1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስዊድን ዕስረኞች መለቀቅና የእስር ቤት ቆይታቸው

ዓርብ፣ ግንቦት 17 1999

የኢትዮጵያ መንግስት በተጠርጣሪ አሸባሪነት ካሰራቸው የውጭ ዜጎች መካከል ሶስቱን ስዊድናውያን ባለፈው ሳምንት ለቋል ። ስዊድናውያኑ የታሰሩት ለአምስት ወራት ነበር ። በእስር ላይ ሳሉም ስቃይና እንግልት እንደደረሰባቸው ጠበቃቸው ስዊድን ውስጥ አስታውቀዋል ።

https://p.dw.com/p/E0XU

እስረኞቹ ደረሰባቸው ስለተባለው ስቃይ ዶይቼቬለ ራድዮ የአማርኛው ክፍል የጠየቃቸው አንድ የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው የጠበቃውን መረጃ ለማግኘት እየጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል ። ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩት ሶስቱ ስዊድናውያን ተለቀው ወደ ሀገራቸው ስዊድን መመለሳቸው እንደተሰማ የስዊድን መንግስት በዕርምጃው መደሰቱን ነበር የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የገለፀው ። የስዊድናውያኑ ጠበቃ ብዮርን ሁርቲክም የዕስረኞቹን መለቀቅ ያልተጠበቀ ግን ዕጹብድንቅ ብለውት ነበር ። እኝሁ ጠበቃ ትናንት ለአንድ የስዊድን ህዝብ ራድዮ ጣቢያ እንዳስታወቁት ደግሞ ስዊድናውያኑ በኢትዮጵያ ዕስርቤት ተሰቃይተዋል ፤ ተንገላተዋል ። የታሰሩት ከማንም በማይገናኙበት አንድ ሜትር ተኩል ካሬ ስፋት በነበረው ጠባብ ቦታ ውስጥ ነበር ። አብዛኛውን ጊዜም እጅና እግራቸው በካቴና እንደተጠፈረ ነው የቆዩት ። ሲተኙ እንክዋን የታሰረው እጃቸው አይፈታም ። ከዚህ በተጨማሪም በምርመራ ወቅት አካላዊና ስነልቦናዊ ስቃይ ደርሶባቸዋል ብለዋል ጠበቃ ቦይርን ሆርቲክ ። ጠበቃው ስዊድናውያኑ ደረሰባቸው ስላሉት ዕንግልት ባልደረባችን ሉድገር ሻዶምስኪ የጠየቃቸው የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት ቃል አቀባይ ኒና ኤርስማን እስካሁን ስለሰዎቹ አያያዝ ምንም ዓይነት ነፃ ዘገባ የለንም ነው ያሉት ። አክለውም የጠበቃውን መረጃ ለማግኘት እየጠበቅን ነው ብለዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት ሶስቱ ስዊድናውያን ከሶማሊያ ተዋጊዎች ጋር ገጥመው ወግተውናል ነው የሚለው ። የስዊድን መንግስት በበኩሉ ለዚህ ምንም ማረጋገጫ የለንም ነው መልሱ ። ቃል አቀባይ ኒና አርስማን እንደሚሉት ዜጎቻቸው የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን በይፋ አልተገለፀላቸውም
“እንዲያውም ፤ የታሰሩበትን ትክክለኛውን ምክንያት በፍፁም አልነገሩንም ። ምንም ዓይነት ክስና ትክክለኛ ህጋዊ አካሄድ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የተያዙት ግለሰቦች በተቻለ ፍጥነት እንዲለቀቁ ጠይቀናል ። ይህም እነርሱን ወደ ስዊድን ለማምጣት ቅድሚያ የሰጠነው ጉዳይ ነበር ። “
ስዊድናውያኑ ከአምስት ወራት በፊት ሶማሊያ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግስትና በሶማሊያ ፍርድ ቤቶች ህበረት መካከል ውጊያ እንደተጀመረ ከሶማሊያ ሸሽተው ኬንያ ከገቡ በኃላ እዚያ ታስረው ወደ መቅዲሾ ከተላኩ በኃላ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱት ። ለመሆኑ የስዊድን መንግስት ግለሰቦቹ ሶማሊያ ለምን እንደሄዱና የት እንደተያዙ ያውቅ ይሆን ?
“በትክክል የት እንደተያዙ አናውቅም እንዲሁም በዕርግጥ ሶማሊያ ውስጥ ምን ይሰሩ እንደነበርም አናውቅም ። ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት አንስቶ ሰዎች ወደ ሶማሊያ እንዳይሄዱ እንመክራለን ። ካለፈው ገና ወዲህም ማናቸውም ሶማሊያ የሚገኝ የስዊድን ዜጋ ሶማሊያን ለቆ እንዲወጣ ተናግረናል ። ምክንያቱም እዚያ ያለው የጦርነት ዓይነት ሁኔታ ነው ። ሆኖም እነርሱ እዚያ ምን ይሰሩ እንደነበር አናውቅም ። “
ሶስቱን ስዊድናውያን ለማስፈታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተካሄደው ድርድር የስዊድን መንግስት የልማት ዕርዳታን መያዝን የመሳሰሉ ግፊጦችን አድርጎ እንደሆነም ቃል አቀባይ ኒና አርስማን ተጠይቀው ነበር ።
“የተካሄዱትን ድርድሮችና በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸውን ወገኖች ዝርዝር ይፋ ወደ ማድረግ አንገባም ። ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር የሚያገናኘንን አማራጭ በሙሉ ሞክረናል ። እዚህ ስዊድን እንዲሁም በአዲስ አበባና በኬንያ በያለበት ሁሉ ግባችን ለመምታት ይኽውም ለፍርድ እስካልቀረቡ ድረስ ከዕስር እንዲለቀቁ ያለውን አማራጭ ሁሉ ሞክረናል “
በአሸባሪነነት ተጠርጥረው ሶማሊያ ውስጥ የታሰሩ አርባ አንድ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር ። ከመካከላቸው የዩናይትድ ስቴትስ የቱኒዚያ የዩጋንዳ የሳውዲ አረብያ እና የታንዛኒያ ዜጎች ይገኙበታል ። ስለተለቀቁት የስዊድን ዜጎችና ስለተቀሩት ዕስረኞች የኢትዮጵያ መንግስት ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሀላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም ።