1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ ሕገ መንግሥት እና የተቃዋሚው ፓርቲ ጥያቄ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2 2007

የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ምንም እንኳን ሃገሪቱን እጅግ ጠንካራ በሆነ አገዛዝ ቢመሩም ተወዳጅ ናቸው። ብዙ የርዋንዳ ዜጎች ፕሬዚደንት ካጋሜ የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ለውጥ ተደርጎ አመራራቸውን ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን እንዲቀጥሉ የቀረበውን ሀሳብ ደግፈዋል። አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ግን ይህንን እቅድ ለማከላከል ቆርጥ ተነስቶዋል።

https://p.dw.com/p/1GBny
Präsident von Ruanda Paul Kagame
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

[No title]

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ከ12 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት በአፍሪቃ ህብረት ባሰሙት ንግግራቸው ላይ ማንም የድሜ ልክ ፕሬዚደንት ሊሆን አይችልም ማለታቸው ይታወሳል። በመዲናይቱ ኪጋሊ የሚገኘው የርዋንዳ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኦባማ ቀደም ሲል የተሰማውን ንግግራቸውን ከማሰማታቸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንዲችሉ ሕገ መንግሥቱን ይሻሻል አይሻሻል በሚለው ጉዳይ ላይ ክርክር ማካሄዳቸው ይታወሳል። በተጨባጭ እንደራሴዎቹ የተከራከሩት የሃገሪቱን ፕሬዚደንት ሥልጣን በሁለት ዘመን በሚገድበው አንቀጽ 101 ላይ ማሻሻያ ለውጥ ይደረግበት በሚለው ሀሳብ ላይ ነበር። የፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን እንዲወዳደሩ በጠየቀው ጥያቄ ላይ የርዋንዳ ሕዝብ ሬፈረንደም ያካሂድ በሚል በምክር ቤት የቀረበው ሀሳብ በእንደራሴዎቹ ብቻ ሳይሆን ከብዙ የሃገሪቱ ሕዝብ ዘንድም ግዙፍ ድጋፍ አግኝቶዋል። ከ11,7 ሚልዮኑ የርዋንዳ ሕዝብ መካከል 3,7 ሚልዮኑ ሬፈረንደሙ ይደረግ በሚል የቀረበውን ጥያቄ በመደገፍ ፈርሞዋል። ተቃዋሚ ወገኖችም ቢሆኑ በብዛት የሬፈረንደሙን ሀሳብ ደግፈውታል። የሶስት ሚልዮን ሕዝብ ፊርማ ግልጹን መልዕክት ማስተላለፉን ነው የተቃዋሚው የሶሻሊስት ፓርቲ መሪ ንኩዚ ጁቨናል ያስታወቁት። እርግጥ፣ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር የሚለውን ሀሳብ በመሠረቱ ይቃወማሉ። ይሁንና፣ ሀሳቡ በሕዝበ ውሳኔ ከተደገፈ ወደፊትም የሃገር አመራሩን ስራ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የፕሬዚደንቱን ሥልጣን በሁለት ዘመን የሚገድበውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ የማስቀየሩን ሀሳብ በጥብቅ የተቃወመው ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የርዋንዳ የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ነው። ፓርቲው ሕዝበ ውሳኔው እንዳይካሄድ ለማከላከል እአአ ባለፈው ሀምሌ 29 ቅሬታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርቦዋል። የፓርቲው ሊቀ መንበር ፍራንክ ሀቢኔዛ ፓርቲያቸው ለምክር ቤት ያቀረው አቤቱታ ለሚመለከተው ክፍል ባለመቅረቡ እና መልስ ባለማግኘቱ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

Flagge von Ruanda
ምስል Carl Court/AFP/Getty Images

ሬፈረንደሙን 30% የርዋንዳ ሕዝብ መሸፈኑ የሕዝቡን ፍላጎት ያንፀባረቀ መሆኑ ቢነገርም፣ የርዋንዳ የሰብዓዊ መብት ማዕከል ባልደረባ ቲየሪ ኬቪን ጋቴቴ ሕዝቡ ድጋፉን በውዴታ መስጠቱን እንደሚጠራጠሩት ገልጸዋል።

« አዎ ብዙዎቹ ደግፈውታል። አንዳንዶቹ የሬፈረንደሙን ሀሳብ በመደገፍ ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ ተጠይቀዋል። ካጋሜ በገጠሩ አካባቢ በጣም ተወዳጅ ናቸው፣ በዚያ የሚኖረው ብዙው ህዝብ ግን ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን መወዳደር ሕገ መንግሥቱን እንደሚጥስ አያውቁም። »

በዚህም የተነሳ የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተቃውሞውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበበት ድርጊት አስፈላጊ እንደነበር ለፓርቲው ሕጋዊ ምክር ያካፈሉት ጠበቃው ቲየሪ ኬቪን ጋቴቴ ገልጸዋል። የአረርንጓዴዎች ዴሞክራቲክ ፓርቲን ያቀረበው አቤቱታ በተደመጠበት ወቅት በፍርድ ቤት ለመገኘት ያቀረቡት ማመልከቻቸው ገለልተኛ አይደሉም በሚል ተቀባይነት ያላገኘላቸው ቲየሪ ኬቪን ጋቴቴ ፓርቲው በፍርድ ቤት ላቀረበው ተቃውሞ የተሳካ ውጤት ማስገኘቱን መጠራጠራቸውን ገልጸዋል።

« ብዙ ዕድል አለው ብዬ አላስብም። ያሳዝናል። የፓርቲው መሪዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸውን ማየት አለማየቱን ለመወሰን ለሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ ሰጥቶዋል። ግን ፣ ጥረታቸው መሳካቱን እጠራጠራለሁ። »

ለተቃውሞው ፓርቲ ሕጋዊ ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ በምርጫ የሃገር አመራር ሥልጣንን የሚይዙ መሪዎች የተመደበላቸውን ጊዜ ብቻ ሊያገለግሉ እንደሚገባ ነው ጋቴቴ ያመለከቱት።

« ሕገ መንግሥት ሊቀየር ይገባል ብዬ አላምንም። ይህ የማምንበት መመሪያዬ ነው። አፍሪቃ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ በተቀየረባቸው ሃገራት ሁኔታው ሲበላሽ እንጂ እስካሁን ሲሻሻል አላየሁም። »

በርዋንዳ የፕሬዚደንቱን የሥልጣን ዘመን ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም የቀረበው ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበት ሀሳብ ይህን ያህል ድጋፍ ማግኘቱን በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የፕሪቶርያው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ወይዘሮ ዮላንድ ቡካ አስገራሚ ብለውታል። ዮላንዳ ቡካ የተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተቃውሞን ትክክለኛ ቢሉትም፣ ም ልክ እንደ ጠበቃው እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጋቴቴ አዎንታዊ መልስ ያገኛል ብለው አያምኑም።

« የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ የርዋንዳን የተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲን ተቃውሞ መደገፉን በጣም እጠራጠራለሁ። ፕሬዚደንት ካጋሜ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ ለማስቻል የተጀመረውን ጥረት ወይም እቅዱን ያቀነባበሩት ከሥልጣን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ነው። የአንድ ሃገር ምክር ቤት እንደራሴዎች በጠቅላላ እና የተቃዋሚ ቡድኖች አባላት ሳይቀሩ ፕሬዚደንቱ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ሕገ መንግሥቱ የሚቀየርበትን ሀሳብ መደገፋቸው በፍፁም ያልተለመደ ነው። እና ይህ ሲታሰብ፣ ፍርድ ቤቱ ግፊት ሊያርፍበት ይችል ይሆናል። »

Bildergalerie Ruanda Versöhnung Bild 5
ኪጋሊምስል James Nzibavuga

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራቲክ ፓርቲን እአአ የፊታችን መስከረም ዘጠኝ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ዮላንዳ ቡካ እንደሚሉት፣ ፍርድ ቤቱ ሬፈረንደሙ እንዲካሄድ ቢፈቅድም እንኳን በሃገሪቱ ተቃውሞ አይነሳም።

« ተቃዋሚዎች በሃገሪቱ አደባባዮች መውጣታቸው የማይታሰብ ነው። ምክንያቱም፣ ጠንካራ ቁጥጥር የሚያደርገው የፀጥታ ጥበቃው ዘርፍ ማንኛውንም በሃገሪቱ የሚታሰብ ተቃውሞን ገና በእንጭጩ የመቅጨት ችሎታ አለው። ይህ በመሆኑም የሃገሪቱን መንግሥት ጠንክሮ ሊጋፈጥ የሚችል የፖለቲካ ቡድን የለም። የአረንጓዴው ፓርቲ የመንግሥት የማስፈራራት ርምጃ ሰለባ ሆኖዋል፣ እንደሚታወሰው፣ አንዱ ከፍተኛ የፓርቲው ተጠሪ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተገድለው ተገኝተዋል። »

የአረንጓዴው ፓርቲ ፖለቲከኛ ኦንድሬ ካግዋ ርዊሴሬካ እአአ በ2010 ዓም ተገድለዋል።

በርዋንዳ አሁን የቀረበው የሬፈረንደም ጥያቄ በጎረቤት ቡሩንዲ ፕሬዚደንቱ ፒየር ንኩሩንዚዛ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሃገራቸውን ሕገ መንግሥት በመጣስ ለሶስተኛ ጊዜ ወደተመረጡበት እና ይህም ደም አፋሳሽ ሁከት ወዳስከተለበት ዓይነት ሁኔታ ያመራል በሚል አንዳንዶች ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ርዋንዳ ፕሬዚደንቱ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን መወዳደር መቻል አለመቻላቸውን በተመለከተ ይደረግ አይደረግ በሚባለው የሬፈረንድም ጉዳይ የተነሳ ሃገሪቱ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቃት የዓለም አቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዮላንዳ ቡካ ገምተዋል።

« ሰዎች የካጋሜን መንግሥት በልማቱ መስክ በሃገሪቱ ላስመዘገበው የኤኮኖሚ እድገት ያሞግሷቸዋል። ይህ የተሳካ ውጤት ግን በዘላቂነት ሊቀጥል የሚችለው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሲኖር ነው። መሪዎች ይህን ሥልጣናቸውን አንድም ለሌላ ፓርቲ ዕጩ ወይም ለሌላ የራሱ የገዢው ፓርቲያቸው አባል በሰላም በሚለቁበት ድርጊት ገሀድ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ ርዋንዳ ውጥረት የታከለበት ጊዜ ይጠብቃታል፣ በሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት የታየው የተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት የመዝለቁ ጉዳይም ሕዝቧን ማሳሰቡ አይቀሩም። »

20 Jahre nach dem Genozid in Ruanda DEU

እአአ በ1994 ዓም ከተካሄደው የጎሳ ጭፍጨፋ በኋላ በርዋንዳ እርቀ ሰላም እስኪወርድ እና ሃገሪቱ አስገራሚ የልማት እድገት እስክታሳይ ድረስ ብዙ ዓመታት ናቸው ያለፉት። ግን እንደሚታወቀው፣ የብዙ ዓመት ልፋትን ለማጥፋት ጥቂት ወራት ይበቃል። ለዚህም አዎንታዊ ኤኮኖሚያዊ እድገት እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ይታይባት የነበረችውን እና የቀድሞው ፕሬዚደንትዋ ሁፌት ፌሊክስ ቡዋኜ እአአ በ1993 ዓም ሲሞቱ ወደርስ በርሱ ጦርነት የወደቀችው ምዕራብ አፍሪቃዊቱን ሃገር ኮት ዲ ቯርን በምሳሌነት መጥቀስ ይበቃል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ