1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስኳር ሕመምን እንከላከል

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2008

የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር በመላዉ ዓለም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1980ዓ,ም ወዲህ በአራት እጅ እጥፍ ገደማ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈዉ ሳምንት ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ እንደሚለዉ በተለይ ችግሩ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ አላቸዉ በሚባሉት ሃገራት እጅግ በፍጥነት እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1IU6b
12.11.2015 DW fit und gesund Diabetes_Teaser

የስኳር ሕመምን እንከላከል

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1980ዓ,ም የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር 108 ሚሊየን ነበር። ከ34 ዓመታት በኋላ ማለትም በ2014ዓ,ም ደግሞ 422 ሚሊየን መድረሱ ተመዝግቧል። ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ቀን ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ነዉ የታሰበዉ። በዚህ ዓመት የዓለም የጤና ድርጅት ይህን ቀን አስመልክቶ ባሰራጨዉ መረጃ መሠረት ከ11 አዋቂ ሰዎች አንዱ የስኳር ሕመም ተጠቂ መሆኑን አመልክቷል። ይህን እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆመዉ የድርጅቱ መግለጫ ሰዎች የአኗኗር ይትበሃላቸዉን እንዲያስተካክሉና አመጋገብ ላይም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። የስኳር ሕመም የምንለዉ በህክምናዉ ዲያቤቲስ የሚባለዉ በአሁኑ ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት በጣም በመስፋፋቱ የሀብታም በሽታ መባሉ ቀርቷል እየተባለ ነዉ።

BdT Fettleibigkeit
ክብደትን መቆጣጠርምስል picture-alliance/dpa/S. Kahnert
Martin-Luther-Universität Halle - Blutuntersuchung
በየጊዜዉ ምርመራ ማድረግምስል picture-alliance/dpa/W. Grubitzsch

ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ቀንን አስመልክቶ የዓለም የጤና ድርጅት WHO ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ የስኳር ሕመምተኞች ቆጥር ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረዉ በአራት እጅ እጥፍ ጨምሯል። በዓለማችን በየዓመቱ 3,7 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ነፍስ የሚቀጥፈዉ በደም ዉስጥ ከፍተኛ የስኳር መጠን መከማቸት መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ተመራማሪዎች እና ሃኪሞች እንደሚሉት አንድ የመፍትሄ ርምጃ ካልተወሰደ በቀር ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ከፍ እያለ ሊሄድ ይችላል። የስኳር ሕመም የሚያደርሰዉን ጉዳት በጥቅሉ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚባሉት ሁለቱም የዲያቤቲስ ዓይነቶች የሚያመጡት ሲሆን በተለይ ሁለተኛዉ ዓይነት የሚባለዉ በጤናም ሆነ በሕይወት ላይ የሚያስከትለዉን መዘዝ ለመቀነስ የአኗኗር ይትበሃልን መለወጥ እንደሚያስፈልግ ነዉ የተገለጸዉ። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከሶስቱ አንዱ ሰዉ ከመጠን በላይ የወፈረ መሆኑን የተጠቆመዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ