1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት እጦት በኤርትራ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 6 2008

በየካቲት ወር በወጣ የጀርመን የስደተኞች መዘርዝር መሠረት ከኤርትራ የመጡ ስደተኞች ብዛት 6 ወይም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሶሪያውያን በብዛት አንደኛ ሲሆኑ ከኢራቅና ከአፍጋኒስታን የመጡት ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው። ኤርትራ ዉስጥ አሁን ደም አፋሳሽ ጦርነት የለም፤ ወጣት ወንዶች ግን ከሀገሪቱ ይሸሻሉ።

https://p.dw.com/p/1IUue
Eritrea Hauptstadt Asmara Panorama
ምስል Reuters/T. Mukoya

[No title]


በርካታ ኤርትራውያን ከሃገራቸው ለምን ይሰደዳሉ? የተመድ ባለፈው ዓመት ስለ ኤርትራ ባወጣው ዘገባ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም አመልክቷል። ሀገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 1993 በይፋ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም። ፕሬሱም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው። በመቶ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ክስ ሳይመሠረትባቸው ታስረዋል ። ከሁሉም ከባዱ ወጣት ወንዶች ላልተወሰነ ጊዜ በሚካሄድ በብሄራዊ ውትድርና ምክንያት ነፃነታቸውን መነፈጋቸው ነው። ወደ ኤርትራ የተጓዘው ጋዜጠኛ ኦሊቨር ራም ዘገባውን ኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ከሚገኝ አካባቢ ይጀምራል። ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
ቶኮምቢያ ከኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ቶኮምብያ ከኢትዮጵያ ድንበር ብዙም አይርቅም። በአካባቢው ጥቂት ከጭቃ የተሠሩ ጎጆዎች አሉ። መሬቱ ደረቅ አካባቢው በረሃ መሰል ነው። እንደ ተቀረው ኤርትራ ኑሮ እዚህም ኋላ ቀር ነው።
«እዚህ ፍጹም ሰላም አለን። ድንበሩም ፀጥታ የሰፈነበት ነው። በዚያ ምንም የሚደረሰ ነገር የለም። እኛም ከኢትዮጵያ ጋር ፀብ አንፈልግም።»
ይህን ያሉት ተስፋ አለም አንዶም የቶኮምብያ ከንቲባ ናቸው። ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ፍትህ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ PFDJ የተባለው ብቸኛው የኤርትራ ፓርቲ አባል ናቸው። ፓርቲው ግን ዴሞክራሲያዊም ሆነ ፍትሃዊ አይደለም። በሀገሪቱ ምርጫ ተካሂዶ ስለማያውቅ PFDJ ከጎርጎሮሳዊው 1993 አንስቶ ኤርትራን ይመራል። የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እስካሁን በሥራ አልተተረጎመም፤ ነፃ ፕሬስም የለም። ኤርትራ በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት ስሟ በጥሩ አይነሳም። አገልግሎቱ ለ18 ወራት ቢሆንም ላልተወሰነ ጊዜ፤ ለዓመታት ይራዘማል። ብዙ ወጣቶች ከኤርትራ የመሰደዳቸው ምክንያት ብሔራዊ ውትድርና መሆኑ ይነገራል። ከንቲባ ተስፋ አለም አንዶም ግን ለዚህ ቀጥተኛ መልስ አልሰጡም።
«ሰዎች መሄድ መምጣታቸው የተለመደ ነገር ነው። በቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሄደው እዚያም በስደተኞች መጠለያ ኑሮ ቀላል ሆኖ አያገኙትም። ስደት አሁን ለወጣቱ እንደ ጀብዱና ፋሽን የተያዘ ነገር ሆኗል።»
አሁን ተያዘ በሚሉት በዚህ ፈሊጥ በየወሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ይሰደዳሉ። የሚሰደዱት በአደገኛ ጉዞ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ከተማዋ ባድመ ምክንያት እልባት ያላገኘ ውዝግብ ውስጥ ነው ያሉት። ነፃ ለመውጣት 30 ዓመት የተካሄደው ጦርነት፤ ከነፃነት በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የተካሄደው ውጊያ እና የባድመ ውዝግብ ኤርትራን አደህይቷል። ኤኮኖሚዋንም አድቅቋል።

በዋና ከተማዋ አስመራ የሚኖሩት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረው አብርሃም እና ጆን የተባሉት ወጣቶች የመንግሥትን እርምጃ ይተቻሉ። እንደነርሱ መንግሥትን የሚኮንን ፍርድ ሳይቀርብ ቅጣቱም ሳይታወቅ ወህኒ ይወረወራል።
«ይህች ሀገር ወደ ኋላ እየሄደች ነው። አርበኞቻችን ለዚህች ሀገር ነፃነት በሚዋደቁበት ወቅት በልማት የተሻለ ደረጃ ላይ ነበረች። በጤና፣ በትምህርት፣ አስፈላጊ በሆኑ ምርቶችም ራሷን የቻለች ነበረች። አሁን ከ25 ዓመታት በኋላ ግን ሀገሪቱ ይህን ማድረግ አልቻለችም።»
ይላል አብርሃም። አብርሃምም ጆንም የከፍተኛ ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል። ግን እነርሱ እንደሚሉት በግሉ ዘርፍ ሥራ የማግኘት እድል የጠበበ ነው። በመንግሥት ሥራ ደግሞ ጥሩ ደሞዝ አይገኝም። ጆን የውጭ ገንዘብ ይመነዝራል። ይህ ክልክል ነው። ቢያዝ ወህኒ ይወርዳል። በሥራውም ደስተኛ አይደለም።
«በጥቁር ገበያ ሥራ መሰማራቴ አያኮራኝም። ሕጋዊ እና እውቅና የተሰጠው ሥራ ብሰራ ነዉ የምመርጠው። ሆኖም መኖር አለብኝ። ሕይወቴ እንዲቀጥል ማድረግ አለብኝ። »
ኤርትራ ዉስጥ ኑሮ እጅግ ተወዷል። አንድ ሊትር ዘይት 6 ዩሮ አንድ ሊትር ጋዝ 3 ዩሮ ያወጣል። በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት የሚሠማሩት በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከ50 እስከ 100 ዩሮ የሚሆን ገንዘብ ነው የሚሰጣቸው። የኤኮኖሚ ሁኔታ ያስከተለው ጭንቀት፣ በመንግሥትና እታሠር ይሆን በሚል ስጋት ሰዉ የነገሰበት ፍራቻ በየሄዱበት ይታያል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ የማነ ገብረ አብ በተለይ የኤርትራን ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትክክል አልተረዳም ይላሉ።
«ኤርትራ ምን እንደሆነች የት እንዳለች የማያውቁ ሰዎች መጀመሪያ የሚጠይቁህ ስለ ብሔራዊ ውትድርና ነዉ። እናም የዚህች ትንሽ ሀገር ጉዳይ እንዴት ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሊሆን ቻለ? ይህ የሚያሳየው የመገናኝ ብዙሃኑን ጨምሮ የተቋማትን ኃይል ነው። »
እንደ አቶ የማነ ኤርትራ አሁን ልትገለል የበቃችው በአንድ ምክንያት ነው።
«ጥገኛ መሆን አንፈልግም። እስከ ወዲያኛው ጥገና መሆን አንፈልግም፤ ይህ ደግሞ እርዳታ ካለመቀበል የተለየ ነዉ። የመተባበር ችግር የለብንም። ከኛ ጋር መተባበር የሚፈልጉ ካሉ በደስታ እንቀበላቸዋለን፤ ችግሩ ባለፉት 18 ዓመታት ኤርትራ በፍፁም አጋሮችና ተባባሪዎች ወዳጆች እንዳታፈራ የተቻለው ሁሉ ጥረት ተደርጓል። ሌላዉ ቀርቶ ዩናይትድ ስቴትስ ለማዕድን ዘርፋችን ብድር እንዳናገኝ ለማገድ ሞክራለች።»
ኦሊቨር ራም እንደዘገበው የኤርትራ ሕዝብ ተምሯል። ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ገንዘብ አያስከፍሉም። ሆኖም በሀገሪቱ እምብዛም የኤኮኖሚ ፕሮጀክቶች አይታዩም ።

Flüchtlinge Eritrea
ምስል AP
Bildergalerie Flüchtlingscamp Tigray in Äthiopien SCHLECHTE QUALITÄT
ምስል Milena Belloni

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ