1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስኮትላንድ የህዝበ ውሳኔ ጥያቄ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2009

የስኮትላንድ መንግሥት በስኮትላንድ ከብሪታንያ ነጻ መውጣት አለመውጣት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይን ጠየቀ። የስኮትላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጅን ዛሬ ለሜይ በጻፉት ደብዳቤ ስኮትላንድ ከአውሮጳ የጋራ ገበያ መውጣት እንደማትፈልግ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/2aTVf
Schottland | Parlament stimmt für neues Unabhängigkeitsreferendum
ምስል Getty Images/WPA Pool/ An. Buchanan

ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት መልቀቂያ ይፋ ማመልከቻ  ካስገባች ከሁለት ቀናት በኋላ ስተርጀን በጻፉት ደብዳቤ የስኮትላንድ ህዝብ መፃኤ ዕድሉን የመወሰን መብት አለው ብለዋል። ባለፈው ሰኔ በተካሄደው የብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት መውጣት አለመውጣት ህዝበ ውሳኔ ላይ ሶኮትላንዶች ከኅብረቱ ጋር መቆየትን ነበር የመረጡት። በጎርጎሮሳዊው 2014 ስኮትላንድ ከብሪታንያ ትነጠል አትነጠል በሚለው ጥያቄ ላይ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከህዝቡ 55 በመቶው ከብሪታንያ ጋር መቆየትን መርጦ ነበር። ሆኖም ስተርጀን ከዚያን ወዲህ ሁኔታዎች በመለዋወጣቸው ሌላ ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ያስፈልጋል ነው የሚሉት። ስተርጀን ስኮትላንድ ከኅብረቱ ጋር እንድትቆይ ቢጠይቁም የብሪታንያ መንግሥት ተቃውሞታል። የስኮትላንድ ፓርላማ ሁለተኛ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ባለፈው ማክሰኞ በ69 በመቶ አብላጫ ድምጽ ተስማምቷል። ሆኖም ካለለንደን መንግሥት ይሁንታ ህዝበ ውሳኔው ሊካሄድ አይችልም። 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ