1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አበይት ሳይንዊ ክስተቶች በ2016

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19 2009

አወዛጋቢ በሆነ በሆነ መልኩ ከሦስት ወላጆች በተገኘ ጽንስ በምድራችን የመጀመሪያው ልጅ መወለዱ ተሰምቷል። ህፃናት ሚጢጢ የራስ ቅል ይዘው እንዲወለዱ የሚያደርገው ከብራዚል የተነሳው ዚካ ተሐዋሲ የዓለም ስጋት ደቅኖ አልፏል። የጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት በርካታ ሳይንሳዊ ክስተቶች ታይተውበታል።

https://p.dw.com/p/2Uygc
USA Supermond über Los Angeles
ምስል picture-alliance/AP Photo/N. Ut

የሳይንሱ ዓለም አበይት ክስተቶች 2016

አወዛጋቢ በሆነ በሆነ መልኩ ከሦስት ወላጆች በተገኘ ጽንስ በምድራችን የመጀመሪያው ልጅ መወለዱ ተሰምቷል። ህፃናት ሚጢጢ የራስ ቅል ይዘው እንዲወለዱ የሚያደርገው ከብራዚል የተነሳው ዚካ ተሐዋሲ የዓለም ስጋት ደቅኖ አልፏል። ከዓለማችን ጋር ተመሳሳይ የሆነች ለኑሮ ተስማማሚ ኤክሶፕላኔት ተገኘች ተብሏል። ለአምስት  ዓመታት ኅዋው ላይ ስትከንፍ የቆየች ጁኖ የተሰኘች መንኲራኲር ጁፒተርን አልፋ ሄዳለች።  

በሮቦት እገዛ ቁፋሮ የሚያከናውን መሣሪያን የጫነች ሰው አልባ መንኲራኲር «ኤክሶማርስ» በሚል ተልእኮ ወደ ማርስ ተወንጭፋለች። ፋልኮን 9 መንኲራኲር ደግሞ ኅዋ ላይ ወደሚገኘው ዓለም አቀፍ ጣቢያ ቁሳቁስ አድርሳ ወደ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ለመመለስ በቅታለች። ምድር አንድ ቀን በኃያል ፀሓያዊ ነበልባል ልትመታ ትችል ይሆናል ተብሏል። እጅግ ግዙፍ ጨረቃ የምሽቱ ሰማይ ላይ ተስረቅርቃለች። ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት በርካታ ሳይንሳዊ ክስተቶች ታይተውበታል። 

የጎርጎሪዮሱ 2016 ዓመት በባተ በሁለተኛው ወር ማለትም የካቲት ላይ ዓለምን ያስደነገጠ ዜና ተሰምቷል። የዚካ ተሐዋሲ። ብራዚል ውስጥ በስፋት የታየው የዚካ ተሐዋሲ ስርጭት በመላው ዓለም እንዳይዳረስ አስግቶ ነበር። 

ዚካ ተሐዋሲ አስተላላፊ ትንኞችን ለመግደል መድሃኒት ሲረጭ
ዚካ ተሐዋሲ አስተላላፊ ትንኞችን ለመግደል መድሃኒት ሲረጭምስል Reuters/O. Rivas

ዚካ የዩጋንዳ ጫካ ውስጥ የተገኘው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1947 ዓመት ነው። ስያሜውንም በዚያው ይዞ ዚካ ተሐዋሲ ተብሏል። ተሐዋሲው በዋናነት ደም መጣጭ በሆነች ትንኝ ይተላለፋል። በተለይ ነፍሰ-ጡር ሴቶችን እና ሕፃናትን ያጠቃል። 

ዚካ ተሐዋሲ ሕፃናት ሚጢጢ የራስ ቅል እና የተጎዳ አንጎል ይዘው እንዲወለዱ የማድረግም ተጽዕኖ አለው። በዚህ መልኩ የተወለዱ ህፃናት ቁጥር ብራዚል ውስጥ በዚህ ወር 2,228 እንደሚደርሱ ተገልጧል። ሌሎች 3,173 ጨቅላዎች የራስ ቅላቸው ማነስ የተከሰተው በዚካ ተሐዋሲ ይሁን በሌላ ምክንያት እየተጠና እንደሆነ ተገልጧል። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ወደ ቴክሳስ ግዛቷ ብሮውንስቪሌ ከተማ ነፍሰ-ጡር ሴቶች እንዳይጓዙ ሰሞኑን አስጠንቅቃለች። በከተማው የዚካ ተሐዋሲ ስጋት አለ ሲል ያስጠነቀቀው የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል ነው። 

በወርኃ የካቲት ከተገኘ ሌላ አስደናቂ የሳይንሳዊ ግኝት መካከል የስበታዊ ኃይል ሞገድ ይገኝበታል። ስበታዊ ኃይል ሞገድ ስለመኖሩ ከ100 ዓመታት በፊት የተነበየው ጀርመናዊው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንሽታይን ነበር። ግኝቱ በተግባር መረጋገጡ በእርግጥም አይንሽታይን ልክ ነበር አስብሏል። 

ለመኾኑ በሣይንሱ ዘርፍ በተለይም በ«አስትሮ-ፊዚክስ» ከፍተኛ እመርታ የተባለለት ይህ ግኝት ምንድን ነው? በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የጠፈር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን የሚተነትኑት ሣይንቲስት ዶ/ር ያብባል ታደሠ መልስ አላቸው። 

«ይህ የተገኘው የስበት ኃይል ሞገድ ከ100 ዓመት በፊት በአልበርት አንሽታይን ተተንብዮ ነበር። አሁን ሙሉ ለሙሉ መኖሩ ተረጋግጧል።»

የስበት ኃይል ሞገዶች በጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ተቋም
የስበት ኃይል ሞገዶች በጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ተቋም ምስል picture-alliance/dpa/M. Hanschke

ያለ አንዳች ስህተት ተለክተዋል የተባሉት እነዚህ የስበት ኃይል ሞገዶች፤ ጽልመታዊ ጉድጓዶች (black holes)ወይንም ኒውትሮን ከዋክብት ከ1,3 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እርስ በርስ ተሽከርክረው ሲላተሙ የተፈጠሩ ናቸው እንደ ሣይንስ ማብራሪያ። ሞገዶቹ በብርሃን ፍጥነት ተጉዘው ምድር የደረሱትም እጅግ ተዳክመው ነው። ተመራማሪዎች እነዚህ የስበት ኃይል ሞገዶች መኖራቸውን በሰው ሠራሽ ልኬት ይፋ ያደረጉት የካቲት 11 ቀን ነበር። ስበታዊ ኃይል ሞገዶቹ የተለኩት በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (LIGO) በተባለው ማለትም በረቂቅ የብርሃን ልቄት የስበት ኃይል ሞገዶች መለኪያ መሣሪያ ነው። 

ምድር ከፀሐይ ከምትርቀው 40 ጊዜ እጥፍ ትርቃለች፤ ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ። ይኽች ከፕላኔቶች ወዲያ በርቀት የምትገኘው ድንክ ፕላኔት፥ ለዘመናት እንቆቅልሽ ሆና ቆይታለች። ከእነ አምስት ጨረቆቿ ከሥርዓተ-ፀሐይ ሽክርክሪት ጠርዝ ላይ ተንሳፋ ምሥጢር ሆና ዘመን ፈጅታለች። 

ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ግን ፕሉቶ በየጊዜው አስደናቂነቷ እየጎላ ነው።  የድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ  ከርሠ ምድር ለሕይወት አመቺ በሆነ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ የተሞላ መሆኑን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ በናሣ የምርምር ተቋም ስትታይ
ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ በናሣ የምርምር ተቋም ስትታይምስል Reuters/NASA/JHUAPL/SwRI

አዲስ አድማስ (New horizons) የተሰኘችው ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር እፕሉቶ ጥግ ደርሳ ድንኪቱን ፕላኔት ትበረብር ይዛለች። በበረዶ ግግር በተሞላው ከርሰ ምድሯ ፕሉቶ ከምድር የማይተናነስ የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ ሸሽጋ ኖራለች። ቋጥኞች፣ የበረዶ ግግሮች፤ አሁን ደግሞ የበረዶ ቅይጥ ውኃዋ ተደርሶባታል፤ ድንኳ ፕላኔት ፕሉቶ። በደቡብ አፍሪቃ፤ ኖርዝ ዌስት ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪው ዶክተር ጌትነት ፕሉቶ ላይ ተገኘ ስለተባለው የበረዶ ቅይጥ የውቅያኖስ ውኃ እንዲህ ነበር ያብራሩት። «አንድ ድንክ ፕላኔት ከፀሓይ በራቀ ቁጥር እየቀዘቀዘ ነው የሚሄደው። ውኃው ክፍል መቶ ሜትር ጥልቀት አለው።» 

አብዛኛው ክፍሏ በጋዞች ክምችት የተሞላ ነውጠኛ ፕላኔት ናት። የአቧራ ቧሂት ጀርባዋን እንደቀለበት ሸብቦ የሚጋልባት፤ መግነጢሳዊ ኃይሏ ያገኘውን ጎትቶ የሚፈጠፍጥ፦ ጁፒተር። ፀሓይ ስትፈጠር በቃኝ ብላ የተወቻቸው በርካታ ቁሶች ተግተልትለው የሰፈሩባት ግዙፏ የጋዝ ክምችት ፕላኔት፦ ጁፒተር። በ67 ጨረቆቿ ታጅባ ኅዋው ላይ ትዞራለች፤ ትዘውራለችም። ጠፈርተኞች የፕላኔቶች ንጉሥ ሲሉ ያሞካሿታል፦ ንጉሥ ፕላኔት።  ሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ የምርምር ተቋም ውስጥ የጁኖ ቀዳማይ መርማሪ የኾኑት ስኮት ቦልተን 1 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ከተደረገባት ቃኚ መንኲራኲር ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

«እጅግ አስደናቂ ፕላኔት ናት። የጁኖ ዋነኛ ተግባር ከጁፒተር ገጽታ ሥር ያለውን መመልከት ነው። ዝቅ ብለን ተጠግተንም እውስጥ ምን እንዳለ እንመለከታለን። ፕላኔቷ እንዴት ተዋቀረች? ይኽስ ገጽታዋ ምን ያኽል ጥልቅ ነው? የሚለውን አንስተን ምሥጢሯን ለመረዳት እንጥራለን።»

ነውጠኛዋ ፕላኔት ከሌሎች ፕላኔቶች ጋር ሆና የምተሽከረከራት ፀሓይ ምናልባት አንዳች ፀሓያዊ ነበልባል ወደ ምድራችን ትሰድ ይሆንን የሚል ጥያቄም በ2016 ሳይንቲስቱ አጭረዋል። 

የጁፒተር ደቡባዊ ዋልታ ምስል በጁኖ ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር የተነሳ
የጁፒተር ደቡባዊ ዋልታ ምስል በጁኖ ኅዋ ቃኝ መንኲራኲር የተነሳምስል picture-alliance/AP Photo/psison|File|Filed|9/2/2016

የምድራችን ፀሓይን ጨምሮ በሰፊው ኅዋ ላይ ፈሰው የሚርመሰመሱ እልፍ አእላፋት ከዋክብት፥ እውስጣቸው ፍንዳታዎችን ያከናውናሉ፤ በዚያም ፀሓያዊ ነበልባሎችን ያመነጫሉ። ከዋክብቱ አልፎ አልፎ መጠኑ ከተለመደው ላቅ ያለ ነበልባልም ወደ ምድር ይለቃሉ። የነበልባሉ ብርታት እና ግለት ከተለመደው እጅግ ሲልቅ ኃያሉ ነበልባል (superflare) ይከሰታል።

ኃያሉ ፀሐያዊ ነበልባል በንጽጽር ሲታይ፦ ከርሰ ምድር እያማቧለቀች ከምትተፋው እሳተ-ገሞራ ዐሥር ሚሊዮን ያኽል መጠን እንደሚደርስ ይጠቀሳል። ዶር ጥላዬ ታደሰ በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ወይም ናሳ  ከዐሥሩ የምርምር ጣቢያዎች ግዙፍ በሆነው እና ዐሥር ሺህ ሠራተኞች በሚገኙበት ጎዳርድ የኅዋ ማዕከል ውስጥ ፀሓያት ላይ ስለሚከሰቱ ፍንዳታዎች ይመራመራሉ። 

«የተለያዩ ፍንዳታዎች ከፀሓይ ላይ ይነሳሉ። የነዚህም ምክንያት ፀሓይ ክብ እና መግነጢሳዊ ኃይል ስላላት ነው። ፀሓያዊ ፍንዳታ ዋና ምክንያቱም የመግነጢሳዊ መስኩ [እየተኮማተረ መዘርጋቱ ነው]»ብለዋል።

የኖቤል ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ
የኖቤል ሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ ምስል picture-alliance/dpa/J. Nukari

በ2016 በሕክምናው ዘርፍ ሲበዛ ያነጋገረ ክስተት ታይቷል። ተመራማሪዎች ከዐሥርተ ዓመታት ምርምራቸው በኋላ ከሦስት ሰዎች ዘረ-መል በመውሰድ የሦስት ወላጆች አንድ ልጅ እንዲወለድ አድርገዋል። በሃያማኖት ሰዎች እና የሞራል አቀንቃኞች ዘንድ ጉዳዩ እጅግ ተወግዟል። ዘረ-መሉ ከሦስት ሰዎች በመርፌ ተወስዶ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ከዳበረ በኋላ መስከረም ወር ላይ  የመጀመሪያው ሦስት ወላጆች ያሉት ህጻን ተወልዷል። በተመሳሳይ ሳይንሳዊ መንገድ ቻይና እና ዩክሬን ውስጥ ሦስት ወላጆች ያሏቸው ልጆች መወለዳቸው ተዘግቧል። 

የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ይፋ የሆነበት 2016 በአካላዊ አወቃቀሩ እና ፈጣን ሥርጭቱ ልዩ የሆነ የጉንዳን ሠራዊት ከኢትዮጵያ ተነስቶ ለዓለም ስጋት ሊሆን ይችላል የሚል ዘገባ የተደመጠበት ዓመት ነው። ለ70 ዓመታት ስትናፈቅ የቆየችው ልዕለ ጨረቃ (supermoon) የታየችው በዚሁ ዓመት ነው።

2016 የጠፈር ተመራማሪዎች በሌላኛው ሩቅ ዓለም ምናልባት ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ካሉ ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለን ሲሉ የገለጡትም ዓመት ነው። ግንኙነቱን ለመጀመርም ሳይንቲስቱ ወደ 1 ሚሊዮን  ዶላር ግድም ለማሰባሰብ አቅደዋል። ገንዘቡ በሬዲዮ ሞገድ መልእክት ወደ ኅዋ ለማስተላለፍ ያስችል ዘንድም ጠንካራ ማቀባበያ ለመገንባት በከፊል ይውላል ብለዋል። ይህ የሥራ ዕቅድ በእንግሊዝኛው (Meti) የሚል ቅጽል አለው። በሌላኛው ዓለም ወደሚኖሩ ፍጡራን መልእክት የማስተላለፍ ብቃት እንደማለት ነው ትርጓሜው በግርድፉ። 

ልእለ-ጨረቃ ከ70 ዓመታት በኋላ የምሽቱ ሰማይ ላይ ጎልታ
ልእለ-ጨረቃ ከ70 ዓመታት በኋላ የምሽቱ ሰማይ ላይ ጎልታምስል picture-alliance/dpa/G. Varga

በፊዚክሱ ዓለም የዘመናችን ጠበብት ስቴፈን ሐውኪንግ  ይህ ሙከራ አንዳች መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። «መልእክት መላኩ አደጋ ውስጥ ይከተናል» ብሏል።

ልናናግራቸው የምንፈልጋቸው ማናቸውም የሌላ ዓለም ፍጡራን እኛን እንደ ተሐዋሲ ነው የሚቆጥሩን፤ እናም ሊገድሉን ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ከምድረ-ገጽ ሊያጠፉን ይችላሉ ሲሉም ሳይንቲስቶች የግንኙነት ሙከራው እንዳይደረግ ወትውተዋል። 

በዚህም አለ በዚያ ግን ሣይንቲስቱ የሌላኛው ዓለም ፍጡራን እስኪያናግሩን ድረስ አንጠብቅም፦ ይልቁንስ እኛ መልእክት እንልክላቸዋለን ሲሉ ቁርጠኛ አቋማቸውን አሳይተዋል።

ግንኙነቱንም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 ዓመት ለመጀመር አቅደዋል። ነገሩ «ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል» እንዳይሆን በሚል በርካታ ሳይንቲስቶችን አስግቷል። 
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ