1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩዋንዳ የሥላላ ድርጅት ኃላፊ መታሠርና መዘዙ

ሐሙስ፣ ሰኔ 18 2007

የሩዋንዳ መንግሥት ክስ፤ ዉንጀላ ወቀሳዉን «የጠላት ወሬ» ነዉ-የሚለዉ።ባለሥልጣኑ የተከሰሱትም የካጋሚን መንግሥት ለማሳጣት በሚሹ ወገኖች ነዉ ባይ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስም የስጳኝ ፍርድ ቤት ያሰራጨዉን የእስራት ዋራንት «በምክንያት ያልተደገፈ» በማለት ላለመቀበል አቅማማ ነበር

https://p.dw.com/p/1FnRQ
ምስል Getty Images/AFP/E. Musoni

[No title]

የሩዋንዳ ብሔራዊ የሥለላና የፀጥታ አገልግሎት ሐላፊ ጄኔራል ካሬንዚ ካራኬ ብሪታንያ ዉስጥ መታሠራቸዉ ሩዋንዳን ከብሪታንያ እና ከስጳኝ ጋር እያወዛገበ ነዉ።ሩዋንዳ ትልቅ ባለሥልጣንዋ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠይቃለች።የብሪታንያ ፖሊስ ካራኬን ማሰሩን የሚቃወሙ በመቶ የሚቆጠሩ የሩዋንዳ ዜጎች ኪጋሊ የሚገኘዉን የብሪታንያ ኤምባሲን ከበዉ እርምጃዉን እያወገዙ ነዉ።እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ ሩዋንዳ ዉስጥ ለተፈፀመ ወንጀል ካራኬን የከሰሰችዉ ስጳኝ ባንፃሩ ብሪታንያ እስረኛዉን አሳልፋ እንድትሰጣት በይፋ ጠይቃለች።

ሩዋንዳዉያን ወዳጅ ጠላቶቸዉ KK በሚል ምሕፃራቸዉ ይጠሯቸዋል።ትናንት የብሪታንያ ኤምባሲን የከበበዉ ደጋፊዎቻቸዉም KK ይፈቱ እያለ ሲፈክር ነዉ የዋለዉ።ሠልፈኞቹ፤ ጄኔራሉ እስኪለቀቁ ድረስ የኤምባሲ ዙሪያ ሠልፍ ተቃዉሟቸዉን እንደማያቋርጡም አስታዉቀዋልም።የሩዋንዳዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሉዊስ ሙሺኪዋቦ ተቃዉሞ ደግሞ ከዲፕሎማሲዉም ወግ ወጣ ያለ ነዉ።«የምዕራባዉያን ትብብር» ይላል ወይዘሮ ሙሺኪዋንቦ በቲዊተር ገፃቸዉ የለጠፉት ፅሁፍ «አፍሪቃዉያንን ማዋረዳቸዉ ተቀባይነት የለዉም።» አከሉ የትንሺቱ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማት።

ካራኬን ለማስፈታት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ራሳቸዉ ወደ ለንደን እንደሚጓዙ የሩዋንዳ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።ከማድሪድ የተሠማዉ ተቃራኒዉ ነዉ።የፕሬዝደንት ፖል ካጋሚ ቀኝ እጅ የሚባሉት ጄኔራል ካሬንዚ ካራኬ ባለፈዉ ቅዳሜ ለንደን አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የተያዙት የስጳኝ ፍርድ ቤት በተገኙበት እንዲታሰሩ ባሳለፈዉ ትዕዛዝ መሠረት ነዉ።ታላላቆቹ ሐይቆች በሚባለዉ አካባቢ ለተገደሉና ለተበደሉ ሰዎች ጥብቅና የቆሙት ዮርዲ ፓሎዉ-ላቭርዶስ እንደሚሉት ዓለም አቀፍ ሕግ መከበር አለበት።

Onesphore Rwabukombe Ruanda Massaker
ምስል picture-alliance/dpa/M. Becker

«ይሕ ዓለም አቀፍ ሕግ ነዉ።ይሕ ዓለም አቀፍ ሥምምነት ነዉ።ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ከግንዛቤ ያስገባ ነዉ።አምስቱን ትላልቅ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች።ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ሥምምነቶችን ማስከበር፤ የብሪታንያ ብቻ ሳይሆን የስጳኝ ባለሥልጣናትና መንግሥታትም ሐላፊነት ነዉ።ዓለም አቀፍ ወንጀልን በተመለከተ ፍርድ ቤት የማቅረብ፤ የመመርመርና ከትትክለኛ ሒደት በኋላ ፍርድ የመስጠት ሐላፊነት አለባቸዉ።»

የስጳኝ አቃቤ ሕግ በከሰባት ዓመት በፊት ባስያዘዉ የክስ ጭብጥ የ1986ቱ የሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ባበቃ ማግሥት የሩዋንዳ ጦር በሺሕ የሚቆጠሩ ሁቱዎችን፤ ሰወስት የስጳኝ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የርዳታ ድርጅት ሰራተኞችን ገድሏል።«ሁለተኛዉ ዘር ማጥፋት» ተብሎ የሚጠራዉን ዘመቻ የሚመራና የሚያስተባብረዉ የሩዋንዳ ጦር የመረጃ ወይም የስለላ ክፍል ነበር።የክፍሉ ሐላፊው ጄኔራል ካሬንዚ ካራኬ።

የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የሁዩማን ራይትስ ዋች ባልደረባ ካሪና ቴርትሳኪያን ድርጅታቸዉ የስጳኝ አቃቤ ሕግ የመሠረተዉን ክስ በቅጡ መርምሮታል ይላሉ።ዉጤቱ፤ ቴርትሳኪያን እንደሚሉት ካራኬ የሚያዙት የሩዋንዳ ጦር ከሩዋንዳም አልፎ ኮንጎ ዉስጥም በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉን የሚጠቁም ነዉ።

«የሩዋንዳ ጦር አዛዦች ለረጅም ጊዜ በተፈፀሙ በርካታ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ናቸዉ።ሰዎች ተገድለዋል።ተገርፈዋል።በዘፈቀደ ታሥረዋል።የሩዋንዳ ጦር አዛዦች ለበርካታ ጅመላ ግዲያዎች ተጠያቂዎች ናቸዉ።በተለይ ሥርዓቱን የሚቃወሙትን ለማጥፋት በ1989 እና በ1990 በተከፈተዉ መጠነ ሠፊ ዘመቻ ለጠፋዉ ሕይወት ተጠያቂዎች ናቸዉ።በዚሕ ተቃዋሚን «የማፅዳት» ዘመቻ ሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን ኮንጎ ዉስጥም በሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።»

ጄኔራል ካራኬ-ከጦሩ የስለላ ክፍል ሐላፊነት ወደ ብሔራዊ የሥለላና የፀጥታ አገልግሎት (NISS) ሐላፊነት ከተሸጋገሩ በሕዋላም የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ከምሕረት የለሽ እርምጃቸዉ አልታቀቡም።የፕሬዝደንት ፓዉል ካጋሚ ተቺና ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት የጄኔራሉ ጨካኝ ረጅም እጅ ሩዋንዳን ተሻግሮ ደቡብ አፍሪቃም ደርሷል።ወይዘሮ ቴርትሳኪያን የካራኬን ድንበር ዘለል የጭካኔ እርምጃ በአብነት ያስረዳሉ።

«ከሩዋንዳ ዉጪ በሚኖሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ግድያና ጥቃት ተፈፅሟል።ደቡብ አፍሪቃ እና ሌሎች ሐገራትም።በጣም የጎላዉና መጥፎዉ ከካራኬ በፊት የሩዋንዳ የሥለላ ድርጅት ሐላፊ የነበሩት የፓትሪክ ካሬጌያ ግድያ ነዉ።ካሬጌያ ከፕሬዝደንት ካጋሚ ጋር ተጣልተዉ ደቡብ አፍሪቃ ተሰደዱ።ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተገደሉ።ጥር 1,2014»

Ruanda Völkermord 1994
ምስል picture-alliance/AP Photo/J.-M. Bouju

እንደ ካሬጌያ ሁሉ ከካጋሚ ጋር ተቀያይመዉ ሥልጣንና ሐገራቸዉን ጥለዉ ደቡብ አፍሪቃ የተሰደዱት የቀድሞዉ የሩዋንዳ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከተቃጣባቸዉ ግድያ ለጥቂት ነዉ ያመለጡት።ስደተኛዉ ጄኔራል የግድያ ሙከራዉ ከከሸፈ በኋላ የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ ሃያ አራት ሰዓት ጥበቃ ያደርግላቸዋል።

የሩዋንዳ መንግሥት ክስ፤ ዉንጀላ ወቀሳዉን «የጠላት ወሬ» ነዉ-የሚለዉ።ባለሥልጣኑ የተከሰሱትም የካጋሚን መንግሥት ለማሳጣት በሚሹ ወገኖች ነዉ ባይ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስም የስጳኝ ፍርድ ቤት ያሰራጨዉን የእስራት ዋራንት «በምክንያት ያልተደገፈ» በማለት ላለመቀበል አቅማማ ነበር።አስፈሪዉን የሩዋናዳ ጄኔራል ከመቀፍደድ ግን እስካሁን ማንም አላዳናቸዉም።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ