1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰው ልጅ ዕዳ በሲና ምድረበዳ፣

ሰኞ፣ ኅዳር 18 2004

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዛ ያሉ ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያንና ሱዳናውያን፤ በግብፅ በኩል የሲናን ምድረበዳ አቋርጠው እሥራኤል ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ፣ በግብፅ ድንበር ጠባቂ ታጣቂዎች እየተተኮሰባቸው፤ ሴቶችና ህጻናት ጭምር መገደላቸው አይዘነጋም።

https://p.dw.com/p/Rz2s
ምስል DW

ሰዎችን ካገር-አገር ከሚያዘዋውሩ ፤ የሲና ዐረብ ዘላኖች እጅ የወደቁት ደግሞ እስካሁን ድረስ የሚፈጸምባቸው ግፍ የሚዘገንን መሆኑን የዜና አገልግሎት ድርጅቶች ያስረዳሉ። የእሥራኤል መንግሥት ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ግዛቱ የሚገቡ ሰዎችን ተቀብሎ ተገቢውን ክብካቤ የማድረግ ፍላጎት የለውም። እንደምንም በለስ ቀንቷቸው የሚገቡትን ከሚያግዙት መካከል፣ የአንዱን ድርጅት ተጠሪ በማነጋገር ተክሌ

የኋላ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

እሥራኤል ውስጥ በቴል አቪቭ ከተማ ፣ የሚገኘው የመንግሥት ያልሆነው ፤ ለሰብአዊ መብት እገዛ እንደሚያደርግ የሚነገርለት ፤ የሀኪሞች ማኅበር፤ (Physicians for Human Rights) ፤ 800 ያህል ተገን ጠያቂዎችን በማነጋገር ያቀረበው ዘገባ ፤ በሲና በረሃ እስካሁን መላ ያልተፈለገለትን የስደተኞች ሰቆቃ የሚያስረዳ ነው። በተጠቀሰው የመንግሥት ባልሆነው ድርጅት ውስጥ ፣ የስደተኞችና ፈላስያን ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ወ/ት ሾኻር ሾኻም ፣ እንዲህ ይላሉ።---

«ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በፊት አንስቶ ከመንግሥት የህክምና እርዳታ ለማያገኙ ተገን ጠያቂዎች የህክምና እርዳታ በሚያደርገው ክፍት ክሊኒካችን ፤ በሲና ምድረበዳ ምን እንደሚደረግ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በርከት ያሉ ታሪኮችን ስንሰማ ቆይተናል።

800 ለሚሆኑ ተገን ጠያቂዎች መጠይቅ አዘጋጀን። አብዛኞቹ፤ ከኤርትራና ከሱዳን ናቸው። የነገሩን ታሪኮች ዘግናኝ ናቸው።»

አንዳንድ የዜና አውታሮች ፤ ዘመናዊ ባርነት በሚሉት ጭካኔ በተመላበት ዘግናኝ እርምጃ፤ ኩላሊትና ጉበት እየተነጠቁ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እስከማለፍ መድረሱን አስታውቀዋል። ተሳክቶላቸው እሥራኤል የገቡት ፤ ምንድን ነው የሚናገሩት?

«ሰዎችን ከቦታ ቦታ በድብቅ ለማሸጋገር የተደራጁና የራሳቸውን መረብ የዘረጉ ክፍሎች፤ መኖራቸውንና እነዚህም ሰዎች ከአያንዳንዱ ሰው እስከ 28,000 ዶላር እንደሚጠይቁ ሰምተናል። ገንዘቡን ለማግኘት ደግሞ ስደተኞቹን ሲና ውስጥ ቁም -ስቅል በማሳያ ጣቢያዎች፤ እንደሚያቆዩአቸው፣ እንደሚያሰቃዩአቸው፣ ሴቶቹንም እንደሚደፍሯቸው ፤ በኤሌክትሪክ አካል የሚያነዝር ሰቅጣጭ እርምጃ እንደሚወስዱ፣ ምግብ እንደሚከለክሏቸው፣ ውሃ እንደሚነፍጓቸው፤ እርስ በርስ እያቆራኑ በሰንሰለት እንደሚያሥሯቸው፣ አሸዋ ላይ እንደሚቀብሯቸው አስረድተውናል።

ይህን ሁሉ የሚያደርጉት፣ ከሚያሰቃዩአቸው ሰዎች ቤተሰቦች፤ ገንዘብ ለማግኘት ሲሆን፣ በሥቃይ ሲቃ ላይ ያሉት ስደተኞችም ቤተሰቦቻቸውን በስልክ እንዲያነጋግሩ ያደርጋሉ--ተጨማሪ ገንዘብ እንዲላክ ለማስገደድ ማለት ነው። በተደጋጋሚ ቁም-ሥቅል እያዩ ፣ አያሌ ወራት በእንዲህ ሁኔታ ሊቆዩ ይችላሉ። አንዳንዴም በጥይት ይገደላሉ። ብዙዎች በእንዲህ ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል። »

የ «ፊዚሻንስ ፎር ሁማን ራይትስ፣ የስደተኞችና የፋላስያን ጉዳይ ሥራ አስኪያጅ ሻኸር ሾሃም፣ ህገ ወጥ በሆነ ተግባር፤ ከአገር- አገር ፤ የሰው ንግድ የሚያካሂዱ ሰዎች ሰለባዎች የሆኑትን ስደተኞች፤ መንግሥታቸው፤የህክምን እርዳታ እንዲሰጣቸው ተጽእኖ ሊደረግበት ይገባል ባይ ናቸው። አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዘውትሮ ስለስደተኞቹ ሰቆቃ አመልክቷል፤ HRW ም እንዲሁ! በሲና የህዝብ ማሳቃያ ማዕከላቱን ማን ይዝጋቸው? ፤ በስደተኞች ላይ የሚሠራውን ግፍ ማን ያቁመው? ኀላፊነቱን ማን ነው መወሰድ የሚገባው ይላሉ?-

«ይህ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የግብፅ ኀላፊነት ነው። በሲና በረሃየሚፈጸመውን ግፍ ዓለም በመላያውቀዋል። UNHCR ስለችግሩ ከማሳወቅ አልቦዘነም። የአውሮፓው ኅብረት ውሳኔ እስከማሳለፍ ደርሷል። በዩናይትድ እስቴትስ ው ጉ ሚንስቴር የሰብአዊ መብት ይዞታ ነክ ዘገባ ላይ ተወስቷል። ሁሉም ያውቀዋል። አሁን፤ እርምጃ ነው መውሰድ ያለበት። ቁም ስቅል የሚያዩትን ተገን ጠያቂዎች ፣ ማስለቀቅ፣ ሰውን ካገር-አገር ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የሚያሸጋግሩትን መያዝና ድርጊታቸውን ማስቆም ነው!»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ