1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳዑዲ ምህረት አዋጅና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውይይት

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ህገ-ወጥ ያላቸውን ዜጎች ግዛቱን በሰላም ለቀው እንዲወጡ የሰጠው የ 90 ቀናት የምህረት ጊዜ ይጀምራል፡፡ ህገ-ወጥ በተባለ መልኩ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አብዛኞቹ ግን የምህረት ጊዜውን ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ሙሉ ፍላጎት እያሳዩ አይደለም ፡፡

https://p.dw.com/p/2a9t4
Saudi Arabien | Diskussionsrunde in der Äthiopischen Botschaft
ምስል DW/S. Shibiru

Ber. Riad(Ethiopian Embassy discussion on Saudi's amnesty proclamation) - MP3-Stereo

በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሴቶች ተወካዮችን ስደተኛው ወደ ሀገሩ በሰላም እንዲመለስ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ የማሳመን ተግባር እንዲያከናውኑ ጠይቋል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከ 3 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በህገወጥ መልኩ በግዛቱ እንደሚኖሩ ይገልጻል ፡፡ እዚህን ህጋዊ ያልሆኑ ሰዎች የራሳቸውን የመጓጓዣ ወጪ ችለው በ 90 ቀናት ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አውጇል፡፡ የተረጋገጠ አኀዝ ባይኖርም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በዚሁ የህገወጥ ባህር መዝገብ ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል፡፡

በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ኤምባሲው በጠራው ስብሰባ ላይ አምባሳደር አሚን አብዱል ቃድር እንደተናገሩት ጉዳዩን አስመልክተው ከሳዑዲ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ በዚህም ኤምባሲው ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ህገወጥ የተባሉ ዜጎቹን በማሳመን ለጉዞ የማዘጋጀት ሂደቱን ዛሬ ነገ ሳይል እንዲጀምር አጽንኦት መሰጠቱን ነው ያብራሩት፡፡

የኤምባሲው የዳያስፖራ እና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሰል አልይ በበኩላቸው የሳዑዲ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት የዘጠና ቀኑን የምህረት ጊዜ ያለመጠቀም ጦሱ ለህጋዊውም ነዋሪ የሚተርፍ ነው፡፡ ህገወጥ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንዲያሳምኑ እና እንዲያግባቡ በኤምባሲው በኩል ተልዕኮ የተሰጣቸው የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶችም ሆኑ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተወካዮች ህገወጥ ከተባሉት የየ አካባቢያቸው ሰዎች ያገኙት መልስ ወደ ሀገር ለመግባት ብዙም ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፡፡

አሰተያየት የሰጡ የተለያዩ ማህበረሰብ ተወካዮች የኢትዮጵያ መንግስት ከስደት ተመላሾችን በተለያዩ መንገዶች የሚያቋቁምበትንና የሚደግፍበትን መንገድ ካወዲሁ ሊያሳውቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ የዛሬ 3 ዓመቱን ህገወጦች የማስመለሱን ተግባር አንስተው የመጡበትን አካባቢ ወጣቶች ልምድ ያካፈሉ አንድ የውይቱ ተሳታፊ አሁንም የተለየ ነገር እንደሌለ ነው ያሰመሩበት፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ባወጣው አዋጅ ገንዘባቸውንም ሆነ ንብረታቸውን እንዲያወጡ ወይንም በህጋዊ መልኩ ለፈቀዱት እንዲወክሉ በፈቀደው መሰረት በተለይ ትንሽም ቢሆን ያላቸውን ገንዘብ በጋራ በማድረግ በተለያዩ መንገዶች በሀገር ውስጥ ለመስራት ለሚፈልጉ ኤምባሲው ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደር አሚን አስረድተዋል፡፡ የሳዑዲ መንግስት አዋጅ ማውጣት ልማዱ ነው ሙሉ በሙሉ አይተገብረውም የሚለው በአንድ በኩል ሀገር ገብተንስ ምን አናደርጋለን የሚለው በሌላ በኩል በተሰጠው ጊዜ ወደ ሀገር የመመለሱን ሀሳብ ያደበዘዘው ይመስላል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ወይንም ተገን የሚያፈላልጉ አለም አቀፍ ተቋማት የሌሉባት ሀገር ናት በህገወጥነት የተፈረጁ የማንኛውም ሀገር ዜጎች ምርጫቸው አንድም በግድም ቢሆን ወደ መጡበት መመለስ አሊያም በሳኡዲ እስር ቤቶች መግባት ብቻ ነው፡፡

ስለሺ ሽብሩ 
አርያም ተክሌ 
ሸዋዬ ለገሠ