1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሣምንቱ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2001

በአውሮፓ የክለቦች እግር ኳስ ሻምፒዮና አስደናቂ እስገራሚም ውጤት መታየቱን እንደቀጠለ ነው። በሻንግሃይ የቴኒስ ማስተርስ፤ በቶኪዮም የማራቶን ሩጫ ተካሂዷል። በፊታችን ዕሑድ ደግሞ ሞንቴ ካርሎ ላይ የዓመቱ የዓለም አትሌቶች ይመረጣሉ።

https://p.dw.com/p/FwdV
ብሬመን በጎል ደስታ
ብሬመን በጎል ደስታምስል AP

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኤፍ-ሢ.ቸልሢይ የመጨረሻውን ቡድን ብሮምዊች አልቢዮንን 3-0 ሲረታ የቅርብ ተፎካካሪው ሊቨርፑልም ቦልተን ወንደረርስን 2-0 አሸንፏል። ለቼልሢይ ከሶሥት ሁለቱን ግቦች በማስቆጠር የድል ዋስትና የሆነው ፕሬሚየር ሊጉን በጎል አግቢነት የሚመራው የፈረንሣይ ተጫዋች ኒኮላይ አኔልካ ነበር። አርሰናል በአንጻሩ በኤስተን ቪላ ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-0 በመሽነፍ የሶሥተኝቱን ቦታ ለማንቼስተር ዩናይትድ አስረክቧል።
ዘንድሮ ደከም ብሎ ከጀመረ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ላይ እያሻቀበ የመጣው ሻምፒዮን ማንቼስተር ዩናይትድ ስቶክ ሢቲይን በለየለት 5-0 ውጤት ሲያሸንፍ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው የፖርቱጋሉ ኮከብና ያለፈው ውድድር ወቅት የዓለም ድንቅ ተጫዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ቼልሢይ በ 32 ነጥቦች ሊጋውን በቀደምትነት ይመራል። ኤፍ.ሢ.ሊቨርፑል በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በጎል ብቻ በመበለጥ ሁለተኛ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በ 24 ነጥብ ሶሥተኛ ሲሆን አርሰናልና ኤስተን ቪላ ደግሞ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብለው ይከተላሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሰንበቱ ከሁሉም በላይ ለኤፍ.ሢ.ባርሤሎና አስደሳች ሆኖ አልፏል። ለምን? ከአራት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ አንዱም የሰንበት ግጥሚያውን ሊያሸንፍ አለመቻሉ በሶሥት ነጥብ ልዩነት የብቻ አመራሩን አስተማማኝ እንዲያደርግ ጥሩ አጋጣሚ ነው የሆነው። ባርሤሎና ሁዌልቫን 2-0 ሲረታ ሬያል ማድሪድና ቫሌንሢያ የሣምንቱ ተሽናፊዎች ናቸው። ቪላርሬያል ደግሞ ከማላጋ ጋር ከእኩል-ለእኩል ከሆነ ውጤት ሊያልፍ አልቻለም። ከፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ 11ኛ ግጥሚያ በኋላ ባርሤሎና በ 28 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ቪላርሬያል በ 25 ሁለተኛ ነው። ተከታዮቹ ቫሌንሢያና ሬያል ደግሞ እኩል 23 ነጥብ አላቸው። በጎል አግቢነት ሊጋውን የሚመራው አሁንም 13 ግቦችን ያስቆጠረው የካሜሩን ኮከብ ሣሙዔል ኤቶ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዘንድሮ ጉድ ያሰኘው ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የወጣ ቡድን ሁፈንሃይም አሁንም በአስደናቂ አጨዋወት የሊጋውን አመራር መሻማቱን እንደቀጠለ ነው። የሣምንቱ ተሽናፊ ከሁሉም በላይ ሻምፒዮኑ ባየርን ሙንሺን ነበር ለማለት ይቻላል። ቡድኑ ከመንሸን ግላድባህ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2-0 ከመራ በኋላ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበት እኩል ለእኩል መውጣቱ አመራሩን እንዳይቀርብ መሰናክል ሆኖበታል። በአንጻሩ ሰንበቱን እፎይ ሊል የበቃው ባለፉት ሣምንታት ብዙ ድክመት የታየበት ቬርደር ብሬመን ነው። ቬርደር ባለፈው ምሽት ኮሎኝን 3-1 ሲያሽንፍ በዚሁ ከ 11 ወደ ሰባተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። ውጤቱ አሠልጣኙ ቶማስ ሻፍ እንዳለው ተጫዋቾቹ እንደገና በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ እጅግ ጠቃሚ ነው።

“የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋችን እጅግ የሚያረካን ጉዳይ ነው። ውጤቱ በጣም ጠቃሚ ነበር። ለምንፈልገው የወደፊት ዕርምጃ ይበልጥ ጥንካሬ፤ ይበልጥ በራስ መተማመን እንዲኖረን የሚያደርግ ነው። ሆኖም በጨዋታችን የበለጠ መጠናከር እንዳለብን እናውቃለን። ቡድኑም በወቅቱ ይሄው ፍላጎት እንዳለው በማሣየት ላይ ነው ብዬ አምናለሁ”

በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና በብሄራዊው ሊጋ ውድድር ባለፉት ጊዜያት ቀድሞ የተለመደ ጥንካሬውን ያጣው ቬርደር በእውነት በማገገም ላይ መሆኑን ሣምንት ከሃምቡርግ በሚያካሂደው ግጥሚያ ጠብቆ መታዘቡ ይመረጣል። በሌላ በኩል ሌቨርኩዝን ሻልከን ለዚያውም ወደ መጨረሻው በአሥር ሰው ብቻ በመጫወት 2-1 ሲያሸንፍ አመራሩ ላይ መቆናጠጡን ቀጥሏል። ሆኖም የዘንድሮው አስደናቂ ቡድን ሆፈንሃይም ቮልፍስቡርግን በግሩም ጨዋታ 3-2 ሲረታ በተመሳሳይ ነጥብ አመራሩን እየተሻማ ነው። ከሌቨርኩዝን የሚነጥለው የጎል ልዩነት ብቻ ነው። ሆኖም አሠልጣኙ ራልፍ ራንግኒክ የመንደሩን ክለብ ድል በዕድል ጭምር የተገኘ ነው ብሎታል።

“ድሉ የዕድልም ነበር። ግን ጨዋታው በአጠቃላይ ሲታይ ይበልጥ በማጥቃታችን ማሽነፋችን በመጨረሻ ተገቢ ነው ለማለት እወዳለሁ። እና በዛሬው ድል ጥቂት ለየት ያለ ቢሆንም ቀደም እንዳሉት ሁሉ በጣም ነው የምንደሰተው”

የሆነው ሆኖ ቀደም ሲል ማንም ያልጠበቀው የዚህ ቡድን አጨዋወት ተመልካችን በጣሙን የሚማርክ ነው። ፍጥነት፣ የረቀቀ ቴክኒክ፣ የሰመረ የቡድን አጨዋወት ሁሉም በወቅቱ የመንደሩ ቡድን መለያ ነው። ጥያቄው በተለይ በፈጣን አጨዋወቱ ሳይዳከም ክረምቱን ይዘልቃል ወይ ይሆናል።

ወደ ኢጣሊያ አንደኛ ዲቪዚዮን ሤሪያ-አ. እንሻገርና የሚላን ከተማ ተፎካካሪ ክለቦች ኢንተርና ኤ.ሢ.ሚላን በሰንበቱ ድላቸው አመራሩን የብቻቸው አድርገውታል። ኢንተር ፓሌርሞን 2-0 ሲረታ ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ ቺየቮን 1-0 አሸንፏል። በአንዲት ነጥብ ልዩነት አንደኛና ሁለተኛ ናቸው። ቀደምቱ ኢንተር በፊታችን ቅዳሜ ጁቬንቱስን መሰል ከባድ ተጋጣሚ ይጠብቀዋል። ጁቬንቱስ ጌኖዋን 4-1 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን ናፖሊና ላሢዮ በቅርብ ይከተላሉ። የሚያሳዝን ሆኖ ባለፈው የውድድር ወቅት ሻምፒዮናውን በሁለተኝነት የፈጸመው ሮማ ምንም እንኳ ላሢዮን 1-0 ቢረታም የሊጋው መጨረሻ 17ኛ ነው። ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳያቆለቁል በጣሙን ያሰጋዋል።

በተረፈ በፈረንሣይ ኦላምፒክ ሊዮን ቦርዶን 2-1 በመሽኘት አመራሩን በሰባት ነጥብ ልዩነት ሲያሰፋ በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አያክስ አምስተርዳም አይንድሆፈንን 4-1 በማሽነፍ ቁንጮነቱን ወስዷል። ብሬዳ በእኩል ነጥብ ሆኖም በጎል ልዩነት ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው ግሮኒንገን ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ብዙም ታዋቂ ያልሆነው ሌክሶስ በጥሩ አጀማመሩ በመግፋት አሁንም በአመራሩ ቀጥሏል። የቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች የሰንበት ውድድር ሂደት ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ነበር።

በአፍሪቃ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ የዘንድሮው የዋንጫ ባለቤት የካይሮው አል-አህሊ ሆኗል። አል አህሊ ለድል የበቃው የፍጻሜ ተጋጣሚውን የካሜሩኑን ኮተን ስፖርት ጋሩዋ በአጠቃላይ ውጤት 4-2 ከረታ በኋላ ነው። የግብጹ ክለብ የአፍሪቃን የክለቦች ሻምፒዮና በጠቅላላው ለስድሥተኛ ጊዜ ሲያሽንፍ ባለፉት አራት ፍጻሜዎች በተከታታይ ተሳታፊ ነበር። አል-አህሊ ትናንት በመልሱ ጨዋታ ከጋሩዋ 2-2 ቢለያይም ከሁለት ሣምንት በፊት በመጀመሪያው ግጥሚያ 2-0 ማሽነፉ አይዘነጋም። የአፍሪቃን እግር ኳስ ካነሣን አይቀር የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ለሕዳር ባወጣው የማዕርግ ተዋረድ ካሜሩንን አንደኛ አድርጎ አስቀምጧል። ሁለተኛ ግብጽ፣ ሶሥተኛ ናይጄሪያ፣ አራተኛ ጋና ስትሆን አይቮሪ ኮስት ደግሞ በአምስተኝነት ተደልድላለች። ኢትዮጵያ በ 52 ሃገራት ንጽጽር 29ኛ፤ ኤርትራ 40ኛ!

አትሌቲክስ

ትናንት ጃፓን ውስጥ ተካሂዶ በነበረ የቶኪዮ ዓለምአቀፍ የሴቶች ማራቶን ሩጫ የአገሪቱ ተወላጅ ዮሺሚ ኦዛኪ አሸናፊ ሆናለች። ኦዛኪ ለድል የበቃችው ታሸንፋለች ተብላ ስትጥበቅ የቆየችውን ሌላ ጃፓናዊት ዮኮ ሺቡዊን 38ኛው ኪሎሜትር ላይ ቀድማ በማምለጥ ነው። ጃፓናውያኑ ከአንድ እስከ ሁለት ሲከታተሉ የብሪታኒያዋ ማራ ያማኡቺ ደግሞ ሶሥተኛ ሆናለች። ከአፍሪቃ ተወዳዳሪዎች ኬንያዊቱ ሣሊና ኮስጋይ አምስተኛ ስትወጣ ደራርቱ ቱሉ ደግሞ ሩጫውን በዘጠነኝነት ፈጽማለች።

ከዚህ ሌላ በአትሌቲክሱ ዓለም በጉጉት የሚጠበቀው የዚህ ዓመት ድንቅ አትሌቶች ምርጫና የሽልማት ሥነ-ሥርዓት በፊታችን ዕሑድ ሞንቴ ካርሎ ላይ ይካሄዳል። የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር እንዳስታወቀው ለምርጫ ከሚቀርቡት ሶሥት ወንዶች መካከል ከኢትዮጵያ ቀነኒሣ በቀለ፤ በሴቶቹም ፉክክር ጥሩነሽ ዲባባ ተፎካካሪዎች ናቸው። ለኢትዮጵያ በዚህ ከፍተኛ ደረጃ ሁለት አትሌቶች ለምርጫ መድረሳቸው ራሱ ከወዲሁ ታላቅ ክብር ነው።

የዘንድሮው የዘንድሮ ነው፤ ቀነኒሣ በቀለ ወደፊት አራት ዓመታት ሻገር ብሎ በመጪው የለንደን ኦሎምፒክ በምን ርቀት እንደሚወዳደር ከወዲሁ ማቅማማት ይዟል። ቀነኒሣ በለንደን ኦሎምፒክ በአሥር ሺህ ሜትር ወይም በማራቶን ሩጫ ሊወዳደር እንደሚችል ትናንት በኔዘርላንድ ኒይሜገን አመልክቷል። ሆኖም አያይዞ እንደገለጸው ወደ መንገዱ ሩጫ መቼ እንደሚያዘነብል ገና አልወሰነም። ቀነኒሣና ሃይሌ ገ/ሥላሴ በለንደን ኦሎምፒክ አብረው ማራቶን ቢሮጡ ለውድድሩ የተለየ ድምቀት እንደሚሰጡ መገመት አያዳግትም። ሆኖም አራት ዓመት ረጅም ጊዜ ነው። ብዙ ነገር ሊለወጥ ይችላል። ለማንኛውም ቀነኒሣ አርቆ መመልከቱ ሊደነቅ የሚገባው ነው።

ቴኒስ

የሰርቢያው ተወላጅ ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት ሻንግሃይ ላይ በተካሄደው የማስተርስ ፍጻሜ ግጥሚያ ሩሢያዊውን ኒኮላይ ዳቪዴንኮን 6-1, 7-5 በሆነ በለየለት ውጤት በማሽነፍ በዓመቱ መገባደጃ ታላቅ ድል ተጎናጽፏል። ለሻንግሃይ የትናንቱ ፍጻሜ ከአራት ዓመታት በኋላ የመጨረሻው የማስተርስ ዝግጅት ሲሆን ለዝነኛው ተጫዋች ለሮጀር ፌደረር ግንባር-ቀደምነትም ምናልባት የፍጻሜው መጀመሪያ ሣይሆን አልቀረም። የስዊሱ ተወላጅ በዚህ ዓመት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ሁሉም ነገር አልተዋጣለትም። ፌደረር ከውድድሩ ቀደም ብሎ ሲሰናበት መጪው ዓመት ቀላል የሚሆንለት አይመስልም። በተቀረ ብርቱ ተፎካካሪው ራፋኤል ናዳል ደግሞ በቁስለት ሳቢያ በውድድሩ ሳይሳተፍ ቀርቷል።

በእግር ኳስ የጀመርነውን ዘገባ በእግር ኳስ ለማጠቃለል በፊታችን ረቡዕ በዓለም ዙሪያ በርከት ያሉ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁም አንዱ በርሊን ላይ በጀርመንና በእንግሊዝ መካከል የሚካሄደው ሲሆን ጨዋታው የወዳጅነት ቢሆንም እንደተለመደው የክብር ትግል የሚታይበት እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው። ሌላው የዓለምን ትኩረት የሚስበው ግጥሚያ ግላስጎው ላይ በስኮትላንድና በአርጄንቲና መካከል የሚደረገው እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። እርግጥ ምክንያቱ ጨዋታው አይደለም።
በተለየ የእግር ኳስ ጥበቡ ዓለምን የማረከው የአንዴው ኳስ ፊደሉ ዲየጎ አርማንዶ ማራዶና፤ የአገሩሕዝብ አቆላምጦ እንደሚጠራው ዲየጊቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የአርጄንቲናን ብሄራዊ ቡድን በአሠልጣኝነት የሚመራ መሆኑ ነው። ማራዶና ገና ከወዲሁ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ድል መቀዳጀት ግቡ መሆኑን ተናግሯል። ተጫዋቾቹ ጥበቡንና የኳስ ተውኔቱን ሊወርሱ ከቻሉ ምኞቱ ዕውን የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። በተረፈ ከተቀሩት የፊታችን ረቡዕ የወዳጅነት ግጥሚያዎች መካክል ፈረንሣይ ከኡሩጉዋይ፤ ኔዘርላንድ ከስዊድን፤ እንዲሁም ግሪክ ከኢጣሊያ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።