1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩስያና የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ

ዓርብ፣ ግንቦት 17 1999

የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልና የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሳማራው ጉባኤ ወቅት

https://p.dw.com/p/E0c4
ምስል AP

የሶቭየት ህብረት መፈረካከስ ትቷዋቸው ያለፋቸው ጠባሳዎች ዛሬም ድረስ ያልሻሩላት ሩስያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከምዕራባውያን ኃያላን ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ ነው ። የዚህ ምክንያቱም ብሄራዊ ጥቅሜን ይጋፋሉ በምትላቸው ልዩ ልዩ ዓለም ዓለም ዓቀፍ ፣ ድንበር ተሻጋሪ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጉዳያች ላይ የምትወስደዋቸው ዕርምጃዎች ናቸው ። የዋሽንግተን መንግስት በአውሮፓ ፀረ ሮኬት ሚሳይል እንዲተከል ከወራት በፊት ባቀረበው ዕቅድ ሩስያ አልተስማማችም ። የአውሮፓ መንግስታት የተቀበሉትን ይህን የዋሽንግተንን ውጥን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀዝቃዛው የሚመሳሰል ነው ሲሉ ተቃውመውታል ። ይህ አቋማቸውም ከዋሽንግተን ጋር እንዳቃቃራቸው ነው ። ከልዕለ ኃያሏ ዩናይትድ ስቴትስ ጋር በዚህ የሀሳብ ልዩነት ውስጥ ያለችው ሩስያ ከጎረቤቶችዋ የቀድሞዎቹ የሶቭየት ህብረት ግዛቶችና ከሌሎችም የአውሮፓ ህብረት አባላት ጋርም ሰላም የላትም ። ከብዙዎቹ ጋር ዕልህ በመጋባት በምትወስዳቸው ያልሰከኑ ዕርምጃዎች መንስኤ አንዳንዶቹን ለችግር መዳረጓ አልቀረም ። በዚህ ረገድ ከወራት በፊት ወደ ጀርመንና ሌሎችም አገራት ነዳጅ የሚያስተላልፈውን ቧንቧ መዝጋትዋ ከቅርብ ጊዜ ዕርምጃዎቿ ውስጥ የሚጠቀስ ነው ። እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችንም በዘላቂነት ለመፍታት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የአውሮፓ ህብረት መሪዎችና የሩስያው ፕሬዝዳንት በሩስያዊትዋ ግዛት በሳማራ ጉባኤ ተቀምጠው ነበር ። የጉባኤው ዓላማ በስተመጨረሻ ላይ የአጋርነት ስምምነት ላይ መድረስ ነበር ። አልተሳካም እንጂ ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን የሩስያና የአውሮፓ ህብረት አጋርነት ስምምነት ማነቆ የሆኑት ዋና ዋና ጉዳዮች ይዳስሳል ።
ከወራት በፊት ከጎረቤትዋ ከቤላሩስ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሩስያ ወደ ጀርመን ፖላንድና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት የነዳጅ ጋዝ የሚያስተላልፈውን ቧንቧ በመዝጋት በኃይል ምንጭ ባለቤትነትዋ ያላትን ጉልበት ለማሳየት ሞክራ ነበር ። በጊዜው ለሶስት ቀናትም ቢሆን ሩስያ ልትጎዳ የቻለችውን ጎድታ አቅምዋንም አሳይታ የዘጋችውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ከፍታለች ። ይህ አጋጣሚም የአውሮፓ ህብረት ለአስተማማኝና ዘላቂ የኃይል ምንጭ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያሳሰበ ነበር ። ችግሩ በተከሰተበት ወቅትም ሩስያ በትልቁም በትንሹም እየተነሳች የየነዳጅ ኃይልዋን መያዣ በማድረግ በርስዋ የነዳጅ ምርት ላይ ጥገኛ የሆኑ አገራትን ችግር ላይ እንዳትጥል አሰራሩ መስመር እንዲይዝ የአውሮፓ ህብረት የስምምነት ዕቅድ ወጠነ ። በዚህ ውጥን መሰረት ነበር የወቅቱ የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ባቀረቡት ሀሳብ እርሳቸው ፣ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆሴ ማኑዌል ባራሶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሩስያዊትዋ ግዛት ሳማራ ውስጥ በምትገኘው በቮልጋ ከተማ ጉባኤ የተቀመጡት ። በንግግሩም በተሳታፊዎች ገንቢ የተባሉ ውይይቶች የመደረጋቸውን ያህል ካለስምምነት የተለያዩባቸውም ነጥቦች ነበሩ ። ገንቢ ከተባሉት ውስጥ የድንበር ቁጥጥር ለማቃለል እንዲሁም የኢንቬስትመንትን ጉዳይ የሚከታተል አዲስ አካል ለማቋቋም የደረሱበት ስምምነት ይጠቀሳል ። ለሩስያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚያስተላልፈውን ቧንቧ በቅርቡ መዝጋትዋን ተከትሎ እጅግ መሰረታዊ በሆነው ለአውሮፓ በምትልከው የኃይል አቅርቦት ላይ የማስጠንቀቂያ አሰራር ስልት መዘርጋት ደግሞ ሌላ ነው ። ሀሙስ ዕለት በተካሄደ የዕራት ግብዣ ላይ ፑቲን ሩስያ በዚህ ወር ከካዛክስታንና ከቱርኬምስታን ጋር የኃይል አቅርቦት ስምምነት መፈራረምዋ አውሮፓን እንደሚጠቅም ለሜርክልና ለባራሶ ነግረዋቸዋል ። እነዚህ በጥሩ ጎናቸው የሚነሱ ነጥቦች ሲሆን አጠቃላዩ የጉባኤው መንፈስ ግን ችግር የተለየው አልነበረም ። በጉባኤው ሂደት በአጠቃላይ አንዳቸው ሌላኛውን ለማሳመን አዳግቷቸው እንደነበር ነው መራሂተ መንስት አንጌላ ሜርክል ከውይይቱ በኃላ የተናገሩት ። ሆኖም አሉ ሜርክል መቼም ቢሆን አንዳችን ስሌላኛችን ከማውራት ይልቅ እርስ በርስ መነጋገሩ ምንጊዜም የሚመረጥ ነው ። እናም እንደርሳቸው አባባል ከፋም ለማም በአህጉሪቱ የኃይል አቅርቦት ጉዳይና ከሩስያ በሚጠበቀው ድርሻ ላይ ፊት ለፊት ተገናኝቶ በግልፅ መነጋገሩ በራሱ እንደ ውጤት ነው የተወሰደው ። አንዳንድ ተችዎችም ተቀራራቢ አስታየየት ነው የሰጡት ። የጀርመንና የሩስያ የውይይት መድረክ ሊቀ መንበር እና በሞስኮ የጀርመን አምባሳደር የነበሩት እርነስት ዮርክ እንደተናገሩት ግልፅነት ሁሉንም ወገን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ።
“ጉዳዮችን አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር አይጠቅምም ሩስያውያንም ቢሆኑ መገምገም የማይሳናቸው ናቸውና በግልፅ መልስ ሲሰጣቸው ሳይቀበሉት አይቀሩም ። ዕርግጥ ነው እነርሱን አጣብቂኝ ውስጥ መክተት አይኖርብንም ። መዝለፍ የለብንም ። የሚጎዳቸውን ነገር ማውሳት አይገባም ። ነገር ግን የራስን አመለካከት መግለፁ ስህተት የለበትም ።”
በአውሮፓ ህብረትና በሩስያ መካከል አወዛጋቢው የኃይል አቅርቦት ላይ ሊደረግ የታሰበውን የአጋርነት ስምምነት ድርድር ሩስያና ፖላንድ በመቃቃራቸው ምክንያት በእዕንጥልጥል እንደተያዘ ነው ። ሩስያ የፖላንድ የስጋ ምርት ወደ ሀገርዋ እንዳይገባ በመከልከልዋ ፖላንድ በአፀፋው የአውሮፓ ህብረትና የሩስያ ድርድር እንዳይካሄድ ዕንቅፋት ሆናለች ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ባራሶ እንዳሉት ሩስያ የፀቡ መንስኤ የሆነውን የፖላንድን የስጋ ምርት አላስገባም የሚለውን አቋሟን ይዛ መቀጠልዋ መሰረተ የለውም ። የአውሮፓ ህብረት ዕምነትም ይኽው ነው ። የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ደግሞ በፖላንድና በሩስያ መካከል በተፈጠረው በዚህ አለመግባባት ላይ የአውሮፓ ህብረት ምክርቤት በሀላፊነት እያሰበበት ነው ።
“ስጋ ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ንግድና የሸማቹን ጥቅም ማስጠበቅ የአውሮፓ ህብረት ፋንታ ነው ። ይህም በአውሮፓ ህብረት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው የአውሮፓ ኮሚሽን እንዲሁም ከፖላንዳውያኑ ባለስልጣናት ጋር በቅርብ በመመካከር የሚከናወን ነው ። ሀያ ሰባት አገሮችን ያቀፈው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ወቅታዊ ፕሬዝዳንት እንደመሆኔ መጠን ፖላንድ በሚመለከታት ጉዳይ ላይ አታተኩርም ለማለት ይቸግረናል ። ለማንኛውም ይህ አውሮፓውያን በሀላፊነት የሚያስቡበትና ወደፊትም ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው ። “
የሩስያ ፀብ ከፖላንድ ጋር ብቻ አይደለም ። ከኤስቶኒያ ከላቲቪያና ከሊትዌንያም ጋር መልካም ግንኙነት የላትም ። የግንኙነቱ መሻከር መንስኤ በኤስቶኒያና ላቲቪያ የሩስያ ዜጎች አያያዝ ነው ። በነዚህ ሀገራት አናሳዎቹ ሩስያውያን እየተጠቁ ነው ስትል ተቃውሞዋን በማሰማት ላይ ናት ። ድርጊቱንም ከአውሮፓውያን የማይጠበቅ ነው የምትለው ። በተለይም ባለፈው ወር ኤስቶኒያ ውስጥ ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት ሰለባዎች ማስታወሻ የቆመው ሀውልት ከተተከለበት ቦታ እንዲነሳ መደረጉና በወቅቱም ሩስያዎች ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ አንድ ሩስያዊ መገደሉ ፀቡን አባብሶታል ። የሀውልቱ መነሳት ሩስያውያንን ብቻ ሳይሆን የክሬምሊን መንግስትንም አስቆጥቷል ። ከሀውልቱ መፍረስ ጋር ተያይዞ የሞተው የሩስያዊው ተቃዋሚ ገዳዮች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብለዋል ፑቲን ። ሩስያ በነዚህ ሀገራት ላይ እነዚህን የመሳሰሉትን ክሶች ብትሰነዝርም ሀገራቱም ሆነ የአውሮፓ ህብረት ክስሱን አልተቀበሉትም ። የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ማኑዌል ባራሶ ኤስቶኒያ የመታሰቢያውን ሀውልት ለማንሳት የደረሰችበትን ውሳኔ አንድ ሉዓላዊ ሀገር ውሳኔ ነው ነበር ያሉት ። ከተከሳቹ አንዷ የሆነቸው የኤስቶኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሀገራቸው የአናሳ ወገኖች መብት አክባሪና ለዓለም ዓቀፍ ህጎችና ደንቦች ተገዥ ናት ፤ ላቲቪያም በበኩልዋ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዋ በኩል ወቀሳው አዲስ አለመሆኑን አስታውሳ የእነርሱ ትክክለኛ አለመሆን የላቲቭያ በዓለም ዓቀፉ ድርጅት የአውሮፓ ህብረት ተቀባይነት ማግኘት ሊረጋገጥ ችሏልም ነው ያለችው ። ላትቪያና ኤስቶኒያ ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጋር ከተቀላቀሉበት ከዛሬ ስልሳ ሰባት ዓመት አንስቶ በተቆጠረው ከግማሽ ምዕተ ዓመት የምልቅ ዘመን ውስጥ በመቶ ሺሆች የሚገመቱ አናሳ ሩስያውያን ወደ ነዚህ ግዛቶች ተሰደዋል ። ሀገራቱ የዛሬ አስራ ስድስት ዓመት ከሶቭየት ህብረት ሲገነጠሉ ባወጡት ህግ በሶቭየት ህብረት ዘመን ወደ ግዛቶቹ የተሰደዱ ዜግነት የሚያገኙት የቋንቋና የታሪክ ፈተናዎችን ካለፉ ብቻ እንደሆነ በደነገጉት መሰረት ወደ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ብቻ ናቸው ዜግነት ያገኙት ። የተቀሩት ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ አልተሳካላቸውም ። ቀድሞም ቢሆን ሁለቱ አገራት በሶቭየት መያዛቸው ህጋዊ ነው የሚል አቋም ያላት ሩስያ በበኩልዋ እነዚህን የመሳሰሉት መሰናክሎች የአናሳዎቹን ሩስያዎች መብት ይጋፋሉ ድርጊቱም ተቀባይነት የለውም ስትል ትከሳቸዋለች ። የአውሮፓ ህብረት ደግሞ የኤስቶኒያና የላትቪያን የዜግነት አሰጣጥ መርህ ከዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ህግጋት ጋር የተጣጣመ ነው የሚለው ። በዚህና ሌሎችም ሩስያ ለሰነዘረቻቸው ወቀሳዎች ህብረቱ ከሀገራቱን ጎን እንደሚቆም ነው ያሳወቀው ። በሌላ በኩል በቮልጋው የሩስያና የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ ላይ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን የአውሮፓ ህብረት የኃይል አቅርቦት ደንብ ፑቲን አጥበቀው ነው የተቃወሙት ምክንያታቸውም ህብረቱ ለሩስያ ኩባንያዎች የኃይል ምንጭ ገበያ ለመክፈት ምንም አልፈየደም የሚል ነው ። ሆኖም ፑቲን በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት ለአውሮፓ አንድነት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገችው አገራቸው ህብረቱን የትብብር ተጓዳኝ አድርጋ ነው የምትወስደው ። ያም ሆኖ ወደ ትብብሩ የሚወስደው ድርድር ከመካሄዱ አስቀድሞ የአውሮፓ ህብረት የራሱን ችግሮች መፍታት አለበት ይላሉ ፑቲን ።
“አንዱ ከባዱ ጉዳይ በሩስያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ትብብር ህጋዊ መሰረት በማስያዝ አዲስ የጋራ ትብብር ማጥናከሪያ ውል ለማስፈረም ይቻል ዘንድ ይጠበቅ የነበረው ድርድር እስካሁን አልተካሄደም ። ሁኔታውን እኛ እያጋነነ አይደለም ። እኛ እንደሚገባን ከኛው የጋራ ድርድር በፊት የአውሮፓ ህብረት የራሱን የውስጥ ችግሮች መፍታት ይኖርበታል ። እኛም ይህን እናከብራለን ። እንደገና በድጋሚ እገልፃለሁ ሩስያ የአውሮፓ ህብረትን ስልታዊ የትብብር ተጓዳን አድርጋ ነው የምትመለከት ። ላሰምርበት የምፈልገው ለአያሌ አስርት ዓመታት የተለያየ ባህል ያላቸው በርካታ ብሄሮችን ያቀፈችው ሩስያ ለአውሮፓ ህብረት አንድነትና ለዲሞክራሲ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግዋን ነው ። “
ሩስያ በአሁኑ ጉባኤ ይህን መሰል አቋምዋን ማንፀባረቅዋ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት ምክንያታዊ ነው ። ፑቲን የህብረቱ የውስጥ ችግር ያሉትም ዕውነትነት አለው ። ይህ መፍትሄ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ሩስያ ለህብረቱ ከበሬታ ባሳየች ነበር ይላሉ አምባሳደር ኽርነስት ዮርክ የሩስያና የጀርመን የውይይት መድረክ ሊቀ መንበር ።
“በተናጠልም የአውሮፓውያን ሀገሮች ከሞላ ጎደል በሩስያውያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ነበር ፤ ጠንከር ባለና ፅኑ አቋምን በሚያንፀባርቅ መልኩ ። ይህ የሆነው አውሮፓውያኑ በአንድነት የቆሙ በማስመሰል ነው ። ነገር ግን ለምሳሌ ያህል የአውሮፓ የአንድነት ግንባታ ቢካሄድ ህገ መንግስቱ መፅናቱ በግልፅ ቢታይ እና የአውሮፓም አንድነት መደምደም ቢያመላክት ኖሮ ሩስያውያኑ አክብሮታቸውን ባሳዩ ነበር ።“
የአክብሮት ነገር ከተነሳ ሩስያ የአውሮፓ ህብረት አባላትን በዕኩል ዓይን ባለማየት ትወቀሳለች ። ይህን አባላቱን የመከፋፈል ሙከራ እንድታቆምም የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆሴ ማኑዌል ባራሶ አስጠንቅቀዋታል ። ባራሶ ለአንድ የጀርመን መፅሄት በሰጡት ቃለ ምልልስ ሩስያ ፖላንድንና የቦልቲክ አገራትን ከተቀሩት የህብረቱ አባላት በተየለ ዓይን ነው የምታያቸው ። ሩስያ እነዚህ ሀገራት የህብረቱ ሙሉ አባል እንዳልሆኑ ነው የምትቆጥረው ። ሆኖም ባራሶ እንዳሉት ሩስያ ህብረቱ የተሰመረተው በትብብር መንፈስ መሆኑን ማወቅ አለባት ። የፖላንድ ጥቅሞች እንደ ፈረንሳይ ጀርመንና ፖርቱጋል ጥቅሞች ሁሉ ህጋዊ መሆናቸውም መገንዘብ ይኖርበታል ። ባራሶ ባለፈው ዓርብ በሰጡት መግለጫም የአንዱ የህብረቱ አባል ችግር የሌላው ችግር መሆኑንም ጠቅሰው ነበር ።
“የፓላንድ ችግር የአውሮፓ ችግር ነው ። የሊቱዌንያና የኤስቶኒያም ችግርም የአውሮፓ ችግር ነው ። ዕውነተኛ መልካምና የቅርብ ትብብር እንዲኖር ከተፈለገ የአውሮፓ ህብረት በአንድነት የመቆም መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው ። “
የቀድሞዎቹን የሶቭየት ግዛቶች በሰብዓዊ መብት መገፋት የምትከሰው ሩስያ ራስዋም ተቃዋሚዎችን በማፈንና ጋዜጠኞችን በመግደልና በማፈን ከሚነሱት አገራት አንዷ ሆና ሰብዓዊ መብትን በመጣስ ጉዳይ ጣትዋን ወደ ሌሎች መቀሰርዋ ትዝብት ላይ ጥሏታል ። በሚያዚያ ወር ሞስኮና ሴንት ፒተርስ በርግ ውስጥ ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ የወሰደው ጠንካራ የኃይል ዕርምጃ እና ከዚያም በርካታ ሰልፈኞች መታሰራቸው ፑቲንን ማስወቀሱ አልቀረም ። አሁንም የቮልጋ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለመካፈል ወደ ሳማራ በማምራት ላይ የነበሩት ታዋቂ ሰዎችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያ ታስረዋል ። ከሳማራው ጉባኤ በፊትም ብዙ ሰዎች ወህኒ ተወርውረዋል ። የተቃዋሚዎች መታሰር እንዳሳበታቸው የገለፁት ሜርክል ተቃዋሚዎቹ ያቀዱትንትን ሰልፍ ማካሄድ ይችላሉ ብዮ ተስፋ አድርጋለሁ ነበር ያሉት በወቅቱ ። በምላሹ ተቃውሞን የመግለፅ መብት እንደሚከበር የገለጹት ፑቲን ጀርመንም ብትሆን የቡድን ስምንት ጉባኤ በሚካሄድበት ስፍራ የመከላከያ ዕርምጃዎችን መውሰድን እንደማትቆጠብ አንስተዋል ። ስለ ሚያዚያው የፖሊስ የኃይል ዕርምጃ ፑቲን በሰጡት መልስ በፖሊስ ተግባር ስህተት ተፈፅሞ ሊሆን ይችላልም ብለዋል ። እነዚህ የመሳሰሉ የውስጥ ችግሮች ያሉባት ሩስያ የአውሮፓ ህብረት አባል ከሆኑት ጎረቤቶቿ ጋር በየምክንያቱ በመቃቃር በምትፈጥራቸው ችግሮች ሰበብ ከህብረቱ ጋር ወደ ጋራ ትብብር ሊያመራ የሚያስችለውን ውል ወደ መፈራረም የሚያደርሰውን ድርድር ማካሄድ አልተቻለም ። ወደ ስልታዊው ትብብር የሚያደርሰው ድርድሩ መዘግየት አይፈለግም ። እናም የጀርመንና የሩስያ የትብብር መድረክ ሊቀ መንበር አምባሳደር ኽርነስት ዮርክ እንዳሉት በሀለቱም ወገኖች በኩል አንዱ ለሌላው አስፈላጊ እንደመሆኑ ሁለቱ ወገኖች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ሊሹለት ይገባል ።
“በመጨረሻም ሁሉም መከናወን የሚችለው በህብረት ብቻ ነው ። ሩስያውያን አውሮፓን ይፈልጉዋታል ። ሩስያም አውሮፓን ትፈልጋለች ። የተደቀኑ ችግሮችና እና በተለያዩ ቋንቋዎች በግልፅ የሚነገሩት ሁሉ መፍትሄ ሊገኝላቸው ይገባል “
ባለፈው ሳምንት በሩስያዋ ግዛት በሳማራ የተካሄደው ጉባኤ በውዝግብቢፈፀምም ገንቢውይይቶች እንደሚቀጥሉ ነው የተነገረው ።