1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ውል ለማዕከላዊት አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2007

የማዕከላዊት አፍሪቃ የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች ፍርንሷ ቦዚዜና የቀድሞው የሰሌካ አማጽያን ዋና መሪ ሚሼል ጆቶዲያ፤ በኬንያ ሸምጋይነት ጠላትነትን ወደ ወንድማማችነት መንፈስ ለውጠው ለሀገር ይጠቅማል የተባለውን የሰላም ውል ትናንት ናይሮቢ ውስጥ መፈራረማቸው ይታወሳል።

https://p.dw.com/p/1F9fI
Zentralafrikanische Republik François Bozizé und Michel Djotodia
ምስል AFP/Getty Images/S. Jordan

ሁለቱ የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች ውሉን ቢፈርሙም፤ የሽግግሩ መንግሥት ገና አልተመሠረተም። ያም ሆኖ ለወደፊቱ ምርጫ በመዲናይቱ በቦንጊ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። የማዕከላዊት አፍሪቃ የሰላም ውል በሚል ርእስ የ DW ባልደረባ ፊሊፕ ዛንድነር ያሰናዳውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።
ሁለቱም የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን ሁሉ እንደሚያከብሩና በዚሁ ወር ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ጉባዔ ለመሳተፍም ቃል ገብተዋል። ሸምጋይ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዑሑሩ ኬንያታ፣ የማዕከላዊት አፍሪቃው የሰላም ውይይት መሳካቱን በመግለጽ በግብዣ እንዲጠናቀቅ ከማድረጋቸውም፤ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሕዝብ በሰላምና በፍቅር እንዲኖር በአርቀ ሰላም አርአያነትን በማሳየታቸው አመስግነዋቸዋል።
«ሁለቱ ወንድሞቼ ፣ የቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች፣ ስለወሰዳችሁት ቁርጠኛ አቋም ላመሠግናችሁ እወዳለሁ። እኛም ድጋፋችንን እንደማንነፍጋችሁ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ። ባለፉት ጊዜያት በሐሳብ እንደማትጣጣሙ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ ያን አስወግዳችሁ በመገናኘት በመምከራችሁ ፤ ባጠቃላይ ላደረጋችሁት ጥረት ዕውቅና እንሰጣለን። ይህ ስምምነታችሁ የሚያሳየው የተቻላችሁን ሁሉ በማድረግ የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ሕዝብ ፣ እርስ-በርስ በመግባባት ፣ በሰላምና ፍቅር እንዲኖር ሰፊ ጥረት ማድረጋችሁን ነው።»
ጆቶዲያና ቦዚዜ የውዝግብ ተማሳሌት ሆነው ነው የሚታዩት፤ ጆቶዲያ የሙስሊም አማጽያን ንቅናቄ (ሴሌካ) ቦዚዜም ጸረ ባላካ ሚሊሺያ ጦረኞች የሚሰኙት የክርስቲያኖች ታጣቂ ኃይል መሪ በመሆን! ይሁንና የሁለቱ የቀድሞ ተጻራሪ መሪዎች ተወካዮች ፣ ናይሮቢ ላይ መጋቢት 30 ቀን 2007 የተኩስ አቁም ውል ተደራርመዋል። በካትሪን ሳምባ ፓንዛ የሚመራው የሽግግር መንግሥት ተወካዮች ግን አልተሳተፉም። ከደቡብ አፍሪቃ «ዖካፒ» የተሰኘው ድርጅት አማካሪና የማዕከላዊት አፍሪቃ ተመራማሪ David Smith እንዲህ ይላሉ---
«በስምምነቱ ያልተጠቀሰው ጉዳይ----ስምምነቱ፤ --ፍርንሷ ቦዚዜና ሚሸል ጆቶዲያ፤ በዚህ ዓመት ፤ ሐምሌ ወይም ነሐሴ በሚካሄደው ምርጫ እንዳይሳተፉ የሚያግድ ነገር የሌለ መሆኑ ነው።»
ሸምጋዮችን በተመለከተ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዑሑሩ ኬንያታ ሌላ ፤ የኮንጎው ፕሬዚድንት ሳሱ እንጉየሱ አቋምም ሆነ ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
«የኮንጎው ፕሬዚዳንት ሳሱ እንጉየሶ፣ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት፣ ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ደጋፊ አለመሆናቸው ምሥጢር አይደለም። እናም፤ የሰላም ስምምነት በማድረግ ፤ ቦዚዜና ጆቶዲያ የሴትዮዋን አቋም የማዳከምና የማስወገድ ፤ በአንጻሩም እነርሱ ወደ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፖለቲካ መመለስ ነው የሚሹት።»
የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ፖለቲካ ከጎረቤቶች ተጽዕኖ ተላቆ አያውቅም። ዴቪድ ስሚዝ እንደሚሉት፤ ኮንጎና ቻድ በየጊዜው ጣልቃ ከመግባት የቦዘኑበት ጊዜ አልነበረም። የቀድሞዎቹ የአገሪቱ መሪዎችም መዲናይቱንና አካባቢዋን ካልሆነ በስተቀር አገሪቱን በመላ በአግባቡ የተቆጣጠሩበት ጊዜ አልነበረም። የማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ ጥሬ ሀብት ለብዙ ዓመታት በጎረቤቶች ተመዝብሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን ሊቀርብ የሚችል ጥያቄ ፤ ሸምጋዩ የኬንያው ርእሰ ብሔር የተገባላቸው ቃል ይኖር ይሆን? ጠቀሜታ ያለው የንግድ ውል ወይም ደግሞ በማዕድን ፍለጋና ማውጣት ረገድ፣ ኬንያ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችል ስምምነት ተደርጎ ይሆን?! የሚል ነው።
በቦንጊ በአሁኑ ጊዜ ዐቢዩ አነጋጋሪ ጉዳይ ለምርጫ መንገድ ጠራጊ የሆነው ሚያዝያ 19 ,2007 የሚካሄደው አገር አቀፍ የዕርቀ ሰላም ጉባዔ ነው። የሽግግሩ መንግሥት ባልደረባ የ 30 ዓመቱ ፍለሪ፣ ሁሉም በዐርቀ ሰላሙ ጉባዔ መገኘት እንደሚገባው የሚያጠያይቅ አይደለም። ማንም ሊገለል አይገባውም ብለዋል። አንድ አላፊ አግዳሚ ግን፤ አገሪቱን ለዚህ ሁሉ ቀውስ የዳረጓት ፤ በዋናነት ጆቶዲያና ቦዚዜ በመሆናቸው፤ በመጀመሪያ ንስሐ ይግቡ ብሏል። የተቃውሞው ወገን አባልና የቀድሞው የቦንጊ ከንቲባ ጆሰፍ ቤንዱንጋ በበኩላቸው በህዝብ ላይ ስለተፈጸመው በደል በይፋና በግልጽ መነገር አለበት፤ የድሞዎቹ 2 ቱ መሪዎች ለአዲሲቱ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፓብሊክ አንዳች ገንቢ ራእይ የሌላቸው ናቸው ፤ እነርሱ አገሪቱን ለማቃጠል እሳት ከለኮሱ በኋላ ፤ ሕዝቡን ለብዙ ሥቃይ ከዳረጉ በኋላ በደንታቢስነት መመለስ ይሻሉ ማለታቸው ተጠቅሷል። ቤንዱንጋ ለፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን እጩ ተወዳዳሪ አድርገው ቀርበዋል። ካታሪን ሳምባ ፓንዛ ግን የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን ሲረከቡ ወደፊት ራሳቸውን ለአመራር እጩ አድርገው እንደማያቀርቡ በይፋ የገቡት ቃል በመኖሩ ፣ የውድድር ተሳታፊ አይሆኑም።

Symbolbild UN Truppen in der Zentralafrikanischen Republik
ምስል picture alliance/AA/Str
Kenia Nairobi CAR Peace Initiative Bozize Djotodia
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ