1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰመርጃም ሬጌ የሙዚቃ ትርኢት 30ኛ ዓመት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2007

ከሳምንት በፊት ቦን አቅራቢያ በምትገኘው የኮሎኝ ከተማ ሰመርጃም የተሰኘው የሬጌ ዘፈን የሙዚቃ ትርኢት 30ኛ ዓመቱን አክብሯል። ከ30 000 በላይ ታዳሚዎችን ያስተናገደው የሶስቱ ቀን ድግስ የእውቁ የሬጌ ዘፋኝ ቦብ ማርሌይ ልጅን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ አርቲስቶችን ያሳተፈ ነበር።

https://p.dw.com/p/1G0Dw
30 Jahre Summerjam
ምስል DW/L. Abebe

የሰመርጃም ሬጌ የሙዚቃ ትርኢት 30ኛ ዓመት

እንደ ጎርጎሮሲያዊያን አቆጣጠር በሐምሌ ወር የመጀመሪያው የሳምንት መጨረሻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሬጌ ሙዚቃ አፍቃሪዎች በአውሮፓ ታዋቂ የሆነውን የሰመርጃም የሙዚቃ ትርኢት ለማየት ወደ ኮሎኝ ከተማ ይጓዛሉ።

ከ 30 ዓመት በፊት የሰመርጃም የሙዚቃ ትርኢት ሲጀምር የአንድ ቀን ትርኢት ነበር፣ ቦታው ደግሞ ትንሿ የጀርመን ከተማ የሎረላይ ውስጥ ነበር። ኋላ ላይ ግን የታዳሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ፤ የዝግጅቱ ቦታ ከስምንት ዓመት በኋላ ቦን አቅራቢያ ወደ ሚገኘው የኮሎኝ ከተማ፤ «የፉውሊንገር ዜ» ወይም የፉውሊንገር ሀይቅ አቅራቢያ ተዛወረ። በዚህ በውሃ በተከበበ ትንሽ ደሴት ላይ በተለይ ከአፍሪቃ እና ከካረቢክ ሀገራት የመጡ አርቲስቶች ተሳታፊ ነበሩ። ኋላም የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ተከተሉ። ሰመርጃም በሚታወቅበት የሬጌ ሙዚቃ ብቻ መወሰኑም ቀረ።

በዘንድሮው የሰመርጃም የሬጌ የሙዚቃ ትርኢት የዝነኛው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌይ ልጅ፤ ዳሚያን ማርሌይ፣ በብዛት በሂፕ ፖፕ ሙዚቃው የሚታወቀው ዋይ ክሊፍ ዦን፣ እና በአሁኑ ወቅት ጀርመን ውስጥ ዝናን ያተረፈው የራፕ ሙዚቃ ተጫዋች ክሮ ጥቂቶቹ አርቲስቶች ነበሩ።

በመጀመሪያው የሙዚቃ ትርኢት ቀን 12 ባንድ እና አርቲስቶች ሁለት መድረኮች ላይ አድናቂያቸውን አስደምመዋል። ከነዚህም ውስጥ ዘንድሮ 40ኛ ዓመቱን ያከበረው የሬጌ ባንድ ስቲል ፐልስ ነው። ባንዱ ስለ፤ ፍቅር፣ እኩልነት ፣ተሰሚ ስላጡ የተጨቆኑ ሰዎች እና ስለ መተሳሰብ ያነሳል። ሌላው የምሽቱን መድረክ የተቆጣጠረው፤ በተለይ በወጣት ጀርመናውያን ዘንድ የሚታወቀው የራፕ እና የፖፕ ሙዚቃ ተጫዋቹ ክሮ ነበር። የዛው የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ የሆነችው አኒያ ፤ ወደ ሰመርጃም ትርኢት ስትመጣ ዘንድሮው 13ኛ ጊዜዋ ነው። ከሁለት ዓመት ልጇ እና ባለቤቷ ጋር ሀይቁ ዳርቻ እየተንሸራሸረች፤ ስለ ሰመርጃም የመጀመሪያ ምሽት የሚሰማትን አካፍላናለች።«እውነቱን ለመናገር ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙዚቃ ትርኢቱ ገቢ ላይ ያተኮረ መሆኑን ማስተዋል ተችሏል። የትናንቱን ክሮን የተመለከትን እንደሆን፤ ለነገሩ ሌሎች የተሻለ ባንድ የያዙ የሙዚቃ ትርኢቶች ተፈጥረዋል። እንደዛም ሆኖ ደስ እያለን ወደዚህ እንመጣለን።

30 Jahre Summerjam
የሰመርጃም ሁለተኛው መድረክምስል DW/L. Abebe

እንደ አኒያ ትርኢቱ በሚዘጋጅበት ከተማ የማይኖሩ ታዳሚያን ደግሞ ለድንኳን መትከያ በተዘጋጀ ስፍራ ደማቅ ቀለም ያሏቸው ድንኳናቸውን መትከል የጀመሩት ገና አንድ ሳምንት አስቀድመው ነው። ሰመርጃም 30ኛ ዓመቱን ከመድፈኑ ባሻገር የዘንድሮውን ትርኢት ከወትሮው ለየት ያደርገው ፤ ጀርመን ውስጥ በጋ ከገባ ወዲህ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት ሳምንት በመሆኑም ነበር። እስከ 40 ሴንቲግሬድ ሙቀት በተለካበት ሰዓት ፤ አብዛኞቹ ሀይቁ ውስጥ እየዋኙ ራሳቸውን አቀዝቅዘዋል። ከዋና ወጥታ ሳሩ ላይ ጋደም ያለችው ታዳሚ ቲና፤ « በሰመርጃም ወቅት እንደዚህ አይነት ሙቀት ከታየ ቆይቷል ። ለነገሩ ግን ሰመርጃምን በመጥፎ አየር አላስታውሰውም። በርግጥ ዝናብ ጥሎ ያውቃል። ቢሆንም ስሜት የሚስቡ አጋጣሚዎች ናቸው ትዝ የሚሉን። በአንድ ወቅት አልፋ ብሎንዲ እየዘፈነ ነበር፤ ያኔ ፀሀይዋ ዳመናውን ሰንጥቃ ወጣች፤ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች የማይረሱ ናቸው። »

በሶስት ቀኑ የሙዚቃ ትርኢት ፤ ከሙዚቃ ባሻገር ሰው ዘና እንዲል እና ዕረፍት እንዲሰማው የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩበት። መመገብ፣ መደነስ፣ አልባሳት እና ጌጣ ጌጦች መሸመት፤ መዋኘትን የመሳሰሉት። ታድያ በዚህ ዝግጅትም ላይ አንዳንድ ጎራ ያሉ ኢትዮጵያውያንም አልጠፉም።

የሰመርጃም የሶስት ቀናት መግቢያ ዋጋ ዘንድሮ 114 ዩሮ የነበረ ሲሆን፤ ቲኬቱ ሁሉ ገና ሳምንት ሲቀረው ተሸጦ አልቆ ነበር። የ 16 ዓመቱ ብሪታኒያዊ አሌክስ እና ጓደኞቹ ግን አስቀድመው መግቢያቸውን አዘጋጅተዋል። ወጣቶቹ ወደ ሰመርጃም ብቻ ሳይሆን ጀርመን ሀገር ሲመጡም የመጀመሪያቸው ነው።« እዚህ በጣም ደስ ይላል። ፀሀያማ ነው። እስካሁን የነበሩት የሬጌ የሙዚቃ ትርኢቶች ደስ ይሉ ነበር። ዛሬ ደግሞ ዳሚያን ማርሌይ ይጫወታል። ስለዚህ ሁሉም ነገር አስደሳች ይሆናል። »

30 Jahre Summerjam
የሙዚቃ ትርኢት እና ዋናምስል DW/L. Abebe

የቦብ ማርሌይ ልጅ ዳሚያን ማርሌይ ወደ መድረኩ ከመውጣቱ በፊት፣ ሌሎች 14 ከተለያዩ ሀገር የመጡ አርቲስቶች ሙዚቃቸውን አቅርበዋል። ለምሳሌ ጃማይካ ያደገችው የሬጌ ተጫዋች ኤይለን ። እንደ ኤይለን ከጃማይካ የመጣው ሌላው አቀንቃኝ ታይረስ ራይሊ ነበር። ከ 15 ዓመቱ ጀምሮ የሙዚቃውን ዓለም የተቀላቀለው ታይረስ ራይሊ ከአለም አቀፍ ዘመናዊ ሬጌ አቀንቃኞች ተርታ ይሰለፋል።

በመጨረሻም በብዙ የሬጌ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቦብ ማርሌይ የመጨረሻ ወንድ ልጅ ዳሜያን ማርሌር ወደ መድረኩ ወጣ፤ እግሩ ጋር የሚደርሱ፣ በእንግሊዝኛ አጠራሩ «ድሬይድስ» ጸጉሩን ወዲህ እና ወዲያ እያደረገ፤ ትርኢቱን በቀዳማዊው አፄ ሀይለ ስላሴ ንግግር ጀመረ። እንዲህ እያለ ሰመርጃም ሶስተኛው ቀን ላይ ደረሰ። ፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሚነገርባት የካሪቢክ ደሴት ማርቲኒክ የመጣው ያንስ ኦዱር ፤ ከመዝጊያው ቀን አርቲስቶች አንዱ ነበር።

ትርኢይቱን ሲከታተል ከነበሩ ታዳሚዎች አንዱ ከፈረንሳይ ሀገር ከአስር ጓደኞቹ ጋር የመጣው ፍራንሲስ ነው፤ እናቱ ጀርመናዊ በመሆኗ ጀርመንኛም ይናገራል።« በጣም ደስ ስለሚለን በየዓመቱ እንመጣለን። ፈረንሳይ ውስጥ ሰመርጃም የለም። ስለዚህ እዚህ መጥተን ሶስቱን ቀን ድንኳን ጥለን እንደሰታለን። ሙዚቃው እጅግ ቆንጆ፤ አሪፍ ነበር»

በሰመርጃም የሙዚቃ ትርኢት ዘንድሮም አረንጓዴ ፣ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ እና የኢትዮጵያ አልባሳት ይሸጡ ነበር። የአንድ ሱቅ ባለቤት የሆኑት ጃማይካዊ ራይና ኤስቴሪያሻ ጸጉር እና ፂማቸውን ሲያሳድጉ 40 ዓመታት ተቆጠሩ ይላሉ። አንገታቸው ላይም ትልቅ መስቀል አድርገዋል።« የኢትዮጵያውን መስቀል፤ አንድ ጊዜ ወደ ሻሸመኔ የሄደ ጓደኛዬ ነው አምጥቶልኝ የገዛሁት። ምክንያቱም እንደ አንድ ራስታ፣ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት። »

30 Jahre Summerjam
ጃማይካዊ ራይና ኤስቴሪያሻ ጸጉር እና ፂማቸውን ሲያሳድጉ 40 ዓመታት ተቆጠሩምስል DW/L. Abebe

ከስዊትዘርላንድ የመጣችው ሰሎሜ አንድ ሱቅ ቁጭ ብላ ፀጉሯን ትጎነጎናለች። ከዚህ የሙዚቃ ድግስ ምን እንደምትጠብቅ ጠይቄያት ነበር።« ከዚህ የሙዚቃ ድግስ ጥሩ ስሜት፣ ጥሩ ሙዚቃ ፣ ጥሩ ሰዎች እና ሰላም እጠብቃለሁ።

የሰመርጃም ሙዚቃ፤ ከፍተኛ ንፋስ እና መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ በመምጣቱ ለአጭር ጊዜ ቢቋረጥም፤ የተፈራው ሳይጥል ቀርቶ ሙዚቃው ቀጠለ። ላለፉት 30 ዓመታት በሬጌ ሙዚቃው የሚታወቀው ጃማይካዊው ቤረስ ሀሞንድ ሙዚቃዎቹን ለህዝብ ያቀርብ ጀመር። ሲያመሻሽም፤ በተለይ በሂፕ ሆፕ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው የሀይቲ ተወላጅ ዋይ ክሊፍ ዦን የመዝጊያውን መድረክ ተቆጣጠረ። ዋይ ክሊፍ ዦን ፤ ከታዋቂዋ ዊህትኒ ሁስተን እና ማይክል ጃክሰን በህይወት በነበሩ ጊዜ አብሯቸው ስለነበረው ቆይታ ሙዚቃቸውን እያሰማ በማስታወስ ፤ ትርኢቱን ቀጠለ።

ዝግጅቱን በድምፅም ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ