1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳዑዲ አረቢያና የኢራን ጠብ

ሰኞ፣ ጥር 2 2008

በትንሺቱ፤ በረሐማ፤ ደሐ አፍሪቃዊት ሐገር ዉሳኔ የጋዜጠኛ ሆሴይን ሻሪያትማዳሪን ያክል የተሳለቀ የለም።«የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር» አለ ካያት የተሰኘዉ ወግ አጥባቂ ጋዜጣ አዘጋጅ «በኢራን የጅቡቲ አምባሰድርን አስጠርቶ ሐገርሕ (ጁቡቲ) በዓለም ካርታ የምትገኝበትን ሥፍራ በ24 ሰዓት ዉስጥ እንድታ መለክተን»

https://p.dw.com/p/1HbZY
ምስል Getty Images/AFD/K. Desouki

የሳዉድ አረቢያ እና የኢራን ጠብ

ሰሞኑን እንዳዲስ የናረዉን የሳዑዲ አረቢያና የኢራንን ዉዝግብ ብዙዎች የሱኒ እና የሺዓ ሙስሊሞች ጠብ ይሉታል።ሌሎች መካከለኛዉ ምሥራቅን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረግ ሽኩቻ ዉጤት ነዉ ባዮች ናቸዉ።ብዙ የማይሰሙ ግን በሰል ያሉ የሚመስሉ እንደሚሉት ደግሞ የዉጪ በጣሙን የምዕራባዉያን ሐይላት ጣልቃ ገብነት ይሉታል።ሌሎች ሁሉም ብለዉ እርፍ።ብቻ ዉዝግብ፤ ጠብ ሽኩቻዉ፤ አረብን አዳርሶ-አፍሪቃ፤ፋርስን ተሻግሮ ቤጂንግ-ሞስኮ፤ ዋሽግተን-ብራስልስ ደርሷል።

የሳዑዲ አረቢያና የኢራን ጠብ አዲስ አይደለም።በ1980ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከዘጠኝ ዓመት በላይ ያስቆጠረዉ የኢራቅና የኢራን ጦርነት የባግዳድና የቴሕራን ጦርነት ብቻ አልነበረም።ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ፤ ፈረንሳይና አብዛኞቹ ምዕራባዉያን መንግሥታት የኋላ ጠላታቸዉን ሳዳም ሁሴይንን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲረዱ ነበር።

ሳዑዲ አረቢያ፤ ኩዌይት፤ ባሕሬን፤ ግብፅና ሌሎችም የአረብ መንግሥታት ኋላ ለአሜሪካኖች ጥቃት አጋልጠዉ የሰጡት የሳዳም ሁሴን መንግሥት ጦርን ደጋፊ፤ አስታጣቂ ነበሩ።በሊባኖሱ የርስ በርስ ጦርነትም የቴሕራን አያቱላሆች እና የሪያድ ነገሥታት ተፋላሚ ሐይላትን በመርዳት ተነክረዉበት ነበር።በቅርብ ዓመታትም ከየመን እስከ ሶሪያ፤ ከባሕሬን እስከ ፤ ሊባኖስ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን በእጅ አዙር ይዋጋሉ።

ሳዑዲ አረቢያ አንድ የሺዓ መንፈሳዊ መሪን በአሸባሪነት ከወነጀለቻቸዉ ሌሎች 46 ሰዎች ጋር በሞት በመቅጣትዋ ሰበብ አሁን የናረዉ ጠብ የፖለቲካ ተንታኝ ፉዓዝ ዤዤብ እንደሚሉት የቆየ ሽኩቻ ዉጤት ነዉ።ሽኩቻዉ ታሪካዊ፤ፖለቲካዊ፤ መልከዓ ምድራዊ ምክንያት ቢኖረዉም፤ የፖለቲካ አዋቂዉ እንደሚሉት ሁል ጊዜ በሐያማኖታዊ ሰበብ ይሸፈናል።

Iran Hossein Jaber Ansari Sprecher Außenministerium
ምስል Tasnim

«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለሶሪያዉ ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማግኘት እየጣረ ነዉ።በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሆነ ስምምነት ይደረጋል የሚል ተስፋም አለዉ።አሁን ግን ይሕን እርሳዉ።ብዙ ሰዎች የየመኑ ጦርነት ይቆማል የሚል ተስፋ አላቸዉ።ይሕንንም እርሳዉ።እኔ አሁን ቤይሩት ነዉ-ያለሁት።ከፍተኛ ዉጥረት አለ።የሊባኖሱ ጠንካራ የሺዓ ፓርቲ ሒዝቡላሕ፤ የሊባኖስ ሙስሊሞችን በሳዑዲ አረቢያ አንፃር ለማሠለፍ እየጣረ ነዉ።ባሕሬን ዉስጥም ዉጥረቱ ነግሷል።በባሕረ ሠላጤዉ አካባቢ በርካታ የሺዓ ማሕበረሰብ አለ።ሳዑዲ አረቢያና ኢራን በየጊዜዉ ተዘዋዋሪ ጦርነት የሚገጥሙት ለሥልጣን፤ለመልከዓ ምድረ-ፖለቲካዊ የበላይነት፤ ተፅዕኖ ለማሳደር ነዉ።ይሁንና እነዚሕ ምክንያቶች ሁል ጊዜ የሐያማኖታዊ ሐራጥቃ ትርጉም ይሰጣቸዋል።»

ጅቡቲ ሳዑዲ አረቢያን ለማስደሰት ከኢራን ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት አቋረጠች የሚለዉ ዜና ከተራዉ ኢራናዊ የገጠመዉ አፀፋ ምፀት ነበር።«ይሕን ስም ሰምቼዉ አላዉቅም» ፃፈ አንዱ ፌዘኛ «ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደነበረንም አላዉቅም» አከለ።«የፈጣሪ ያለሕ» ቀጠለ ሌላዉ «ጅቡቲን አጣን ምን ይበጀን ይሆን?» እያለ።

በትንሺቱ፤ በረሐማ፤ ደሐ አፍሪቃዊት ሐገር ዉሳኔ የጋዜጠኛ ሆሴይን ሻሪያትማዳሪን ያክል የተሳለቀ የለም።«የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር» አለ ካያት የተሰኘዉ ወግ አጥባቂ ጋዜጣ አዘጋጅ «በኢራን የጅቡቲ አምባሰድርን አስጠርቶ ሐገርሕ (ጁቡቲ) በዓለም ካርታ የምትገኝበትን ሥፍራ በ24 ሰዓት ዉስጥ እንድታ መለክተን»

ሰሜን ሱዳን እና ሶማሊያም ለሪያድ ያላቸዉን ታማኝነት ለማረጋገጥ ከኢራን ጋር የነበራቸዉን ግንኙነት አቋርጠዋል።ሰወስቱም ሐገራት የሱኒ ሙስሊም የሚበዙባቸዉ ናቸዉ።ከኢራን ጋር ግንኙታቸዉን ያቋረጡት የቴሕራን-ሪያድ ጠብ የሺዓ-ሱኒ ጠብ ሥለሆነ ነዉ ብሎ ማሰብ ግን ሲበዛ ከባድ ነዉ።

በምዕራባዉዉያን ማዕቀብ፤ክስና ወቀሳ ምክንያት ከዓለም የተገለለዉ የፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር መንግሥት ከሪያዶች ወግኖ የየመን ሁቲ አማፂዎችን መደብደብ ሲጀምር ዓላማዉ የሪያዶችን ርዳታና ድጋፍ ማግነት እንጂ ሐያማኖታዊ ወገንተኝነት እንዳልሆነ ግልፅ ነዉ።የመንግሥትነት አቅም፤ ቅርፅና መዋቅር ብዙ የሚጎለዉ የሐሰን ሸሕ ማሕሙድ መስተዳድር ከአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብ የበለጠ ጠላት የለዉም።የሞቃዲሾዉን መስተዳድር የዩጋንዳ፤ የኬንያ፤ የኢትዮጵያ እና የብሩንዲ ወታደሮች ባይጠብቁት ኖሮ አሸባብ መነቃቅሮ በጣለዉ ነበር።

በክርስቲያን አፍሪቃዉያን ወታደሮች የሚጠበቀዉ የሼኽ ማሕሙድ መስተዳድር ለሙስሊም አረብ ወግኖ ከሙስሊማይቱ ፋርስ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ የተጣደፈበት ምክንያት የሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ወገንተኝነት ብሎ መደምደም ግራ አጋቢ ነዉ።

ለተቀፅላዎቹ የአፍሪቃ መንግሥታት ቀርቶ ለራሳቸዉ ለሪያድ ነገስታትና ለቴሕራን አያቱላሆች እንኳን የጠብ፤ ሽኩቻ ዉዝግባቸዉ ምክንያት ሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ነዉ ብሎ መደምደም ሲበዛ ከባድ ነዉ።ጠቡ በአንድ ሰዉ ግድያ ሰበብ አሁን የናረበት ምክንያት ደግሞ ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ሳባስታይን ዞንስ እንደሚሉት ኢራን ከምዕራባዉያን ጋር ያላትን ግንኙነት ማሻሻሏ ነዉ።

Iran Protest in Teheran gegen Hinrichtung in Saudi-Arabien
ምስል Getty Images/AFP/A. Kenare

«ኢራን ዳግም እያንሰራራች ነዉ ማለት ይቻላል።ሳዑዲ አረቢያ ባንፃሩ መዳከሟ እየተሰማት ነዉ።ሳዑድ አረቢያ እዉነትም ሆነ ሐሰት፤ በጠላትዋ ኢራን በሚደገፉ ሐይላት የተከበበች ያሕል ይሰማታል። ባሕሬን፤ሶሪያ፤የመን፤ኢራቅ ሁሉም ጋ የኢራን ደጋፊዎች (እያቆበቆቡ ነዉ-ብላ ታስባለች።) ከምዕራባዉያን በተለይም ከዩናይትድ ስቴትስ የሚደረግላት ድጋፍም እንደቀነሰባት ነዉ የምትቆጥረዉ።በዚሕም ምክንያት በጥይት እንደቆሰለ አዉሬ ይሰማታል።ተከታዮቿ ሐገራት ባንፃሩ የሆነ እርምጃ ወስዳ ሐይሏን እንድታሳያቸዉ ግፊት ያደርጋሉ።በዚሕም ምክንያት አሁን ከዲፕሎማሲዉ መንገድ በወጣና ምናልባትም በቀድሞዉ ንጉስ አብደላሕ ዘመን ከሚደረገዉ በከፋ መንገድ እርምጃ ወስዳለች»

ይሁንና በአብደላሕ ዘመንም ቢሆን የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት በጠላትነት የተሞላ ነበር። ፎሪን ፖሊሲ የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ መፅሔት እንደዘገበዉ ንጉስ አብደላሕ ሰኔ 5 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉን የፈረንሳይ መከላከያ ሚንስትር ሔርቭ ሞሪን ተቀብለዉ ሲያነጋገሩ« በዓለም ላይ መኖር የማይገባቸዉ ሁለት መንግሥታት አሉ» አሏቸዉ አሉ ንጉሱ ለሚንስሩ «ኢራንና እስራኤል።»

ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ለማቆም ከምዕራባዉያን ጋር ሥትስማማ ስምምነቱን አጥብቀዉ የተቃወሙት ግን ሁለት መንግሥታት ነበሩ።የንጉስ አብደላሕዋ ሳዑዲ አረቢያ እና የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁዋ እስራል።እንዲያዉም እስራኤል ኢራንን ለመደብደብ ተዋጊ ጄቶች ብታዘምት ጄቶቹ በሳዑዲ አረቢያ የአየር ክልል ላይ እንዲበሩ የሪያድ ነገስታት ፈቀድዋል የሚል ዘገባም አለ።

በዚሕም ሰበብ አሁን እጅግ የተካረረዉ ጠብ ቁርቁስ ከሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ልዩነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ፤ መልከዓ ምድራዊ የበላይነት የመያዝ ሽሚያ፤ ለምዕራባዉያን የማደር ጥድፊያ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።የሳዑዲ አረቢያዉ የፖለቲካ ተንታኝ ጀማል አል ኻሽጂም ጠቡ የኤምባሲ፤ የሺዓ መንፈሳዊ መሪ መገደልም ጉዳይ አይደለም።

«አንድም የኢራንን የበላይነት ተቀብለን አሸናፊነቷን ማረጋገጥ አለብን አለያም እንቢኝ ማለት አለብን።ጉዳዩ የኤምባሲ ወይም የአል ኒምር መገደል አይደልም።የበላይነትን ለማረጋገጥ ከዚሕ የበለጠ ብዙ ጉዳዮች አሉ»

ሁለቱ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐብታም፤ ትላልቅ መንግታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1929 ነበር።ይሁንና የሳዑዲ አረቢያ መሥራችና የያኔዉ ንጉስ ሳዑድ በ1955 ቴሕራንን እስከ ጎበኙበት ድረስ ግንኙነቱ ብዙ የሚባልነት አይነት አልነበረም።ከአስር ዓመት በኳላ በ1966 ንጉስ ፈይሰል ቴሕራንን፤ ሻሕ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ሪያድን ሲጎበኙ ደግሞ በነግስታት የሚገዙትን ሐገራት ወዳጅነት ደመቀ።ምዕራባዉያን መንግሥታት በተለይም ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ የሶቬት ሕብረትን መስፋፋት ለመግታት ሁለቱን መንግሥታት ይረዱ፤ ወዳጅነታቸዉንም ይደግፉ ነበር።የዓለም እስላማዊ ጉባኤ፤ የዓለም ሙስሊሞች ሊግ፤ የእስላላማዊ መማክርት ድርጅት የሚባሉትን ዓለም አቀፍ እስላማዊ ማሕበራት የመሠረቱትም ዛሬ በሱኒና በሺዓ ሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ልዩነት ሰበብ ይዋጋሉ የሚባሉት ሐገራት ናቸዉ።ሳዑዲ አረቢያና ኢራን።

Iran Saudische Botschaft in Teheran gestürmt
ምስል picture alliance/dpa/M.-R. Nadimi

የሁለቱ ሐገራት ነገስታት በ1960ዎቹ ማብቂያዎች የተለዋወጧቸዉ ደብዳቤዎች የወዳጅነቱን ጥብቀት መስካሪዎች ናቸዉ።«ወድሜ ሆይ አስተዳደርሕን ዘመናይ አድርገዉ» አሉ የኢራኑ ሸሕ ለንጉስ ፌይሰል በጻፉት አንድ ደብዳቤያቸዉ።«ሐገርን ከፈት አድርግ፤ ወንድና ሴት ተማሪዎች አንድ ላይ እንዲማሩ አድርግ፤ ሴቶች ሚኒሰከርት እንዲለብሱ ፍቀድ-----እያሉ ቀጠሉ እና «አለበለዚያ ከዙፋንሕ ላይ ለመቆየትሕ እኔ ዋስትና ልሰጥ አልችልም።

ንጉስ ፈይሰል መለሱ «ግርማዊ ሆይ ምክርዎን አደንቃለሁ።አንድ ነገር ግን ላስታዉስዎ» እያሉ « እርስዎ የፈረንሳይ ሻሕ አይደሉም።ሕዝብዎ ዘጠና በመቶዉ---ሙስሊም ነዉ።ይሕን እንዳይዘነጉ።» ተባባሉና ለፈይሰል ከዙፋን መወገድ የሰጉት ሻሕ እራሳቸዉ ከዙፋን ተከነበሉ።1979።ጠቡም ከረረ።

በሰሞኑ እሰጥ አገባ አፍሪቃዉያኑ መንግሥታት ቀድማ ሳዑዲ አረቢያን ተከትላ ከኢራን ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኘት የቀነሰችዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ናት።የሁለቱ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ትላልቅ መንግሥታት ጠብ የጀመረዉም እኒያ ሰባት ትናንሽ ግዛቶች ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ መዉጣታቸዉ ሲታወጅ ነበር።1971።

የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች የአካባቢዉን ባላባቶች አባብለዉ በ1892 ከቱርክ እጅ የቀሟቸዉን የአቡዳቢ፤የዱባይ፤ የሻርጃሕ፤ የአጅማን፤ የራዕስ አል ኻይማ፤ የዑም አል ቁወይን ትናንሽ ግዛቶች ጥለዉ ለመዉጣት ሲዘጋጁ ለሰወስት ሐይላት ሰወት የተለያ መልዕክት ነበረዉ።

ለሰባቱ ኤምሬቶች ነፃ መንግሥት ለማወጅ የሚዘጋጁበት፤ ሳዑዲ አረቢያ ቢቻል ከራሷ የመቀላቀል ይሕ ቢቀር ተፅዕኖዋን ለማሳረፍ የማስላት ስልት የምታዉጠነጥነበት፤ ኢራን የጥንት ታሪክ ቆጥራ ግዛቶቹን ከራስዋ ለመቀየጥ የምታስብበት አጋጣሚ ነበር።

ታሕሳስ 1 1971 ዚያድ ቢን ሡልጣን አል ነሕያን እንደ መጀመሪያዉ ፕሬዝደንት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ነፃነት ከአቡዳቢ ሲያዉጁ፤ የኢራኑ ንጉስ መሐመድ ሬዛ ፓሕላቪ ከቴሕራን ያዘመቷቸዉ የኢራን መርከቦች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚባሉ ሰወስት ትናንሽ ደሴቶችን ተቆጣጠሩ።እኒያ ሥልታዊ ትናንሽ ደሴቶች ዛሬም ድረስ የኢራን አስራ-አረተኛ ክፍለ-ግዛት ናቸዉ።የኢራን እና የሳዑዲ አረቢያ ወዳጅነትም ያኔ መደፍረስ ጀመረ።

Großbritannien Proteste gegen die Hinrichtung von Nimr Al-Nimr in Saudi Arabien
ምስል Reuters/T. Melville

ይሁንና የኢራን እስላማዊ አብዮተኖች የሻሕ መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቬን መንግሥት አስወግደዉ ሥልጣን እስከ ያዙበት እስከ 1979 ድረስ ጠቡ የተካረረ አልነበረም።የኢራን እስላማዊ አብዮተኞቹ ሥርዓታቸዉን ያስፋፋሉ የሚለዉ የሳዑዲ ገዢዎች ሥጋት፤ በምዕራባዉያን ማስፈራሪያና ግፊት እየጋመ እነሆ ዛሬ ጅቡቲንም ጨመረ። እስኪ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ