1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነት

ማክሰኞ፣ የካቲት 16 2002

የኢራን፥የሰሜን ኮሪያን፥ የበርማን ወይም የሌላዉን በፀጥታዉ ምክር ቤት በኩል የሚያልፍ ጉዳይ ካለ ቻይናን አስፈላጊ ያደርጋታል።ቻይናም ምዕራቡን አለም-በጣሙን አሜሪካን ለፖለቲካ-ለንግዷም በግዷ ትፈልጋታለች።የወደፊቱን አናዉቅም። ላሁኑ ግን በርግጥ ይፈላለጋሉ

https://p.dw.com/p/M8FR
ታይዋን-ምስል AP GraphicsBank


22 02 10

የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነት፥ የጦር መሳሪያ ሽያጭ፥ ታይዋንና ቲቤት።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።በጣሙን፥-የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር፥በመጠኑ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሙከራ-እቅድ እንዴትነት አለምን ሲያነጋግር ሰሞኑን፥ ዩናይትድ ስቴትስ ታይዋንን ለማስታጠቅ መወሰኗ፥ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የቲቤቱን መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማን ማነጋገራቸዉ፥ ጉግልና የቻይና መንገሥት ከገጠሙት አተካራ ጋር ተዳምሮ የሁለቱን ሐያል-ሐብታም ሐገራት ግንኙነት አጠያያቂ አድርጎታል።የአጠያያቂዉን ጉዳይ ምክንያት የእስካሁን ግንኙነታቸዉ ሒደት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

ከሳምንት በፊት በይፋ እና በተደጋጋሚ እንደተነገረዉ የዩናትድ ስቴትሷን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተንን ባለቤታቸዉን ሆስፒታን አስትቶ ከኒዮርክ ዶሐ፣ ከሪያድ፣ ጂዳ ያጓዛዉ፣ የመንግስታቸዉን ትኩረት ብዙ የሰባ፥ ወዳጆቹን ያሰጋዉ ትልቅ ነገር አንድ ነዉ።የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር።ክሊተን ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ-ሳዑዲ አረቢያ ላይ እንዳሉትም የኢራን መንግሥት የኑክሌር ቦምብ ይመረትበት ይሆናል ተብሎ የሚጠረጠረዉን ዩራንየም ይበልጥ ለማብላላት መወሰኑ በአካባቢዉ አለመረጋጋትን ያስከትላል።
              
«ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የተብላላ ዩራንየም እንደምታመርት ለIAEA አስታዉቃለች።ይሕ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ የጣሰ ጠብ ጫሪነት ነዉ።ይሕ አካባቢዉን ከከፋ አለመረጋጋት እንደሚከተዉ እና ኢራንን ይበልጥ እንደሚያስገልላት የኢራን መንግሥት ያዉቀዋል።»
መልዕክቱ በርግጥ ግልፅ ነዉ።ብዙዎቹ የፖለቲካ  ተንታኞች እንደሚስማሙበት የኢራን እርምጃ በርግጥ እንደተጠረጠረዉ የኑክሌር ቦምብ ከመሥራት ደረጃ ከደረሰ ወትሮም ሰላምና መረጋጋት የማያዉቀዉን ምድር ከባሰ ትርምስ ይዶል ይሆናል።ይሁንና ወይዘሮ ክሊንተን የባሕረ-ሠላጤዉን አካባቢ ሐገራት በኢራን አንፃር ለማስተባበር የተጓዙት መስተዳድራቸዉ ለታይዋን የ6.4 ቢሊዮን ዶላር ዘመናይ ጦር መሳሪያ ለመሸጥ በወሰነ ማግስት ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ ታይዋንን እንደ ሃያ-ሰወስተኛ ግዛትዋ ለምታያት ቻይና በዉስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እንደመግባት የሚቆጠር ነዉ።የመሳሪያዉ ሽያጭ እንደተሰማ የቻይና መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያሰራጨዉ መግጫ ደግሞ የዋሽግተን ባለሥልጣናት የማይፈልጉት ገና ሲሞክረዉ የሚወነጅሉበትን እራሳቸዉ ማደራጋቸዉን መስካሪ ነዉ።
               
«የጦር መሳሪያዉ ሽያጭ በቻይና የዉስጥ ጉዳይ በግልፅ ጣልቃ መግባትን የሚያረጋግጥ ነዉ።እና የቻይናን ብሔራዊ ፀጥታ ክፉኛ የሚጎዳ ነዉ።ቻይና የዩናይትድ ስቴትስ ዉሳኔን አጥብቃ ትቃወማለች።(ዉሳኔዉ) ሁለቱም ወገኖች እንዲሆን የማይፈልጉትን መሰነጣጠቅ ያስከትላል።»

Tibet Dalai Lama während einer Pressekonferenz in Dharamsala, Indien
ዳላይ ላማምስል AP

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊተን እንዳሉት ኢራን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ ጥሳለች።አለም አቀፉ ድርጅት በኢራን ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጥልም ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ እየጣሩ፥ ሌሎች የምክር ቤቱን  አባላትም እያስተባበሩ ነዉ።ምክር ቤቱ ኢራንን እንዲቀጣ ደግሞ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላት የቻይና ድጋፍ ወሳኝ ነዉ።

ክሊተን ያሉትን ከማለታቸዉ ከአንድ ሳምንት በፊት ግን ቻይናዊዉ አቻቸዉ ያንግ ጂቺ እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ ለታይዋን ዘመናይ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መወሰኗ የነሐሴ መግለጫ ተብሎ የሚጠራዉን ዉል የጣሰ ነዉ።
               
«ዩናይትድ ስቴትስ ሥለ ጦር መሳሪያ ሽያጭ ያላትን ባሕሪ ትለዉጣለች፥የነሐሴ አስራ-ሰባቱን መግለጫ ታከብራለች፥ እናም ከኛ ጋር በ(ታይዋን) ሰርጡ ሰላማዊ ጉዳይ ላይ በጎ እመርታ እያሳየች ላለችዉ ለታይዋን የጦር መሳሪያ መሸጥዋን ታቆማለች የሚል ተስፋ አለኝ።»

ቻይና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት አቋርጣለች።ለታይዋን የሚሸጠዉን የጦር መሳሪያ በሚያመርቱ የአሜሪካ ኩባንዮች ላይ ማዕቀብ ለመጣልም አስጠንቅቃለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ለታይዋን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ የወሰነችዉ፥ የቻይና አፀፋ ዛቻ-ማስጠንቀቂያ የጋመዉም፥ ቻይና ጉግል የተባለዉ የአሜሪካ ግዙፍ የኢንተርኔት መረጃ አቅራቢ ድርጅት የሚያሰራጫቸዉን መረጃዎች በከፊል ማገዷ የሁለቱን ሐገራት የንግድ ግንኙነት ማዛባቱ፥ይሕ ቢቀር ማወሳሰቡ አነጋግሮ ሳያበቃ ነዉ።

እርግጥ ቻይና የዛተች-ያስጠነቀቀችዉን ያክል አታደርግም።አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ቤጂንጎች ዛቻ ማስጠንቀቂያዉ ያጋጋሙት የብሔረተኛ ሕዝባቸዉን ስሜት መጋራታቸዉን ለማንፀባረቅም ሊሆን ይችላል።አለምን በኢራን አንፃር ለማስተባበር-የሚጥሩትን፥አሜሪካ መራሹ አለም አቀፉ ጦር አፍቃኒስታን የከፈተዉን የአዲስ ጥቃት ዉጤት በንቃት የሚከታተሉትን የዋሽግተን መሪዎችን ትኩረት ለማናጠብ ግን በቂ ነበር።

የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፊሊፕ ክሮዉሌይ።
               
«ይሕንን እርምጃ በማወጃቸዉ እናዝናለን።ያሉትን ለመፈፀም ሥላላቸዉ እቅድ የሚያነጋግሩን ከሆነ ከነሱ ጋር እንወያይበታል።»

የንግድ፧ የጦር መሳሪያ ሽያጩ አልበቃ ያለ ይመስል-ፕሬዝዳት ኦባማ የቲቤቱን መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማን አነጋግረዋቸዉ አረፉት።ከፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ ቀዳማዊ ጀምሮ ዋይት ሐዉስን የተፈራራቁበት የአሜሪካ መሪዎች ቤጂንግ የቲቤትን ግዛት ለማስገንጠል የሚታገሉ የምትላቸዉ ዳላይ ላማን ያለነጋገረ የአሜሪካ መሪ አልነበረም።ቻይናም ዉይይት ንግግሩን ያልተቃወመችበት ወቅት የለም።ያሁኑ ግን ተደራረበ።
                
ማኦ ዜዱንግ፣ ዴንግ ዚያኦፒንግም ለቅርብ ዘመኒቱ ቻይና የታላላቆች ታላላቅ ናቸዉ።የአንድ ትዉልድ ዉጤት፣ግን ታላቅና ታናሾች።አንድ ርዕዮት-ተጋሪ ግን ያፈፃፀም ተፃራሪ።በሁለቱ የትልቆች ትልቅ-አንድነት-ልዩነት የሚወከሉት ኮሚንስቶች በ1949 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የቤጅንግን ቤተ-መንግሥት ሲቆጣጠሩ ዩናይትድ ስቴትስ የቤጂንግ ኤምባሲዋን ነቅላ ዘመን የከዳቸዉን፣ ሕዝብም የጠላቸዉን ቺያንጋይ ካይ ሼክን ተከትላ ታይፔ-ታይዋን ገባች።

የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነትም የኮሚኒስት-ኢፔሪያሊስቶች የጠላትነት መልክ-ቅርፅ ያዘ።በቀጥታ እንደተፈራሩ፣ በዲፕሎማሲዉ እየተተሻኮቱ ከኮሪያ ልሳነ ምድር፣ እስከ ቬትናም በተዘዋዋሪ ጡንቻ ይፈታተሹ ገቡ።ፕሬዝዳንት ሊዮንደን ጆንሰን በ1964 የወሰኑትን ወዲያዉ ባያጥፉት ኖሮ ግን ሁለቱ ሐገሮች በተዘዋዋሪዉ ዉጊያ ያፈሰሱ፣ ያስፈሰሱት ደም ያናረ-ያከረረዉ ጥላቻ በአስራ-አምስተኛ አመቱ ለመገመት ከሚከብድ መዘዝ በዶላቸዉ ነበር።

ኮሚንስት ቻይና የኑክሌር ቦምብ ለማምረት መቃረቧን ያወቁት ጆንሰን የቻይንና የኑክሌር ተቋም በአዉሮፕላን ለማስመታት ወስኑ።ግን መዘዙን ፈሩ እና ዉሳኔያቸዉን ወዲያዉ ሻሩት። ሕዝባዊት ቻይናም የማትደፈር ሐያል ሆነች።ኑክሌር ታጠቀች።

የቻይና ኑክሌር መታጠቅ፥ በቬትናሙ ጦርነት ቻይና የምትደግፋቸዉ ኮሚንስቶች ማሸነፋቸዉ የዋሽንግተን ፖለቲከኞች ሥለ ቻይና የሚከተሉትን መርሕ-ቆም ብለዉ እንዲያስቡ ሲያገድዳቸዉ፥በ1969 ኮሚንስት ቻይና ከኮሚንስት ሶቬየት ሕብረት ጋር በድንበር ግዛት ሰበብ መጋጨቷ የቤጂንግ መሪዎች ምዕራቡን እንደ አማራጭ ወዳጅ እንዲያዩት አስገደዳቸዉ።

US-Präsident Barack Obama mit chinesischem Präsident Hu Jintao
ኦባማና ሁ (ይፈላለጋሉ)ምስል AP

ከሁሉም በላይ ማኦ ባንድ ወቅት ዘብጥያ ወርዉረዋቸዉ የነበሩት ዴንግ ዚያኦፒንግ ሥለ ኮሚንስታዊዉ ርዕዮት በጣም ሥለምጣኔ ሐብት መርሁ የነበራቸዉን አመለካከት ትክክለኝነት አረጋገጣላቸዉ።

የሁለቱ ሐገራት የጠላትነት ክረት በሚስጥር ዉይይት ረግቦ፧ በኒክሰን ጉብኝት ለስልሶ በሰላሳኛ አመቱ በሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኘት ተለወጠ።1979 ።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ ሕዝባዊት ቻይና እንደ ሐገር እዉቅና ስትሰጥ ከቻይና ላፈነገጠችዉ ታይዋን ሙሉ ወታደራዊ፥ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ለማድረግም በሕግ ደንግጋ ነበር።የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር ለታይዋን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ የወሰነዉም የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ፊሊፕ ክሮዉሌይ እንደሚሉት በያኔዉ ሕግ መሰረት ነዉ።
                
«ይሕ (እርምጃ) ታይዋን ራስዋን ለመከላከል የሚያስፈልጋትን የጦር መሳሪያ እንድትታጠቅና  ለማስታጠቅ የተደነገገዉን ሕግ ለማክበር ያለበትን ሐላፊነትና ቁርጠኝነት የሚያመለክት እና ከቻይና አንድ ሐገርነት መርሕ ጋር የሚያጣጣም ነዉ።»

የዛሬዋ ሕዝባዊት ቻይና ግን የ1979ኟ አይደለችም።በ2009  ዩናይትድ ስቴትስ በአጠቃላይ የሐገር ዉስጥ ምርት-GDP በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ከአለም ሐገራት አንደኛ ናት።ቻይና ሁለተኛ።በ2008ም እንዲሕ ነበር።ታይዋን ከምትሸጠዉ ሸቀጥ አርባ-አምስት ከመቶዉን የምትገዛዉ ቻይና ናት።ለዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ገንዘብ ያበደረችዉ ሐገር-ቻይና ናት።ከጦር ሐይሉ-ጉልበቷ፥ ከምጣኔ ሐብት ጡንቻዋ፥ ከሕዝብ ብዛቷ ሌላ፥ ድምንፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኗ-የኢራን፥የሰሜን ኮሪያን፥ የበርማን ወይም የሌላዉን በፀጥታዉ ምክር ቤት በኩል የሚያልፍ ጉዳይ ካለ ቻይናን አስፈላጊ ያደርጋታል።ቻይናም ምዕራቡን አለም-በጣሙን አሜሪካን ለፖለቲካ-ለንግዷም በግዷ ትፈልጋታለች።የወደፊቱን አናዉቅም። ላሁኑ ግን በርግጥ ይፈላለጋሉ።ይወዛገቡ ይሆናል።ግን አምርረዉ አይጨካከኑም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማኝ።

dw,Agenturen

ነጋሽ መሐመድ ሂሩት መለሰ