1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰማያዊ እና አረና ትግራይ ፓርቲዎች የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ

ዓርብ፣ ጥቅምት 24 2010

የሰማያዊ እና አረና ትግራይ ፓርቲዎች በሳምንቱ መጨረሻ ተከታታይ ቀናት ቅዳሜ እና እሁድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ለዶቼ ቬለ ገለፁ። እንዲያም ሆኖ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፉ እዉቅና እንደተነፈገ አመልክቷል። አረና በበኩሉ ከሚመለከተዉ አካል ምላሽ እየጠበቀ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2mw3c
Demonstration der Blue Party in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል DW

Blue party /on lone version/ - MP3-Stereo

ሠማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ አረና ትግራይ በመቀሌ በመጭው እሁድ የሚያካሂዱት ሠላማዊ ሠልፍ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች እና የንጹሀን ዜጎች ግድያ ይቁም በሚል የሚካሄድ መሆኑን የየፓርቲዎቹ ሃላፊዎች ገልጸዋል። የሠማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን ባልቻ ለዶቼቬለ እንደገለጹት በመጭው እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ ፓርቲያቸው ሊያካሂድ ያሰበው ሠላማዊ ሠልፍ በሀገሪቱ ውስጥ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶች መንግሥት በቂ ምላሽ እንዲሰጥ መጠይቅ ነው። ባለፈው መስከረም 28 ፓርቲያቸው ሠላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ቢያቅድም እውቅና ያገኘው ዘግይቶ በመሆኑ መሠረዙን የሚያስታውሱት አቶ ጌታነህ የፊታችን እሁድ ጥቅምት 26 ቀን ተቆርጦለት የነበረው ሠላማዊ ሠልፍም በቂ የፖሊስ ኃይል የለም በሚል በዛሬው እለት እውቅና እንደተነፈገው  በቃል ተገልጾልናል ሲሉ ለዶቼቬለ አብራርተዋል። ፓርቲው ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ የሠላማዊ ሠልፎች እውቅና መነፈጉን በማመልከትም ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ለማስጠበቅም አቤት እንደሚልም ገልፀዋል። የአረና ትግራይ ፓርቲ በበኩሉ በመጭው ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን በመቀሌ ከተማ ሠላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚመለከተውን አካል አሳውቆ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ የመቀሌው ሠላማዊ ሠልፍ ነቀምት ላይ ህይወታቸው ከጠፋ ሰዎች ማንነት ጋር የተገናኘ ነው በሚል መረጃዎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ሲሠራጭ ታይቷል። የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ እንደሚሉት ግን የቅዳሜው ሠላማዊ ሠልፍ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመለከት ነው። እንደ አቶ አብርሃ ገለጻ ሠላማዊ ሠልፉ እንዲካሄድ የህዝብ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ከአሁን ቀደም ፓርቲው ባካሄዳቸው ስብሰባዎች አረጋግጧል።ይህን እንጂ ሠላማዊ ሠልፉ በመንግሥት በኩል እውቅና ቢነፈገው ይህንኑ ለህዝብ እንደሚያሳውቁ እና ፍርዱንም ለህዝብ እንደሚተዉ አቶ አብርሃ ጨምረው ገልጸዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሸዋዬ ለገሠ