1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኛ አስተርጓሚዎች

ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2007

ባለፈው ማክሰኞ ብቻ 3,709 ያህል ስደተኞች ምሥራቅ አውሮፓን አቋርጠው ደቡብ ጀርመን ሙኒክ ከተማ ገብተዋል። የጀርመን ወቅታዊ ፈተና ስደተኞቹን የምታቆይበት ቦታ ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን፤ ከስደተኞችቹ ጋር ለመግባባት ስደተኞቹ የሚናገሩትን ቋንቋ የሚያስተረጉሙ ማፈላለግ ነው።

https://p.dw.com/p/1GQkj
Bildergalerie Flüchtlingsunterbringung in Deutschland
ምስል imago/epd

የስደተኛ አስተርጓሚዎች

በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ እጅግ አነጋራሪ እና አሳሳቢ የሆነው የስደተኞች ጉዳይ ነው። ሠሞኑን ጀርመን የሚገቡት አብዛኞቹ ስደተኞች ፤ የሶርያ እና የአፍጋኒስታን ዜጎች ሲሆኑ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ከመካከላቸው አልጠፉም። እነዚህ ስደተኞች እዚህ ሀገር ሲገቡ እና ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው አስተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል።

ዳንኤል ተሰማ፤ በምዕራብ ጀርመን - የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ ነው። በሙያው ምግብ አብሳይ ሲሆን በትርፍ ጊዜው ደግሞ ወደ ጀርመን ለሚገቡ ስደተኞች በአማርኛ አስተርጓሚነት ያገለግላል። ላለፉት 14 ዓመታት ጀርመን ቤቱ የሆነችው ዳንኤል ፤ ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ለስደተኞች በአማርኛ ቋንቋ ከሚያስተረጉሙ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነው። የዮንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ቤተል እንደሻውም በትርፍ ጊዜዋ ትተረጉማለች። ጀርመን ሀገር 13 ዓመት ያስቆጠረችው ቤተል «አውስሌንደር ዓምት » በመባል ከሚጠራው የውጭ ዜጎችን ጉዳይ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት አልፎ አልፎ የስልክ ጥሪ ይደርሳታል።

Griechenland Flüchtlinge aus Eritrea vor Rhodos
አብዛኞቹ የአፍሪቃ ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ነው ኢጣሊያ የሚደርሱትምስል picture alliance/AP Photo

ዳንኤል መተርጎም ከጀመረ አምስት ዓመት ገደማ ሆነው። እሱም ይሁን ቤተል የሚተረጉሙት አልፎ አልፎ ነው። ሁለቱም ወጣቶች ሲተረጉሙ ትልቁ ፈተናቸው የሚሰሙትን ታሪክ በትክክል መተርጎሙ ሳይሆን፤ የስደተኞቹ ችግር ውስጣቸው መቅረቱ ነው።ከዚያ ባለፈ ግን ፤ ያለ ክፍያ ርዳት ለሚፈልጉ ስደተኞች ድጋፉን እየለገሰ እንደሆነ ዳንኤል ይናገራል።

ዳንኤል ጊዜ ካለው ከሚኖርባት ከተማ ኮሎኝ በአቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች እየተዘዋወረ ይተረጉማል። አንዳንዴ ፤እንደ ቤተል አስተርጓሚዎች በአካል መገኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ደግሞ መስሪያ ቤቱ በስልክ እንዲተረጉሙላቸው ይጠይቃል።

ጀርመን ለገቡ ስደተኞች በአማርኛ ቋንቋ ስለሚያስተረጉሙ ሁለት ወጣቶች የስራ ተሞክሮ የበለጠ ከድምፅ ዘገባው ያገኛሉ።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ