1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥነ-ግጥምና ሥነ-ጥበብ ትስስር

ሐሙስ፣ ሰኔ 26 2006

«ሃሳብ አልጠል ሲል፤ በልብ የያዙት፤ በጭንቅላት የሚጉላሉት፤ በቀለም ቡሩሽ፤ በስዕል መልክ አልወጣ ሲል፤ ቃላት ቋጥሮ ግጥምን የመደርደር ባህላችን የቆየና የሚኖር ነዉ። የሥነ-ጥበብ ቤተሰቡ ሥነ-ግጥም በከፍተኛ ደስታ እና ኃዘን እንዲሁም ፍቅር ግዜ ሃሳባችንን በቃላት አምቀን የምንተነፍስበት ዘዴ ነዉ» ይሉናል፤ ሰዓሊና ገጣሚ እሸቱ ጥሩነህ

https://p.dw.com/p/1CUkt
Kunst Festival in Addis Abeba
ምስል DW/A. T. Hahn

የኢትዮጵያ ሰዓልያን እና ቀራፅያን ማኅበር ከፑሽኪን ማዕከል ጋር በመተባበር ሥነ-ግጣምያን እና ሰዓልያን ያላቸዉን የተቀራረበ ኪነ-ጥበባዊ ሥራ ተመልክተዋል። የኢትዮጵያ የሰዓልያን እና ቀራፅያን ማኅበር በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ርዕሶች ላይ ታዳሚን በማሰባሰብ፤ በየወሩ በሚያዘጋጀዉ እና ትናንት ምሽት ለአስረኛ ግዜ በተካሄደዉ የኪነ-ጥበባት መድረክ ላይ በተለይ የታዋቂዉ ገጣሚና ሰዓሊ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ስራዎች በዋነኝነት የቀረቡ ነበሩ።

የኢትዮጵያ የሰዓልያን እና ቀራፅያን ማህበር በየወሩ አንድ ግዜ የሚያዘጋጀዉ ኪነ- ጥበብን ከተመረኮዙ ሥራዎች መካከል ትናንት ባዘጋጀዉ አስረኛ ዝግጅቱ ላይ ሰዓልያን ከሥነ- ግጥም ጋር ያላቸዉን የተለየ ኪነ-ጥበባዊ ቅርበት ተመልክቶአል። በርካታ ሰዓልያን ከሥነ-ጥበባዊ ሥራዎቻቸዉ ባሻገር እንደ ስዕሉ ሁሉ የታመቀ ሃሳብን በምናባቸዉ ቀርፀዉ በግጥም መልክ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል። ለዚህም በቀዳሚነት ሁለገብ ጥበበኛዉ ገብረክርስቶስ ደስታ ይታወሳል። ትናንት የሰዓልያን እና የገጣምያን ሥራ በተወሳበት መድረክ ላይ የገጣሚና ሰዓሊ የገብረክርስቶስ ደስታ ሥራዎች «በኢላይትመንት የስዕል አካዳሚ ዳይሬክተር፤ በሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ቀርቦ ነበር።
ግጥምና ሥነ- ጥበብ ግንኙነታቸዉ ምን ላይ ይሆን? በሩስያ የሥነ-ጥበብ ከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት የኢንላይትመንት የስዕል አካዳሚ ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ ስዕልና ስነ- ጥበብ መግለጫቸዉ ይለያይ እንጂ፤ በአዕምሮ ዉስጥ ሲቀረፁ ይዘታቸዉ አንድ ነዉ ሲሉ በስፋት አስረድተዋል። በኢትዮጵያ የሥነ- ጥበብ ትምርት ቤት መምህር የሆኑት ሰዓሊ በቀለ መኮንን፤ የኢትዮጵያ የስዓሊና የቀራፅያን ማኅበር ባዘጋጀዉ መድረክ ላይ የሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ኃብተማርያም ሥራዎችን አቅርበዋል። በዚሁ መድረክ ላይ ሌላዋ ተጋባዥ ሰዓሊና የሥነ-ጽሑፍ ሰዉ ወጣት ምህረት ከበደ፤ በአሁኑ ግዜ በዩኤስ አሜሪካ የምትኖር ታዋቂዋን ገጣሚና ሰዓሊ የከበደች ተክለአብ ሥራዎችን ይዛ ቀርባ ነበር። ወደ አስር አመታት ግድም በሶማልያ ዉስጥ እስር ላይ የነበረችዉ ሰዓሊ ግጥሞችዋን የፃፈቻቸዉ በእስር ላይ ሆና እንደነበር ተነግሮአል። ወጣት ምህረት ከበደ በዚህ መድረክ ይዛዉ ከቀረበችዉ የሰዓሊ ከበደች ተክለአብ ግጥሞች መካከል የዝናብ ጠብታ የሚለዉ ይገኝበታል።
ሥነ- ጥበብ፤ ሙዚቃ፤ ሥነ-ጽሑፍ የመሳሰሉ ጥበባዊ ስራዎች የተሳሰሩ ናቸዉ የሚሉት የኢላይትመንት የስዕል አካዳሚ ዳይሪክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በተለይ ደግሞ ሥዕልና ሥነ- ግጥም የኅብረተሰብን ዕምቅ ሃሳብ መግለጫ መሆናቸዉን ይናገራሉ። በስዕሎቻቸዉ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሥነ- ግጥሞችንም በመጻፋቸዉ የሚታወቁት ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ በዝግጅቱ ላይ ካቀረቡት ግጥሞች መካከል መንገድ ስጡኝ ሰፊ የተሰኘዉ የሰዓሊና ገጣሚ የገብረክርስቶስ ደስታ ግጥም ይገኝበታል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ከሰዓሊ ባልደረቦችዋ ጋር ጥበባዊ ሥራዎችዋን ይዛ ጀርመን በርሊን መዲና ላይ የተመልካች ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ያለችዉ ወጣት ሰዓሊና ገጣሚ ምህረት ከበደ ግጥም በጃዝ ምሽት በሚለዉ ዝግጅት ላይም ተሳታፊ ናት። ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!

Kunst Festival in Addis Abeba
አለ የሥነ - ጥበብና ዲዛይን ት/ቤትምስል DW/A. T. Hahn


አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ