1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን አሜሪካ የነጻ ንግድ ማሕበርና ዕርምጃው

ረቡዕ፣ ነሐሴ 16 1999

የሰሜን አሜሪካ የነጻ ንግድ ማሕበር የናፍታ ዓባል መንግሥታት መሪዎች ካናዳ ውስጥ ያካሄዱትን የሁለት ቀናት ጉባዔ ባለፈው ማክሰኞ አጠናቀዋል። የድርጅቱ ጉዞ ወዴት ነው? ዓላማና ግቡስ?

https://p.dw.com/p/E0ck
ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ
ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽምስል AP

በአሕጽሮት ናፍታ በመባል በሚታወቀው ማሕበር ውስጥ የተሰባሰቡት ሶሥት ሃገራት የአሜሪካ፣ የካናዳና የሜክሢኮ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔውን ያጠቃለሉት ከአውሮፓና ከእሢያ አኳያ እየጠነከረ የሄደውን ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ፉክክር ለመቋቋም ቆርጠው መነሣታቸውን በማስረገጥ ነው። በሌላ በኩል ማሕበሩ የአካባቢውን ሕዝብ ስሜት ያላደመጠ፤ በመሪዎችና በተጠቃሚ ኩባንያዎች ፍላጎት የሚመራ ነው ሲሉ ነቀፌታ የሚሰነዝሩት ታዛቢዎችና የሕብረተሰብ ቡድኖች ብዙዎች ናቸው። እንደነርሱ ከሆነ በአካባቢው ነጻ ንግድ የታላላቁን ኩባንያዎች ያህል ድሃው ሕዝብ ተጠቃሚ አልሆነም።

ከ 13 ዓመታት ገደማ በፊት፤ እ.ጎ.አ. በ 1994 በአሜሪካ፣ በካናዳና በሜክሢኮ መካከል የጸናው የሰሜን አሜሪካ የነጻ ንግድ ውል የሶሥቱን ሃገራት የንግድ ግንኙነት በሰፊው መክፈቱ ይታወሣል። ማሕበሩ ተቋቁሞ ሥራውን ከጀመረ ወዲህ የአካባቢው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ከ 293 ወደ 883 ቢሊዮን ዶላር፤ ማለት በሶሥት ዕጅ ገደማ ማደጉ ነው የሚነገረው። እርግጥ ይህ የትስስሩ አንድ ገጽታ ይሁን እንጂ በሌላ በኩል የታላላቁን ኩባንያዎች ያህል ሰርቶ-አደሩ ሕዝብ አልተጠቀመም። የናፍታ ውል ከሰፈነ ወዲህ የሶሥቱም ሃገራት ገበሬዎች ገቢ አቆልቁሏል። በተለይም ፉክክሩን መቋቋም አቅቷቸው መሬታቸውን ያጡት አነስተኛ ገበሬዎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ናችው።

ፖሊሲው ከሕዝብ ይልቅ ለኩባንያዎች የቀረበ መሆኑ

ይህ የተሳሳተ ወይም እንበል ሚዛን ያልጠበቀ ፖሊሲ ምንም እንኳ ወዲያው ጎልቶ መታየቱ ባይቀርም ናፍታን እንዲያውም ከኩባ በስተቀር የአካባቢውን ሃገራት ወደጠቀለለ በአሕጽሮት FTAA የአሜሪካዎች የነጻ ንግድ ማሕበር ወደተሰኘ የነጻ ንግድ ክልል ለማስፋፋት ጥረት መደረጉ አልቀረም። ይህም አነስተኛውን ገበሬ እስከ ተከታይ ትውልድ ድረስ ሊዘልቅ የሚችል የምግብ ዋስትና እንዳሳያሳጣ የሚሰጉት ታዛቢዎች ብዙዎች ናችው። ባለፉት ዓመታት 34 የሚሆኑ የአካባቢው ሃገራት ናፍታን ወደ ማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ፤ እስከ ካራይብም ጭምር በማስፋፋት የተጠቀሰውን የአሜሪካዎች የነጻ ንግድ ማሕበር ለመፍጠር ውጣ-ውረድ ሲሉ ቆይተዋል።

ይህም ላይ ላዩን በጎ ይምሰል እንጂ ከሁሉም በላይ የንግድ ጥቅምን የሚያስቀድም በመሆኑ በአካባቢ ተፈጥሮ፣ እንዲያም ሲል በድሃው ሕብረተሰብ ሕልውናና በሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ብርቱ አደጋ የደቀነ ሆኖ መገኘቱ ዛሬ በየጊዜው የሚሰማ ጉዳይ ነው። ስጋቱ በእርግጥም ያለ ምክንያት አይደለም። የእስካሁኑ የሰሜን አሜሪካ የነጻ ንግድ ማሕበር የናፍታ ይዞታ ለብዙዎች ሠርቶ-አደር ቤተሰቦችና ለአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ የቅዠትን ያህል ነው የሆነው። በናፍታ ውል የተነሣ በአሜሪካ 750 ሺህ የሥራ ቦታዎች እንዳልነበሩ ሲሆኑ የኋላ ኋላም የሠራተኛው ገቢ በአማካይ 23 ከመቶ ሊያለቁል በቅቷል።

የሜክሢኮስ ተጠቃሚነት እስከምን ድረስ ነው

በሜክሢኮም የአምራቹ ሠራተኛ ገቢ ከ 1995 እስከ 1999 21 ከመቶ ሲቀንስ እስካሁን ያገገመው በጥቂቱ ብቻ ነው። በአጠቃላይ የናፍታ ውል ከጸና ወዲህ በድህነት የሚኖረው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ከቀድሞው ከፍ ብሏል። በአካባቢው ሰፊ የነጻ ንግድ ክልል ለመፍጠር በተያዘው ጥረት አንዱና ትልቁ ችግር ንግግሩ የሕዝብን ፍላጎትና ስጋት የሚገባውን ያህል ያካተተ አለመሆን ነው፤ ነበርም። እንግዲህ የንድዱ ፖሊሲ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ በየጊዜው የተደረገው ጥሪ ብዙም ሰሚ ጆሮ አላገኘም። በሌላ በኩል ዜጎች በዚህ መልክ በጨለማ ውስጥ እንዲገቱ ተደርገው ሳለ ታላላቆቹ ኩባንያዎቹ ግን በፖሊሲው ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ፤ ፍላጎታቸውንም እንዳሻቸው ለማራመድ ይችላሉ።
ለምሳሌ የአሜሪካን መንግሥት ተደራዳሪዎች የሚያማክሩት፤ የድርድሩን ይዘት ቀድመው ለማግኘት የሚችሉትም የኩባንያዎች ተጠሪዎች ናቸው። የአሜሪካዎችን የነጻ ንግድ ደምቦች ራሳቸው እንደሚፈልጉት ለማስረቀቅ ሥልጣን አግኝተዋል ለማለት ይቻላል። እንደ ብዙው የግሎባላይዜሺን የችግር ቅርስ እዚህም የሕዝብን ቁጣ የሚቀሰቅሰው ይሄው ሃቅ መሆኑ ነው። በተያዘው መንገድ የሚሰፍን ውል የሠራተኞችን መብት የሚራገጥና ሙያተኞችን የሥራ ዋስትናን የሚያሳጣም ነው የሚሆነው። የሠራተኞች ጥቅም የሚጠበቅበትን ሁኔታ በሚገባ ያላስቀመጠው የናፍታ ውል ለዚህ በቂ ምሳሌ ነው።

ኩባንያዎች ነቅለው ወደ ሌላ አገር እንደሚሄዱ በማስፈራራት የሠራተኛውን ደሞዝ ዝቅ አድርገው ለማቆየትና የሙያ ማሕበራትን ግፊትም በድን ለማድረግ መጣራችው የተለመደ የተጽዕኖ ዘዴያቸው ሆኗል። በኮርንዌል ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሠረት የሰሜን አሜሪካው የነጻ ንግድ ማሕበር ውል ከሰፈነ ወዲህ ወደ ውጭ በመኮብለል ዛቻ ሠራተኛውን ለመጫን የሞከሩት ኩባንያዎች ከጠቅላላው ሁለት ሶሥተኛው ይሆናሉ።

የፖለቲከኞችና የሕዝብ አመለካከት አለመጣጣም

ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ እርግጥ ፖለቲከኞች የሚናገሩት ሌላ ነው። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆርጅ-ደብልዩ-ቡሽ ትናንት ከካናዳው ጉባዔ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አገራቸው ከካናዳና ከሜክሢኮ ጋር የምታደርገው ትብብር ብልጽግናን በማራመድ ላይ ያለመ መሆኑን አመልክተዋል። ቡሽ እንዲህ ይላሉ “የውይይቱን መንፈስና ለምን ጠቃሚ ነው ብዬ እንደማስብም ልነግራችሁ እወዳለሁ። ከካናዳና ከሜክሢኮ ጋር በቅርብ መሥራታችን ለሕዝቦቻችን የሚጠቅም ሲሆን ይሄም በየጊዜው እየተገናኘን መደበኛ ንግግር እንድናካሂድ ጥሩ ምክንያት የሚሆን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ብልጽግናን ለማራመድ ጥርጊያ ለማመቻቸት እንፈልጋለን። የካናዳ ማሕበራዊ ኑሮ ባለበት ተጠናክሮ መቀጠሉ፤ ብልጽግናም ወደ ሜክሢኮ መስፋፋቱ የምንሻው ነገር ነው”

አባባሉ ባልከፋም ነበር። ችግሩ ሕዝብ ያልተጠየቀበት፣ ስጋቱ ያልተደመጠበትና በሂደቱ ያልተሳተፈበት ትስስር ለብዙሃኑ የሚዳሰስ ብልጽግናን ሊያስከትል አለመቻሉ ላይ ነው። ከዚህ አንጻር ታዲያ ነጻ የንግድ ክልል የማስፋፋቱ ጥረት ተገቢውን ፈር ይዟል ለማለት ብዙም አያስደፍርም። የተለያዩት ነጻ ውሎች፤ እንዲሁም የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የሚያራመዱት በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረ የዕድገት ሞዴል ወይም ዘይቤ በዓለም ላይ ለተፈጥሮ ይዞታ ዝቤት ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጓል። የውጭ ዕዳችውን ለመክፈል ደኖቻቸውን የሚመነጥሩት፣ ባሕሮቻቸውን ከመጠን በላይ አሣ በማጥመድ የሚያራቁቱትና ሌላም የተፈጥሮ ሃብታቸውን የሚመዘብሩት የደቡቡ ዓለም አገሮች ጥቂቶች አይደሉም። በሜክሢኮ የናፍታ ውል ከሰፈነ ወዲህ ከ 15 የሚበልጡ የአሜሪካ የእንጨት ምርት ኩባንያዎች ሲሰፍሩ የተፈጥሮው ዝቤት በፍጥነት እያደገ ነው የመጣው። በጉዌሬሮ ክፍለ-ሐገር ብቻ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ አርባ በመቶው ደን ወድሟል። ይህም የመሬት መሸርሸርና የዘር ጥፋት እንዲከተል ነው ያደረገው።

የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲና የኣባቢው ታዳጊ ሃገራት

አሜሪካ በአካባቢው ለማስፋፋት የምትፈልገው ነጻ ንግድ በተለይ በብልጽግና ደረጃ ላይ በማይገኙት አገሮች ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዛኝ የሚሆንበት ሌላም ምክንያት አለ። የነጻው ንግድ ስምምነት የማዕከላዊው፣ የደቡብ አሜሪካና የካራይብ አገሮች ትምሕርትና ጤና ጥበቃን የመሳሰሉትን የማሕበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ወደ ግል ዕጅ እንዲያሻግሩ ሊጋፋ የሚችል ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ሥርቶ-አደሩንና ዝቅተኛውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ለውጡ ከአሁኑ በአንዳንድ ቦታዎች እየተካሄደ ሲሆን መሠረታዊው አገልግሎት የሚጠይቀውን ወጪ መክፈል ተስኗቸው የሚሰቃዩት እነዚሁ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች ናችው። ለምሳሌ በቦሊቪያ ከተማ በኮቻባምባ በውሃ አገልግሎቱ ዘርፍ ወደ ግል ዕጅ መሻገር ሳቢያ የዚህ መሠረታዊ ጸጋ ዋጋ በአንዴ በዕጥፍ እስከመናር ደርሶ ነበር።

የሰሜን አሜሪካው የነጻ ንግድ ድርድር በዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ላይ ሲታይ እንደቆየው ሁሉ የጠንካሮቹ መንግሥታት ተጽዕኖ ጎልቶ የሚታይበት ነው። አሜሪካ ለምሳሌ ድርድሩን ተጠቅማ ሌሎቹ አገሮች የጂን ምርቶቿን እንዲቀበሉ ለመገፋፋት ትሞክራለች። በዚህም የተነሣ ነጻው ንግድ በዛሬይቱ ዓለማችን የብዙሃኑን ጥቅም ያከበረ ሆኖ ሊራመድ መቻሉን አጠያያቂ የሚያደርጉት ጥቂቶች አይደሉም። ከዓመት ወደ ዓመት ብቅ የሚሉት መረጃዎችም ይህንኑ ግምት የሚያጠናክሩ ናቸው። በዓለም ንግድ ላይ ከ 60ኛዎቹ እስከ 90ኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ የተፋጠነ ዕድገትና የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ በታየባችው አርባ ዓመታት ውስጥ በዓለምአቀፍ ደረጃም ሆነ በአንድ አገር የውስጥ ግንኙነት ንጽጽር የድሃና የሃብታሙ ልዩነት ይባስ እየከፋ ነው የመጣው። ነባሩ ሁኔታ ካልተቀየረ ደቡቡ ዓለም ከሰሜኑ ተጽዕኖ ሊላቀቅ የሚችል አይሆንም፤ የወደፊት የዕድገት ተሥፋውም የሩቅ ሕልም ሆኖ ነው የሚቀረው።

የተሻለው አማራጭ ምን ሊሆን ይችላል?

ችግሩ ባለበት እንዳይቀጥል ከተፈለገ ምርጫው አንድ ብቻ ነው። በአሜሪካም ሆነ በሌላው ክፍለ-ዓለም የነጻ ንግድ ውሎች ማሕበራዊና የተፈጥሮ ጥበቃ ሃላፊነት በተዋሃደው አማራጭ ላይ ሊመሠረቱ ይገባቸዋል። እስካሁን በአጠቃላይ በዓለም ንግድ ላይ የታየው ድርድር የዶሃውን ለማስታወስ ይቻላል፤ ብዙም ለተሥፋ ምንጭ የሚሆን አይደለም። ዓለምአቀፉን ንግድ ለማለዘብና የታዳጊ አገሮችን ድርሻ ለማሻሻል ተብሎ በዶሃ የተነሣው ድርድር ዛሬ ከስድሥት ዓመታት በኋላም ይህ ነው የሚባል ፍሬ ሊታይበት አልቻለም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አሜሪካን የመሳሰሉት የበለጸጉ መንግሥታት ለገበሬዎቻችው የሚሰጡትን ድጎማ ለመቀነስና ገበዮቻቸውን ለመክፈት በተገቢው መጠን ዝግጁ አለመሆናቸው ነው።

ለዚሁ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር መክሸፍ በተለይ ተጠያቂ የሆነችው አሜሪካ በተናጠል ከአንድ አገር ወይም ከአካባቢ መንግሥታት ቡድኖች ጋር ባይላተራል ውል ማስፈኑን የተጽዕኖ መሣሪያ አድርጋ ትጠቀምበታለች። ይህ ዝንባሌ እየጠነከረ የሚሄድ ሲሆን በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ በሚሰፍን ውል የጋራ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉትን ታዳጊ አገሮች በተናጠል እንዲመቱ ጥርጊያን የከፈተ ነው። አንድ የማዕከላዊውም ሆነ የደቡብ አሜሪካ አገር ወይም ሃገራት በዚህ የተናጠል ድርድር የዋሺንግተንን ተጽዕኖ ሊቋቋም የሚችል፤ የሚችሉ አይሆኑም። ዛሬ በናፍታም ሆነ በካፍታ፤ ማለት የማዕከላዊ አሜሪካ የነጻ ንግድ ማሕበር ደረጃ ያለው ሃቅ ይሄው ነው።