1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ውዝግብ መባባስ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2004

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደቡብ ሱዳን ጦር ሂጂሊጅ የተባለውን የሰሜን ሱዳን ግዛት እና በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ንጣፍ የተቆጣጠረበትን ርምጃ ከራስ መከላከል ያለፈ ድርጊት ነው ሲል፡ እንዲሁም፡ የሱዳን መንግሥት ደቡብ ሱዳንን በቦምብ ማጥቃትዋን በጥብቅ አወገዘ።

https://p.dw.com/p/14dj6
The main base camp for Heglig oil field near Bentiu, southern Sudan, is shown May 10, 2001. Since July 1997, a consortium of Chinese, Canadian, Malaysian and Sudanese companies have spent more than $1 billion to bring Sudan's oil online. Critics and humanitarian groups say the money is fueling an 18-year civil war in the south in which an estimated 2 million people have already died, mainly from war-induced famine. (AP Photo/Abdul Raouf)
ምስል AP

ዩኤስ አሜሪካ፣ የአፍሪቃ ህብረትና የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት  የደቡብ ሱዳን ጦር ካላንዳች ቅድመ ግዴታ ለቆ እንዲወጣ አሳስበዋል። ይሁንና፡ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ጦራቸው ከሂጂሊጅ እንዲወጣ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል። በሁለቱ ሀገሮች መካከል አሁን እየተባባሰ የመጣው ውዝግብ፡ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት፡ ዩኤንኤችሲአር እንደገለጸው፡ ብዙዎችን እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ አድርጎዋል።  

የሱዳን ጦር በዩኒቲ ክፍለሀገር አንድ ሥልታዊ የደቡብ ሱዳንን ድልድይ በቦምብ ካጠቁ በኋላ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች አንዱ ሌላውን ጦርነት ለመጀመር አቅዶዋል በሚል እርስበርስ መወቃቀስ ጀምረዋል። በዚሁ ጊዜ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር ባለፈው ማክሰኞ ገና በሚገባ ያልተከለለውን ድንበሩን ተሻግሮ በሱዳን ከያዘው ከሀገሪቱ ነዳጅ ዘይት መካከል ሀምሳ ከመቶው የሚመረትበትን የሂጂሊጅን ግዛት ለቆ የሚወጣበትን ቅድመ ግዴታ አስቀምጣለች። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር ባናባ ማርየል ቤንጀሚን እንዳስረዱት፡ ቅድመ ግዴታው ሱዳን ጦርዋን ከአቢየ የምታስወጣበትን እና በየብሱና በአየር የምታካሂደውን ጥቃት በጠቅላላ የምታቆምበትን ሀሳብ ያጠቃልላል። በደቡብ ሱዳን የቀድሞው የተመድ ተልዕኮ ኃላፊ ፒተር ሹማን ደቡብ ሱዳን ይህን ርምጃ ለመውሰድ ያነሳሳት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዱ፡

« ሁሉ ነገር የራሱ ታሪክ አለው። የሱዳን ጦር ከአንድ ዓመት በላይ በፊት አቢየን የያዘበትን፡ በአቢየ መካሄድ የነበረበት ሕዝበ ውሳኔ ሳይካሄድ የቀረበትን፡ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሂደቶችን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ችላ ያለበት ድርጊት አሁን ውዝግቡ እንዲባባስ ድርሻ አበርክቶዋል። የተደረሱ ስምምነቶች ነበሩ። አንድ ልዩ ተልዕኮም ተዘጋጅቶ ነበር። ይህ ሁሉ አሁን የታየውን ሁኔታ አስከትሎዋል። እንደሚመስለኝ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአዲሲቱን ሀገር የደቡብ ሱዳን የሰላም ፍላጎትን በሚገባ አላጤኑላትም። እኔ ከጥቂት ጊዜ በፊት ጁባ ነበርኩ። በሰሜኑ አካባቢ ወዳለው የድንበር አካባቢም ተጉዤ ነበር። ካርቱምም ሄጄ ነበር። ብዙ ሰዎችን አነጋግሬአለሁ። እና ሰው በተለይ ደቡብ ሱዳን ዜጎች መልስ ላላገኙት አወዛጋቢ ጉዳዮች ባፋጣኝ መልስ እንዲገኝላቸው ያሳዩት ጠንካራ ፍላጎት አስገርሞኛል። የዓለም አቀፉ ድርጅቶች ተወካዮች ያሳዩት ቸልተኝነትና ለውዝግቡ በአፍሪቃ ህብረት የተሰየመው በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው የሸምጋዮች ቡድን መፍትሄ ያስገኛል ብለው የጠበቁበት ድርጊትም አስገርሞኛል። »
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአዲስ አበባው ድርድር ይቀጥል ዘንድ ወሳኝ አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይችል እንደነበር ፒተር ሹማን በመግለጽ ትችት አሰምተዋል።

« ዓለም አቀፉ ማህበረሰብብዙ ማድረግ በተገባው ነበር። ጉዳዩን የአፍሪቃ ህብረት ከፍተኛ የሽምጋዮች ቡድን ብቻ በመተው ፈንታ ራሱም ፡ ጀርመንም ጭምር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸው ነበር። ራሳቸውን የደቡብ ሱዳን ወዳጆች ብለው የሚጠሩት ወገኖች በደቡቡ ላይ ግፊት ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን፡ ከዚችው አዲስ ሀገር ጋ ጠንከር ያለ ውይይትም መጀመርና ፍላጎትዋ በርግጥ ምን መሆኑን ለመረዳት መሞከር ነበረባቸው። »
አሁን ጦርነት አፋፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ተቀናቃኝ ሀገሮች ከኃይል ተግባር እንዲታቀቡ፡ ደቡብ ሱዳንም የያዘችውን ግዛት ለቃ እንድትወጣና ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳስቦዋል። ይሁንና ይህ ገሀድ መሆኑን ፔተር ሹማን አብዝተው ይጠራጠሩታል።

« አይመስለኝም፡ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች፡ ታቦ ምቤኪ የሚመሩት የሸምጋዮች ቡድን ጭምር አቢየን ጉዳይ በተመለከተ ተዓማኒነት አጥተዋል። የሱዳን ጦር ባለፈው ዓመት አቢየን በያዘበት ጊዜ በደቡብ ሱዳን ርዕሰ ከተማ ጁባ ነበርኩ። የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቡድን ደግሞ ካርቱም ነበር፤ ግን የሱዳን ጦር አቢየን በያዘበት ርምጃ አንጻር ቡድኑ ያሰማው ተቃውሞ በጣም የሰጠው ደካማ ነበር። እና በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ተራው ሕዝብም ሳይቀር ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሊያምኑ እንደማይችሉ ነው ያስታወቁት። ምክር ቤቱ ሥራውን በሚገባ የሚያከናውን ከሆነ በሰሜን ሱዳን እና ነፃ መንግሥት የመሆን መብታችንን ሊነፍጉ በሚፈልጉ ላይ ርምጃ መውሰድ አለበት። እና አቢየን መያዝ በቸልታ በታለፈበት ጊዜ እምነታችንን አጥተናል። ከዚያ በኋላ ሌላ የተመ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ተቋቁሞዋል፡ ይሁንና፡ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ተግባሩን ማካሄድ አልቻለም። እና የተገባ ቃል በተደጋጋሚ የተጣሰበት፡ ይህን ወይም ያኛውን ሁኔታ የሚቆጣጠር የሚታዘቡ ኮሚቴዎች፡ ኮሚሽኖች ሲቋቋሙ ብቻ ነው የታየው፤ እና ሕዝቡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ እምነት የለውም። »
የደቡብ ሱዳን ጦር ሰሞኑን በሱዳን የተቆጣጠረው ሂጂሊጅ ከሚገኝበት የደቡብ ኮርዶፋን ክፍለ ሀገር በርካቶች በውዝግቡ ሰበብ መሸሽ መገደዳቸውና ብዙዎችም በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በናይሮቢ ኬንያ የሚገኙት የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት፡ በምህፃሩ ዩኤንኤችሲአር ተጠሪ ወይዘሮ ቪቭየን ታን ገልጸዋል።


« እስካሁን ወደ ደቡብ ሱዳን የዩኒቲ ክፍለ ሀገር የሸሹ አሥራ ስምንት ሺህ ስደተኞችን መዝግበናል። በተለይ ቀውሱ በቀጠለበት ድንበር አካባቢ አቅራቢያ በሚገኘው ኒዳል በተባለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከለላ ያገኙ አሥራ ስድስት ሺህ ስደተኞች ሁኔታ እጅግ አሳስቦናል። ይህ የመጠለያ ጣቢያ ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ በተዋጊ አይሮፕላኖች የቦምብ ጥቃት ተደብድቦዋል። እና ጣቢያው አሁንም እንደገና ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጣልበት ሠግተናል። አሁን የተጎዳ አንድም ስደተኛ የለም። ወደፊት የሚካሄድ ጥቃት ግን ከድንበር ባሻገርም ሊስፋፋ እና የስደተኞቹን ህልውና ሥጋት ላይ ሊጥል ይችላል። በመሆኑም፡ እነዚህን ስደተኞች መረጋጋት ወደሚታይበትና የተሻለ አገልግሎት መስጠት ወደምንችልበት ወደደቡባዊ የደቡብ ሱዳን አካባቢ ለማዛወር እየሞከርን ነው፤ ግን፡ ስደተኞቹ በኑባ ተራሮች አካባቢ ከሚገኘው በድንበሩ አካባቢ ካለው ትውልድ ቦታቸው ብዙ መራቅ ስለማይፈልጉ የመዛወሩን ሂደት አልተቀበሉትም። በድንበሩ አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ እንደልብ መንቀሳቀስ አንችልም። ይህም ለስደተኞች ርዳታ በምናቀርብበት ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎዋል። »
ስደተኞቹ አካባቢያቸው በቦምብ መደብደቡን እና ውጊያውም መቀጠሉን የገለጹት ስደተኞች ወደመጠለያ ጣቢያው ለመድረስ ብዙ ሣምንታት በእግራቸው መጓዛቸውን አስታውቀዋል። ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ የስደተኛው ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል ዩኤንኤችሲአር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ቪቭየን ታን አስረድተዋል።

« በዚሁ አካባቢ ወዳሉት ብዙዎቹ ጣቢያዎች የሚያደርሱት መንገዶች ጥቂት በመሆናቸው የዝናቡ ወራት በቅርቡ ሳይጀምር እና እዚያ መድረሱ አዳጋች ከመሆኑ በፊት ብዙ የምግብ ርዳታ የርዳታ ቁሳቁስ ለማዘጋጀት እየሞከርን ነው። »

               


 አርያም ተክሌ

A member of the rebel movement Sudan Liberation Army (SLA) - Abdul Wahid walks as a water tank is installed, during the delivery of 30,000 litres of water by the African Union - United Nations Mission in Darfur's (UNAMID) peacekeeping troops from South Africa, in Forog, some 45km (28 miles) north of Kutum March 28, 2012. The water is to aid the local population in the construction of a clinic. REUTERS/ Albert Farran/UNAMID (SUDAN - Tags: POLITICS MILITARY SOCIETY) THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS
ምስል Reuters

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ