1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሣምንቱ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 20 2006

በሣምንቱ መገባደጃ ላይ የተከናወኑ ዓበይት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች በተለይም የእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ዋነኛ ትኩረታችን ይሆናል። የጀርመኑ ቡንደስሊጋ እና የበርሊኑ ማራቶን ውጤቶችን የሚመለከቱ ዘገባዎችንም አጠናቅረናል።

https://p.dw.com/p/19rup
BRAUNSCHWEIG, DEUTSCHLAND. FUSSBALL -29.09.13, Eintracht Braunschweig vs VfB Stuttgart, 1. Bundesliga, Saison 2013-2014. Bild zeigt:Ibrahima Traore (VfB Stuttgart) und Ken Reichel (Eintracht Braunschweig)
ምስል picture alliance/CITYPRESS 24

ትናንት እና ከትናንት በስተያ በተደረጉ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች እንደ ሊቨርፑል በለስ የቀናው ቡድን የለም። በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል የመጨረሻ ደረጃ የሚገኘው ሰንደርላንድን 3 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ጉድ አድርጎታል። ለሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ግብ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፍው ዳንኤል ስቱሬጅ ነበር። ዳንኤል ከማዕዘን በኩል ከስቴቨን ጄራርድ የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ ሊያሳርፍ ችሏል። ይህች ግብ ግን በድጋሚ በዝግታ ስትታይ ዳንኤል በጭንቅላት አስመስሎ ግቧን ከመሬት በማላተም ያስቆጠረው በቀኝ ክርኑ አስደግፎ ነበር። ሊቨርፑሎች ሁለተኛዋን ግብ አግኝተው ደስታቸው ወደ ጮቤ ለመቀየር ከስምንት ደቂቃ በላይ መጠበቅ አልነበረባቸውም። የመጀመሪዋን ግብ ያስቆጠረው ዳንኤል ስቱሬጅ 36ኛው ደቂቃ ላይ የሰንደርላንድ ተከላካዮችን አታሎ ከግቡ በስተግራ በኩል ተመቻችቶ ይጠብቀው ለነበረው ሉዊስ ሱዋሬዝ የላካትን ኳስ ሱዋሬዝ በቀኝ እግሩ ከመረብ እንድታርፍ አድርጓል። ከእረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ ላይ የሰንደርላንዱ ኤማኑኤል ጊያቼሪኒ ለቡድኑ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፤ መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ ሲቀር ሉዊስ ሱዋሬዝ ለሊቨርፑል ሶስተኛዋን ለእራሱ ደግሞ ሁለተኛዋን ግብ በግራ እግሩ ሊያስቆጥር ችሏል። አሁንም ኳሷን አመቻችቶ የላከለት ዳንኤል ስቱሬጅ ነበር። ዳንኤል በትናንቱ ጨዋታ ኮከብ ሆኖ ነበር ያመሸው።

ሊቨርፑል
ሊቨርፑልምስል Getty Images

ትናንት ኖርዊች ስቶክ ሲቲን በብሪታንያ ስታዲየም 1 ለባዶ አሸንፏል። ከትናንት በስተያ 6 የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ በርካታ ግቦች የተቆጠሩት በአስቶን ቪላ እና ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ ላይ ነበር። አስቶን ቪላ ተቀናቃኙን 3 ለ2 ሊረታ ችሏል። ሳውዝ ሐምተን ክሪስታል ፓላስን 2 ለምንም ሲያሰናብት፣ ሁል ሲቲ ዌስት ሐም ዩናይትድን 1 ለባዶ ረቷል። ካርዲስ ሲቲ ፉልሀምን፣ አርሰናል ስዋንሲን እንዲሁም ዌስት ብሮሚች ማንቸስተር ዩናይትድን 2 ለ አንድ አሸንፈዋል። ቸልሲ ከቶትንሀም ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ቸልሲ እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ ሲመራ ቆይቶ ቡድኑን የታደገው አንጋፋው ጆን ቴሪ ነበር። የማታ ማታ ግን ቸልሲ ነጥብ መጣል ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ተጫዋቹ ፈርናንዶ ቶሬስን በቀይ ሊያጣ ችሏል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእስካሁኑ ግጥሚያ አርሰናል ሊቨርፑልን በሁለት ነጥብ አስከትሎ የደረጃ ሠንጠረዡን ሲመራ፤ ቶትንሐም በ13 ነጥብ ከሊቨርፑል ጋር እኩል ሆኖ በግብ ልዩነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቸልሲ ከአርሰናል በ4፣ ከሊቨርፑልና ቶትንሀም ደግሞ በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ማንቸስተር ሲቲ በ10 ነጥብ ስድስተኛ ማንቸስተር ዩናይትድ በ7 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። 16ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ የተጠጋው ኒውካስትልም በነጥብ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር እኩል ሲሆን ልዩነቱ የግብ ነው። በወራጅ ቀጣናው የመጨረሻው አውራ ሆኖ በአንድ ነጥብ የሚሰቃየው ሰንደርላንድ ትናንት በሊቨርፑል በደረሰበት ቅጣት የግብ እዳዎቹ ወደ 10 አሻቅበዋል።

አሁን ደግሞ ወደ ጀርመኑ ቡንደስሊጋ እንሻገርና ኢትጵያውያን ተሳተፉበትን የበርሊኑ ማራቶን እናስከትላለን። በጀርመኑ ቡንደስሊጋ ኃያላኑ ቡድናት አሁንም ጥንካሬያቸውን እያሳዩ ነው። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና ባየርን ሙንሽን በግብ ልዩነት እኩል ነጥብ ይዘው የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተናንቀዋል። የደረጃ ሠንጠረዡን እንመለስበታልን።

Fussball UEFA Champions League SSC Napoli - Borussia Dortmund
የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕምስል picture-alliance/dpa

ትናንት ቬርደር ብሬመን ከኑርንበርግ ጋር ተፋልሞ 3 ለ3 በሆነ ውጤት ነጥብ ሊጋራ ችሏል። ሽቱትጋርት የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው አይንራትህክት ብራውንሽቫይግን 4 ለባዶ አሸክሞ ባለህበት እርገጥ ብሎታል። ከትናንት በስትያም እንዲሁ ኃያሉ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ ከታች ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ፍራይቡርግን 5 ለ ምንም በሆነ ልዩነት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል። የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቡድኑ የተሻለ ተጫውቶ የተሻለ ውጤት እንዳስመዘገበ ገልጸዋል።

«ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ነው ድንቅ ጨዋታ ያደረግነው። ሰው ሳይቀነስባቸው እስከ 44ኛው ደቂቃ ጭምር ኳስ ወደፊት እየገፋን የተሻለ ነው ያጠቃነው። ከዛ ደግሞ ፍራይቡርጎች ዕድል ጠመመችባቸውና ፍፁም ቅጣት ምት አገኘን፤ አንድ ተጫዋቻቸውም ከሜዳ በቀይ ተሰናበተ። ከእዛ በቃ ማንም ሊያቆመን አልቻለም ማለት እችላለሁ። ሁሉም ሠላም ነው፤ 5 ለ 0 ድንቅ ውጤት ነው።»

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ማርኮ ሮይስ ለዶርትሙንድ የመጀመሪያዋን ግብ በጨዋታ ሁለተኛዋን ደግሞ ፋሎ ዲያግኔ በሰራው ጥፋት በተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ቡድኑ 2 ለዜሮ እየመራ እረፍት ሊወጡ ችለዋል። ከእረፍት መልስ ደግሞ ሮበት ሌቫንዶቭስኪ በ58ኛው እና 70ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን፣ እንዲሁም ጃኩብ ብላስቺኮቭስኪ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር ዶርትሙንዶች በሰፊ ልዩነት ለማሸነፍ ተሳክቶላቸዋል።

የዶርትሙንዱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ሌላኛው ኃያል ባየር ሙንሽን በደረጃ ሠንጠረዡ በ11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ዎልፍስቡርግን 1 ለባዶ በሆነ ጠባብ ልዩነት ሊያሸንፍ ችሏል። ለሙንሽነሮች ብቸኛዋን ግብ በ63ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ባሳለፍነው ረቡዕ በተካሄደው የጀርመን እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ ግጥሚያ ላይ ባየርን ሙንሽን ሐኖቨርን 4 ለ1 ሲቀጣ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ ቶማስ ሙለር ነበር። ቶማስ የተቀናቃኙ ዎልፍስቡርግን ጠንካራ የመከላከል ብቃት ሳያደንቅ አላለፈም።

የማራቶን ሯጮች
የማራቶን ሯጮችምስል Fotolia/ruigsantos

«አሰልጣኛችንም ቢሆን እላይ ያሉት ሶስቱ ድንቅ ቡድኖች ከሚያደርጉትን ፈጣን አጨዋወታ አንፃር ከምንም በላይ ማሸነፉን የሚፈልግ ነው የሚመስለኝ። ማየት እንደሚቻለውም ዎልፍስቡርጎች ተጠናክረው ነው የገቡት። ጨዋታው ከባድ ነበር። »

ቅዳሜ ዕለት እዚህ ጀርመን ከተደረጉ ግጥሚያዎች መካከል የባየር ሌቨርኩሰን እና የሐኖቨርም ጨዋታ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። ሌቨርኩሰን ሐኖቨርን 2 ለባዶ ሊረታ ችሏል። የባየር ሌቨርኩሰኑ አንበል ሲሞን ሮልፌስ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራትን ግብ እንደመንደርደሪያ በመውሰድ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጠው አዲሱ ተጫዋች ሲድኒ ሳም በ37ኛው ደቂቃ ላይ ለቡድኑ ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

«በርካታ ዕድሎችን አምክነናል። በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የተሻለ ብንጫወትም፤ ብዙ የተሻለ ማድረግ፣ የተወሰኑ ዕድሎችንም መጠቀም ነበረብን። እንዲያም ሆኖ ግን ደህና ነው።»

በደረጃ ሰንጠረዡ 19 ነጥቦችን ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየርን ሙንሽን በ18 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ከተቆናጠጠው ባየር ሌቨርኩሰን ጋር የፊታችን ቅዳሜ የሚያደርገው ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃል። የደረጃ ሰንጠረዡን ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከባየር ሙንሽን በእኩል ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት እየመራ ይገኛል። ሐኖቨር 96 የተባለው ቡድን በ12 ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ነው።

ትናንት በበርሊን በተካሄደው የማራቶን ውድድር ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ሊያስመዘግብ ችሏል። ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት በማራቶን ኃያልነታቸውን አሳይተዋል። ዊልሰን ኪፕሳንግ 40ኛውን የበርሊኑ ማራቶን በአንደኝነት ያጠናቀቀው በ 2 ሠዓት ከ 3 ደቂቃ ከ23 ሰኮንድ ሲሆን፤ በሀገሩ ተወላጅ ፓትሪክ ማካዉ እጎአ በ2011 የተያዘውን ክብረወሰን በ15 ሰከንድ ልዩነት አሻሽሏል።

ዊልሰን 40ኛውን የበርሊን ማራቶን ባሸነፈበት ወቅት
ዊልሰን 40ኛውን የበርሊን ማራቶን ባሸነፈበት ወቅትምስል picture-alliance/dpa

በማራቶን ሲወዳደር ሁለተኛ ጊዜው የሆነው ኢሊዉድ ኪፕቾግ የተሰኘው ሌላኛው ኬንያዊ በ2 ሠዓት ከ4 ደቂቃ ከ5 ሰከንድ ዊልሰንን በመከተል ሁለተኛ ለመውጣት ችሏል። ጂኦፍሬይ ኪፕሳንግ በሁለተኛነት ድል ካስመዘገበው የሀገሩ ልጅ ኢሊዉድ ሁለት ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ሶስተኛ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊው ሲሳይ ጂሳ 2 ሠዓት ከ12 ደቂቃ ከ17 ሠከንድ በመግባት 10ኛ መውጣቱን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። በትናንቱ ድል ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ 40,000ዩሩ ተሸላሚ ሲሆን፤ ክብረወሰን በመስበሩ ደግሞ ተጨማሪ 50,000 ዩሮ ይጠብቀዋል።

በበርሊኑ የሴቶች ማራቶን በተመሳሳይ ኬንያውያን ጥንካሬያቸውን በማሳየት ጀርመናዊቷ ኢሪና ሚኪቴንኮን ሶስተኛ ከመሀከላቸው በማስገባት ከአንድ እስከ አራተኛ ተከታትለው ለማሸነፍ ችለዋል። ቀደም ሲልም ውድድሩን በአንደኝነት ልታሸንፍ እንደምትችል የተገመተላት ኬንያዊቷ ፍሎሬንስ ኪፕላጋት በ2 ሠዓት ከ21 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ አንደኛ ስትወጣ የቀድሞ ሠዓቷ በአንድ ደቂቃ ተኩል መዘግየቱ ታውቋል። ሻሮን ቼሮፕ በ2 ሠዓት ከ22 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ሁለተኛ ሌላኛዋ ኬንያዊት ሄላህ ኪሮፕ በ2 ሠዓት ከ28 ደቂቃ ከ02 ሠከንድ በአራተኛነት ለማጠናቀቅ ችላለች።

የበርሊኑ ማራቶንን ትናንት ያስጀመረው በበርሊን ማራቶን የአራት ጊዜያት አሸናፊው እና የሁለት ጊዜ ባለክብር ወሰኑ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነበር። በበርሊን ማራቶን ከእዚህ ቀደም ክብር ወሰን ያስመዘገቡ ስምንቱም ባለድሎች ከ119 ሀገራት የተውጣጡት 41, 120 ተወዳዳሪዎች ረጫቸውን ከመጀመራቸው በፊት በቦታው ተገንተው እንደነበር ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ