን ለማጋጀት ማመልከቻ ልታቀርብ ተነሳስታለች። በርሊን ቀደም ሲል የ 2009-ን የዓለም ሻምፒዮና ማስተናገዷ የሚታወስ ነው። የአውሮፓ አትሌቲክስ ማሕበር በመጪው 2013 አዘጋጁን አገር ይመርጣል።

ባለፈው አርብ ተካሂዶ በነበረ የሩሢያ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በውንዶች 1,500 ሜትር ሪጫ ዬጎር ኒኮላየቭ ሲያሸንፍ በሴቶች የለና አዛኮቫ ቀዳሚ ሆናለች። በ 5 ሺህ ሜትር ደግሞ በወንዶች አንድሬ ሣፍሮኖቭ፤ በሴቶችም ኦልጋ ጎሎቭኪና ጠንካሮቹ ነበሩ። በተቀረ በርዝመት ዝላይ ሤርጌያ ኒኮላየቭ 8 ሜትር በመዝለል አሸንፏል።

እግር ኳስ

Christiano Ronaldo
ምስል DPA

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የትናንቱ ሰንበት የክሪስቲያኖ ሮናልዶና የሊዮኔል ሜሢ ጥበብ የተመልካችን ልብ የሰወረበት ነበር። አዕምሮው ፈጥኖ የሚያሰላው የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሢ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ሲያስገባ ሮናልዶም በተረክዙ በቄንጥ ባስቆጠራት ጎል፤ ሁለቱም በየፊናቸው ለየክለባቸው ድል እንደገና ዋስትና ነበሩ። ሬያል ማድሪድ ራዮ ቫሌካኖን በሮናልዶ ብቸና ጎል 1-0 ሲረታ ባርሤሎናም አትሌቲኮ ማድሪድን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ሬያል በትናንት ድሉ በአሥር ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሤሎና በ 54 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ሶሥተኛው ቫሌናሢያ 40 ነጥቦች ሲኖሩት ለሻምፒዮንነት ከእንግዲህ ጭብጥ ዕድል አይኖረውም። በጎል አግቢነት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 29፤ እንዲሁም ሜሢ 28 አስቆጥረው ሊጋውን በግንባር-ቀደምነት ይመራሉ።

በእንግሊዝ ፕሬሚይር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ብላክበርን ሮቨርስን 3-0 በማሸነፍ አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል። ማንቼስተር ዩናይትድም በበኩሉ ግጥሚያ ትናንት ኖርዊች ሢቲይን 2-1 ሲረታ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ለማኒዩ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሁለቱ አንጋፋ ተጫዋቾች ራያን ጊግስና ፖውል ስኮልስ ነበሩ። ሶሥተኛው ቶተንሃም ሆትስፐር አርሰናልን ሁለት ለባዶ ከመራ በኋላ በአስደናቂ ሁኔታ 5-2 ተሸንፎ ከሜዳ መውጣቱ ብዙዎችን አስደንቋል።

በግጥሚያው ትልቅ ጥንካሬ ያሳየው አርሰናል አሁን አራተኛ ሲሆን ቦልተን ዎንደረርስን 3-0 ያሸነፈው ቼልሢይም በጎል ልዩንት ብቻ በመበለጥ አምሥተኛ ነው። በተቀረ ሊቨርፑል በዌምሊይ ስታዲዮም በተካሄደ የፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ካርዲፍ ሢቲይን በመከራ አሸንፎ የዘንድሮው ባለድል ሊሆን በቅቷል። ሊቨርፑል ለዋንጫ የበቃው በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት ግጥሚያ በጥቅሉ 3-2 በማሸነፍ ነው። ጨዋታው ከመደበኛ ተጨማሪ ጊዜ በኋላ ያበቃው 2-2 በሆነ ውጤት ነበር።

በኢጣሊያ ሊጋ ቀደምቱ ኤሲ ሚላንና ጁቬንቱስ 1-1 ሲለያዩ ሚላን በአንዲት ነጥብ መምራቱን ቀጥሏል። ኡዲኔዘና ላሢዮ ደግሞ አምሥት ነጥቦች ወረድ ብለው ሶሥተኛና አራተኛ ናቸው። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከኦላምፒክ ሊዮን በ4-4 ውጤት በመወሰኑ በአንዲት ነጥብ ልዩነትም ቢሆን አመራሩን ለሞንትፔሊየር ማስረከቡ ግድ ነው የሆነበት። በኔዘርላንድ ሊጋ አይንድሆፈን ፋየኖርድን 3-2 ሲያሸንፍ አመራሩን በሁለት ነጥቦች ልዩነት ከፍ ሊያደርግም በቅቷል። ለዚህም ምክንያት የሆነው የሁለተኛው ክለብ የአልክማር በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰን ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና ቤንፊካ በእኩል 49 ነጥብ ሊጋውን ይመራሉ።

ቡንደስሊጋ

Fußball Bundesliga Borussia Dortmund Hannover 96
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ያለፈው ውቅት ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ትናንት ሃኖቨርን 3-1 በማሸነፍ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ ችሏል። ያለፉትን ስባት ግጥሚያዎቹን በተከታታይ ላሸነፈው ክለብ ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው የፖላንዱ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ነበር።

ግላድባህ ከሃምቡርግ 1-1 በመለያየት ከሁለተኛ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ሻልከን 2-0 ያሸነፈው ባየርን ሙንሺን ወደ ሁለተኛው ስፍራ ከፍ ብሏል። በቅርቡ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና በቡንደስሊጋው ውድድርም ጥቂት ድክመት ታይቶበት የነበረው ባየርን በትናንት ድሉ ዋነኛው የዶርትሙንድ ተፎካካሪ በመሆን ሲቀጥል የክለቡ ፕሬዚደንት ኡሊ ሄነስ በተጫዋቾቹ በጣሙን መደሰቱን ነው የገለጸው።

«ለማረጋገጥ የምፈልገው ዛሬ በጣም ጥሩ መጫወታችንንና የበለጠም ጎል ልናስቆጥር በተቻለን እንደነበር ነው። እንደማስበው ምናልባት 4-1 ወይም 5-1 ተገቢው ውጤት በሆነ ነበር። ያም ሆነ ይህ ቡድናችን ዛሬ ከ ሀ እስክ ፐ እጅግ አርኪ ጨዋታ ነው ያሳየው»

ሻልክ አራተኛ ሲሆን ኮሎኝን 2-0 የረታው ሌቨርኩዝን ደግሞ ብሬመንን ከአምሥተኛው ቦታ መፈንቀሉ ተሳክቶለታል። ኮሎኝ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎቹ ስድሥተኛውን ሽንፈት ተከናንቦ ወደ 14ኛው ቦታ ሲያቆለቁል ሄርታ በርሊን ደግሞ የ 73 ዓመቱን አንጋፋ አሰልጣኝ ኦቶ ሬሃገልን በመቅጠር ከወደቀበት አዘቅት ለመውጣት የጣለው ትልቅ ተሥፋ ቢቀር ለጊዜው የቅዠትን ያህል ሆኖበታል።

የበርሊኑ ክለብ በአውግስቡርግ 3-0 ሲረታ ይህም በስድሥተኛ ግጥሚያው ስድሥተኛው ሽንፈት መሆኑ ነው። በዚሁ ጊዜ 14 ጎሎችም ሲቆጠሩበት በፊናው ያገባት አንዲት በቻ ናት። እናም ወደመጣበት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳይመለስ ቶሎ መንቃት ይኖርበታል። ለማንኛውም በጎል አግቢነት እያንዳንዳቸው 18 አስቆጥረው ሊጋውን የሚመሩት አሁንም የባየርኑ ማሪዮ ጎሜስና የሻልከው ክላስ-ያን-ሁንቴላር ናቸው።

በተረፈ በዚህ ሣምንት አጋማሽ በዓለምአቀፍ ደረጃ በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከልም ጀርመን ከፈረንሣይ፤ እንግሊዝ ከኔዘርላንድ፤ ፖርቱጋል ከፖላንድ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ ክቬኔዙዌላና ኢጣሊያ ከዩ ኤስ አሜሪካ በተለየ ትኩረት የሚጠበቁት ናቸው። ደቡብ ኮሪያ ትናንት ቀደም ብላ ባካሄድችው የወዳጅነት ግጥሚያ ኡዝቤኪስታንን 4-2 ስትረታ የዘንድሮዋ የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊ ዛምቢያ በበኩሏ ተጫዋቾቿና ለማሳረፍ ስትል ከጋቡን የነበራትን ግጥሚያ መሰረዟን አስታውቃለች።

ቴኒስ

Flash-Galerie Schatten Tennis
ምስል AP

የሁንጋሪያዋ ቲሜያ ባቦስ ትናንት በሜክሢኮ የሞንቴሬይ-ኦፕን የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ የሩሜኒያ ተጋጣሚዋን አሌክሣንድራ ካዳንቱን 6-4, 6-4 በሆነ ውጤት አሸንፋለች። በሜንፊስ ፍጻሜ ደግሞ የአውስትሪያው ዩርግን ሜልሰር የካናዳውን ሚሎሽ ራኦኒክን አሸንፏል። ከዚሁ ሌላ የስፓኝ ተወላጆች እርስበርስ በተጋጠሙበት በብዌኖስ አይርስ ኦፕን ዴቪድ ፌሬር ኒኮላስ አልማግሮን አሸንፏል። በማርሤይ ዓለምአቀፍ ፍጻሜም የአርጄንቲናው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮ ፈረንሣዊውን ሚሼል ሊዮድራን በሁለት ምድብ ጨዋታ ለመርታት ችሏል።

ቢስክሌት

Tour de France 2008 8. Etappe Mark Cavendish
ምስል AP

በቢስክሌት እሽቅድድም የብሪታኒያው የዓለም ሻምፒዮን ማርክ ካቬንዲሽ ትናንት በኩም-ብራስልስ ደርሶ መልስ የ 195 ኪሎሜትር ውድድር አሸናፊ ሆኗል። ለካቬንዲሽ ይሄው ዘንድሮ ክካታር-ቱውር ሁለት እሽቅድድሞች በኋላ ሶሥተኛው ድል መሆኑ ነው። በዚያው በቤልጂግ በጌንት አካባቢ በተካሄደ የ 200 ኪሎሜትር እሽቅድድም ደግሞ የአገሪቱ ተወላጅ ሤፕ ፋንማርከ ባልድል ሆኗል። በቡጢ ለማጠቃለል ሰንበቱን ካርዲፍ ላይ በተካሄደ የቡጢ ግጥሚያ ዮዌልሱ ናታን ክሌቨርሊይ የአሜሪካ ተፎካካሪውን ቶሚያ ካርፔንሲይን በፍጹም የበላይነት በማሸነፍ የዓለም ቡጢ ማሕበር የመለስተኛ ከባድ ሚዛን ክብሩን መልሶ ሊይዝ በቅቷል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ