1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ሙከራና ዉግዘቱ

ሰኞ፣ የካቲት 11 2005

የቀድሞዉ ዩናይትድ ስቴትስ የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ጥምረት ሊቀመንበር አድሚራል አርተር ራድፎርድ መስከረም 1956 ለሐገራቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ያካፈሉት ዕቅድ ያን በእንጥልጥል የቆመዉን ጦርነት ሐገራቸዉ የኮሪያ ልሳነ-ምድርን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የምትችልበትን ሥልት ያካተተ ነበር።

https://p.dw.com/p/17gcJ
SA-3 ground-to-air missiles are displayed before a portrait of former North Korean leader Kim Il-Sung during a military parade to mark 100 years since the birth of Kim Il-Sung, the country's founder, in Pyongyang on April 15, 2012. The commemorations came just two days after a satellite launch timed to mark the centenary fizzled out embarrassingly when the rocket apparently exploded within minutes of blastoff and plunged into the sea. AFP PHOTO / Ed Jones (Photo credit should read Ed Jones/AFP/Getty Images)
የሰሜን ኮሪያ ሚሳዬልምስል Ed Jones/AFP/Getty Images


ሶቭየት ሕብረት ከተንኮታኮች ከሃያ-ዓመት በለጠ።ቻይና አሁንም ከሰሜን ኮሪያ ጎን እንደቆመች ነች። ዋሽንግተን ተባባሪዎችዋን አስከትላ ከሞስኮ፣ ቤጂንግ-ፒዮንግያንግ ኮሚንስቶች ጋር በተዋጋችበት ዘመን ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ያሰፈረችዉን ጦሯን ታጠናክራለች። ፒዮንግዮንግ ዋሽንግተንና ተባባሪዎቿን ታወግዛለች።እራሷ ግን አዉዳሚ ጦር መሳሪያ ትታጠቃለች።ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን ታስፈራራለች።ግን በተቃራኒዉ ደቡብ ኮሪያና ጃፓንን ለዉጊያ ታደራጃለች።ደሞ በመሐሉ ድርድር እያሉ የሠላም ወዳዱን ዓለም ቀልብ ያንጠለጥላሉ።ወዲያዉ ይፋረሳሉ።ፒዮንግዮንጎች ኑኩሌር ቦምብ ያፈነዳሉ።ዋሽግተን-ብራስልሶች፣ ሶል፣ ቶኪዮዎች፣ ይፎክራሉ፣ ፒዮንግያንጎችን ያስቀጣሉ።ዓለምን ያሸማቅቃሉ።ሐምሳ ዘመናቸዉ። ቀጥለዋልም።ግን ለምን-ደግሞስ እንዴት?ላፍታ አብረን እንጠየቅ።


ፒዮንግዮንግ አዲስ ወጣት መሪ። ኪም ጆንግ ኡን።አዲስ ዓመት። ጥር አንድ-2013 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያን አቆጣጠር ነዉ)።አዲስ መልዕክት እና ምናልባት በጎ ተስፋ።«የሐገሪቱን መከፋፈል ለማስወገድ እና ዳግም ለማዋሐድ በሰሜንና በደቡብ መካካል ያለዉን ፍጥጫ ማስወገድ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ።ያለፈዉ ዘመን እንደሚያመለክተዉ በኮሪያዎች መካካል ያለዉ ፍጥጫና ጠብ የሐገሪቱን ሕዝብ ከጦርነት ከመዶል ሌላ የፈየደዉ የለም።»

ዋሽንግተን።አዲስ ዓመት።አሮጌ፥ ሽማግሌ መከላከያ ሚንስትር።ሊዮን ፓኔታ።አሮጌ-መልዕክት እና ምናልባት ቀቢፀ ተስፋ።

«ሰሜን ኮሪያ በጠብ ጫሪነት ባሕሪዋ መቀጠሏ በጣም ያሳስበናል።ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘረዉን ማንኛዉንም ትንኮሳ ለመቋቋም ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን።እንደተዘጋጀንም እንቀጥላለን።ይሁንና በስተመጨረሻዉ የዓለም አቀፉ ቤተ-ሰብ አባል መሆኑ እንደሚሻላቸዉ ይወስናሉ የሚል ተስፋ አለኝ።»

እና በአዲሱም ዘመን የሩቅ ጭላንጭሉ አዲስ ተስፋ-ሳይጀመር፥ አሮጌዉ ዉዝግብ፥ ዛቻ፥ ፉከራ፥ ቀጠለ።የኮሪያ ልሳነ-ምድር።


ኪም ጆንግ ኡን ታሕሳስ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ የሞቱትን አባታቸዉን ኪም ጆንግ ኢልን የተኩት አባታቸዉ በሞቱ-በሳልስቱ ነበር።የታላቁን መሪ ታላቅ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ግን የታላቁ መሪ ታላቅ ሐዉልት እስኪጠናቀቅ፣ በታልቅ መሪዉ ሞት ልቡ የተሰበረ ሕዝባቸዉ እስኪፅናና መጠበቅ ነበረባቸዉ።

የታላቁን መሪ ስንብት ከመምራቱ፣ ትልቁን ሐዉልት ከማስቀረፅ፣ መመረቁ ጥድፊያ አረፍ-ዘና ሲሉ ሌላ ትልቅ ሥራ-ጠበቃቸዉ።የአያታቸዉ የኪም ኢል ሱንግ መቶኛ የልደት በዓል።በኪም ጆንግ ኡን እምነት የትልቆቹ ትልቅ፥የአዋቂዎቹ አዋቂ፥ የብልሆቹ-ብልሕ፣ ኪም ኢል ሱንግ የሶል ጠላቶቻቸዉን፥ የዋሽግተን ደመኞቻቸዉን ለማርበትበት የወጠኑትን ልጃቸዉ ኪም ጆንግ ኢል በሁለት ሺሕ ስድስት በይፋ ገቢር አድገዉታል።የኑክሌር ቦምብ ሙከራ።


አዉዳሚዉን ቦምብ ከጃፓን፥ ደቡብ ኮሪያ አልፎ በኪም ኢል ሱንግ አገላለፅ ከ«ሰዉ በላይቱ» አሜሪካ ግዛት ላይ የሚዘረግፈዉን የሩቅ ርቀት ሚሳዬልንም ኪም ጆንግ ኢል አሰርተዉታል።ልጅ-አባቱን ሆነ-ይሏል-እንዲያ ነዉ።ግን ሳያስሞክሩት ሞት ቀደማቸዉ። ኪም ጆንግ ኡንም እንዳባታቸዉ፥ ያባታቸዉ ልጅ መሆናቸዉን ማስመስከር አለባቸዉ።የአያታቸዉ መቶኛ የልደት በዓል ለዚያ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ።

የአያታቸዉን ዉጥን፣ የአባታቸዉን ሥራ በፍተሻ ለማረጋገጥ የአባታቸዉን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ መያዝ አለባቸዉ።ሚያዚያ-አስራ አንድ ሁለት ሺሕ አስራ ሁለት።የዲሞክራሲያዊት ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያ የሠራተኛ ማሕበር ጉባኤ ሊቀመንበሩ አድርጎ መረጣቸዉ።ሚያዚያ አስራ-ሰወስት ሁለተኛዉን ትልቅ ሥልጣን ያዙ።የዲሞክራሲያዎት ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያ ብሔራዊ የመከላከያ ኮሚቴ ዋና ሊቀመንበር ሆኑ።

ሚያዚያ አስራ አምስት።የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስታዊ ሥርዓት መስራች የኪም ኢል ሱንግ መቶኛ የልደት በዓል።በዓሉን በልዩ ሁኔታ የሚያበስረዉ ኡንሐ-3 ሚሳዬል ማለዳዉ ላይ ተቀባበለ።ሰላሳ-ሜትር ይረዝማል።ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል።ተተኮሰ።ግን ወዲያዉ ተፈረካከሰ።እና ሙከራዉ ከሸፈ።ኪም ጆንግ ኡንና ታማኞቻቸዉ አፈሩ።ተከዙም።ግን በዓል ነዉ። የታላቁ መሪ ታላቅ የልደት በዓል ፒዮንግዮግ በድግስ፥ ጭፈራ፣ በቀረርቶ ትቀልጥ ገባች።


የኮሪያዉ ጦርነት ኢትዮጵያዉያን ወታደሮችን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ በላይ ሕይወት ጠፍቶበታል።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ቆስሏል።ተሰዷል፥ ተፈናቅሏልም።ኮርያን ለሁለት ሰንጥቋታል።ግን አሸናፊም-ተሸናፊም አልተለየበትም። በ1953 ከተፈረመዉ ተኩስ አቁም ዉል ባለፍ ፍፃሜዉም አስካሁን በይፋ አልታወጀም።

የቀድሞዉ ዩናይትድ ስቴትስ የጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ጥምረት ሊቀመንበር አድሚራል አርተር ራድፎርድ መስከረም 1956 ለሐገራቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ያካፈሉት ዕቅድ ያን በእንጥልጥል የቆመዉን ጦርነት ሐገራቸዉ በበላይነት የምትወጣበትን አለያም የኮሪያ ልሳነ-ምድርን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የምትችልበትን ሥልት ያካተተ ነበር።

ደቡብ ኮሪያን ቦምብ ማስታጠቅ።ወይም የአዉቶሚክ ቦምብ ማስፈር።ጦርነቱን ለማስቆም አሜሪካኖች እራሳቸዉ በ1953 የፈረሙት ዉል አንቀፅ አስራ-ሰወስት ዲ ተፋላሚዎች አዳዲስ ጦር መሳሪያዎችን ወደ ኮሪያ ልሳነ-ምድር እንዳያስገቡ ይደነግጋል።

አድሚራል ራድፎርድ የዉሉን ይዘት ከዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቢረዱም ዕቅዳቸዉን አልሰረዙም። ባንድ ወቅት እንደሳቸዉ ባለአምስት ኮኮብ ጄኔራል ለነበሩት ለፕሬዝዳት ዳዊት አይዘናወር አሳወቁ። ፕሬዝዳንቱ የራድፎርድ ዕቅድ ገቢር እንዲሆን አዘዙ።ዉሉ ተጣሰ።በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ከ1958 ጀምራ ኑክሌር የተሸከሙ ሚሳዬሎች፥ አዉቶሚክ ቦምብ የሚተኩሱ መድፎች ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር ታዘምት ያዘች።

ኪም ኢል ሱንግ «አሜሪካኖች ዉሉን ጣሱ፥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አዘመቱ---» እያሉ ዋሽግተኖችን አዉግዘዉ፥ በዋሽግተኖች ላይ ፎክረዉ ዝም አላሉም።የጠላቶቻቸዉን አይነት መሳሪያ ከጃቸዉ የሚዶሉበትን ጊዜ ያሰላስሉ ገቡ-እንጂ።ስታሊንን ማኦንም ቢጠይቁ ለጊዜዉም ቢሆን አልረዷቸዉም።በ196ዎቹ አጋማሽ ብቻዉን ገቡበት።

የኪም ኢል ሱንግ ሐሳብ ገቢራዊ እስኪሆን ብዙ ዓመታት ፈጅቷል።የኑክሌር መርሐ-ግብሩ እንዳዲስ ያቀጠላጠለዉን ነባር ጠብ፥ ፍጥጫ ለማስወገድ ዩናይትድ ስቴትስ እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚመሩት ደቡብ ኮሪያና ጃፓን፥ከሰሜን ኮሪያና ለሰሜን ኮሪያ ከሚያግዙት ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር በተከታታይ ተደራድረዋል።የተለያዩ ዉሎች ተፈራርመዋል።ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብሯን በዓለም አቀፍ መርማሪዎች እስከማስፈተሽ ደርሳ ነበር።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ «ዓለም አይበቃኝ» ባሉበት ዘመን የብዙ ዓመታት የድርድር ዉጤት የሆነዉን ለንቋሳ ዉል ገለባበጡት።የአድሚራል ራድፎርድ ዕቅድ፥ የአይዘናወር ዉሳኔ የጫረዉን መዘዝ ቡሽ ሲቆሰቁሱት ሠላም ለማያዉቀዉ ዓለም ዘጠኛ ባለ ኑክሌር ሐገርን መዘዘ። ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያዉን የኑክሌር ቦምብ ፈተሸች።ሁለት ሺሕ ስድስት።

ዩናይትድ ስቴትስ ከ1950 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለችዉ ማዕቀብ እንደፀና ነዉ።በሁለት ሺሕ ስድስት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሌላ ማዕቀብ ጣለባት።ሁለት ሺሕ ዘጠኝ-ሰሜን ኮሪያ ሌላ የኑክሌር ቦምብ አፈነዳች።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ሌላ ማዕቀብ ጣለ።አሰልቺ ዑደት።አስጊ ሒደት።


ኪም ጆንግ ኡን ወጣት ናቸዉ።ግን በሃያ-ዘጠኝ ዓመታቸዉ ሁሉንም ጠቀለሉት።ከኑክሌየር ቦምብ ዩናይትድ ስቴትስን እስከሚመታ የሩቅ-ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳዬል፣ ከፈጣን ረቂቅ ጄት እስከ ባሕር ሰርጓጅ ጀልባ እስካፍንጫዉ የታጠቀዉን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ጦር ለማዘዝ አባታቸዉ በሁለት ሺሕ አስር የለጠፉላቸዉ የጄኔራልነት ማዕረግ በቂ አልነበረም።

ግንቦትና ሰኔን፥ ሚያዚያ አጋማሽ የተሞከረዉ የኑክሌር ቦምብ አወንጫፊ ሚሳዬል የከሸፈበትን ምክንያት ሲያጣሩ ምናልባትም ዳግም የሚሞከርበትን ብልሐት ሲያሰላሰሉ ቆዩና ሐምሌ ላይ-የማርሻል ማዕረግ ደረቡ።ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት አርጅቶ ሊሰናበት ዕለታት ሲቀሩት አዲሱ መሪ-አሮጌዉን ሚሳዬል ዳግም አስፈተሹ።ተሳካላቸዉ።ዋሽግተን፥ ሶል፥ ቶኪዮዎች ፎከሩ።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አወገዘ።

በመሐሉ ኪም ጆንግ ኡን ሰላሳ ዓመት ደፈኑ።ጥር ስምት።ከልደታቸዉ ሰባት ቀናት በፊት በአዲሱ ዓመት አዲስ ያስተላለፉትን ተስፋ-አዘል መልዕክት አሜሪካ መራሹ ዓለም ሊቀበለዉ ቀርቶ ለማጥናት ማስተንተን አንኳን አልፈለገም።እንዲያዉም በተቃራኒዉ አሮጌዉን ፉከራ፥ ዉግዘት አጡዞ በሰሜን ኮሪያ ተቋማት ላይ ሌላ ማዕቀብ አስጣለ።ጥር አጋማሽ።

የካቲት አስራ-ስድስት የኪም ጆንግ ኡን አባት፥ የኪም ጆንግ ኢል የልደት ቀን ነዉ።የ«አንፀባራቂዉ ኮኮብ ዕለት»።ኪም ጆንግ ኡን ለራሳቸዉ ልደት አላደረጉትም።በአባታቸዉ ልደት ዋዜማ ቢያደርጉት ምናለ? የካቲት አስራ-ሁለት። አደረጉት።ሰወስተኛዉን የኑክሌር ቦምብ አስሞከሩ።

«በታላቁ የአንፀባሪቂ ኮኮብ ዕለት ዋዜማ ይሕን የተሳካ የኑክሌር ቦምብ ሙከራ ዜና በመስማቴ እንደ ወታደር በጣም ኮርቻለሁ።ሙከራዉ የሳተላይት በማምጠቃችን ማዕቀብ ላስጣሉቡን ለዩናይትድ ስቴትስና ለተከታዮችዋን አስደንጋጭ መልዕክት ነዉ።» አሉ የጦር መኮንኑ።

ዘመኑ-ተቀይሯል።መሪዎቹም ተለዋዉጠዋል።ኪም ጆንግ ኡን ወጣት አዲስ መሪ ናቸዉ።ደቡብ ኮሪያም የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዝዳት መርጣለች።አዲሲቱ መሪ ፓርክ ጉዩን-ሔይ ዴን በመጪሡ ሳምንት ሥልጣናቸዉን ይረከባሉ።አዲስ ናቸዉ።ሥልት-ዑደቱ ግን ምስራቅ-ሆነ ምዕራብ፥ ሰሜን ሆነ ደቡብ ያዉ ነዉ።አሮጌ።

«ይሕ የኑክሌር ሙከራ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ቁጥር 1718: 1874 እና (በቅርቡ) ሚሳዬል ከተሞከረ በሕዋላ የተወሰነዉን 2087ን በግልፅ የጣሰ ነዉ።»የደቡብ ኮሪያ የፀጥታ ጉዳይ የበላይ።ፕሬዝዳት ኦባማም ሥልጣናቸዉ በአራት ዓመት አሮጌ-ይሁን እንጂ እንዳዲስ የያዙት ዘንድሮ ጥር ነዉ።ሐምሳ ዓመት ለዘለቀዉ ዉዝግብ፥ ፍጥጫ፥ ግን አዲስ ሥልት አልቀየሱም።ወይም መቀየሳቸዉን አላስታወቁም።ዛቻዉን ግን እንደ ብዙ ቀዳሚዎቻቸዉ አንቆረቆሩት።

«እጅግ አደገኛዉ ጦር መሳሪያ እንዳይሰራጭ የሚደረገዉን ዓለም አቀፉ ጥረት መምራቷን ትቀጥላለች።የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ፀጥታና ብልፅግናቸዉ የሚከበረዉ ዓለም አቀፍ ግዴታቸዉን ሲያከብሩ ብቻ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ኦባማ እንደመራዋለን ያሉት ዓለም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለማስጣል ጥረቱን ቀጥሏል።አዲሱ ማዕቀብ የኑክሌር ቦምብ፥የሚሳዬል ሙከራዉን ለማስቆም መተከሩ ግን ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ዑደቱ ግን አልተቋረጠም።እስከ መቼ አይታወቅም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

North Korean leader Kim Jong-Un presides over an enlarged meeting of the Central Military Commission of the Workers' Party in this undated recent picture released by North Korea's official KCNA news agency in Pyongyang February 3, 2013. KCNA said that members of the commission, members of the Korean People's Army Supreme Command and commanding officers of the large combined units including the navy, air force and strategic rocket force, attended the meeting. KCNA did not state expressly the date when the picture was taken. REUTERS/KCNA (NORTH KOREA - Tags: POLITICS MILITARY) ATTENTION EDITORS - THIS PICTURE WAS PROVIDED BY A THIRD PARTY. REUTERS IS UNABLE TO INDEPENDENTLY VERIFY THE AUTHENTICITY, CONTENT, LOCATION OR DATE OF THIS IMAGE. THIS PICTURE IS DISTRIBUTED EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. NO THIRD PARTY SALES. NOT FOR USE BY REUTERS THIRD PARTY DISTRIBUTORS. QUALITY FROM SOURCE
ኪም ጆንግ ኡንምስል Reuters
North Korean soldiers march in front of flower waving civilians during a mass military parade in Pyongyang's Kim Il Sung Square to celebrate 100 years since the birth of the late North Korean founder Kim Il Sung on Sunday, April 15, 2012. North Korean leader Kim Jong Un delivered his first public televised speech Sunday, just two days after a failed rocket launch, portraying himself as a strong military chief unafraid of foreign powers during festivities meant to glorify his grandfather. (Foto:David Guttenfelder/AP/dapd)
የኪም ኢል ሱንግ 100ኛ ልደትምስል AP
North Korean soldiers march in front of flower waving civilians during a mass military parade in Pyongyang's Kim Il Sung Square to celebrate 100 years since the birth of the late North Korean founder Kim Il Sung on Sunday, April 15, 2012. North Korean leader Kim Jong Un delivered his first public televised speech Sunday, just two days after a failed rocket launch, portraying himself as a strong military chief unafraid of foreign powers during festivities meant to glorify his grandfather. (Foto:David Guttenfelder/AP/dapd)
የኪም ኢል ሱንግ 100ኛ ልደትምስል AP
A North Korean missile Taepodong class is displayed during a military parade to mark 100 years since the birth of the country's founder Kim Il-Sung in Pyongyang on April 15, 2012. The commemorations came just two days after a satellite launch timed to mark the centenary fizzled out embarrassingly when the rocket apparently exploded within minutes of blastoff and plunged into the sea. AFP PHOTO / PEDRO UGARTE (Photo credit should read PEDRO UGARTE/AFP/Getty Images)
ሰሜን ኮሪያ-ወታደራዊ ትርዒትምስል PEDRO UGARTE/AFP/Getty Images
A North Korean missile Taepodong class is displayed during a military parade to mark 100 years since the birth of the country's founder Kim Il-Sung in Pyongyang on April 15, 2012. The commemorations came just two days after a satellite launch timed to mark the centenary fizzled out embarrassingly when the rocket apparently exploded within minutes of blastoff and plunged into the sea. AFP PHOTO / PEDRO UGARTE (Photo credit should read PEDRO UGARTE/AFP/Getty Images)
ሰሜን ኮሪያ-ወታደራዊ ትርዒትምስል PEDRO UGARTE/AFP/Getty Images

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ













ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ