1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች መስህብ ደቡብ አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2009

ብዙዎች ደቡብ አፍሪቃን ልክ እንደ ጀርመን የተሻለ የኑሮ እድል የሚገኝባት አድርገው ይመለከቷታል።  የሶርያ ቀውስ እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አብዛኞቹ ስደተኞች ከሚገኙባት ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች። እስከ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ስደተኞች ነበሩ ተገን የጠየቁት።

https://p.dw.com/p/2Xzo4
Flüchtlinge in Südafrika
ምስል Getty Images/AFP/M. Safodien

flüchtlinge in südafrika - MP3-Stereo

ደቡብ አፍሪቃ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ ፍልሰትን በተመለከተ ሰፊ ተሞክሮ አላት፤ የደቡብ አፍሪቃ የስደተኞች ተገን አሰጣጥ ፖሊሲም  ከተመድ የስደተኞች ጥበቃ ውል የተሻለ መሆኑ ይነገራል። ታድያ ጀርመን እና የአውሮጳ ህብረት ከደቡብ አፍሪቃ ትምህርት ሊወስዱ ይችሉ ይሆን?

ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተሰደደው የቡሩንዲ ተወላጅ ዠርሜይን በደርበን ከተማ ማዕከል በሚገኝ አንድ ጎስቋላ ህንፃ ስፋቱ አስር ካሬ ሜትር በሆነ፣ ሶስት አልጋዎች በተዘረጉበት እና ጥቂት ልብሶች ግድግዳ ላይ በተሰቀሉበት አንድ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ይኖራል። ለዚህ የተጨናነቀ ጠባብ ክፍል 90 ዩሮ ይከፍላል። ግን የ37 ዓመቱ በወቅቱ ስራ አጥ በመሆኑ ወደፊት ኪራዩን እንዴት እንደሚከፍል አያውቀውም፣ ካልከፈለ ደግሞ መንገድ አዳሪ የመሆን ስጋት ተደቅኖበታል። ይሁንና፣ ከ12 ዓመት በፊት ከትውልድ ሃገሩ ቡሩንዲ ሲወጣ ግን የተሻለ ኑሮ የማግኘት ህልሙ አሁን የደረሰበትን ዓይነት ሁኔታ ይመስላል ብሎ አልጠበቀም አልነበረም።
« ቡሩንዲ ውስጥ ያኔ ጦርነት ነበር። ወላጆቼ በውጊያ ከተገደሉ በኋላ ራሴን ለማዳን መሰደድ ነበረብኝ። ስለዚህ ህይወቴን ለማዳን ስል ነበር ወደ ደቡብ አፍሪቃ የመጣሁት። »
ብዙዎች ደቡብ አፍሪቃን  በመላ አፍሪቃ ጥሩ የኑሮ እድል ሊገኝባት የምትችል ሃገር አድርገው ነው የሚያዩዋት። ጦርነትን እና የኃይል ተግባርን የሚሸሹ ወይም ስራ፣ እንዲሁም፣ ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ኑሮ የሚፈልጉት ወደ ሶስት ሚልዮን የሚጠጉ የኢትዮጵያ፣ ሶማልያ፣ ቡሩንዲ፣ ኮንጎ፣ ዚምባብዌ እና የሌሎች ሃገራት ዜጎች 53 ሚልዮን ሕዝብ ባላት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ይኖራሉ። ብዙዎቹ እንደ ሃገር ጎብኚ በሕጋዊ መንገድ ደቡብ አፍሪቃ ከገቡ በኋላ በዚያው እንደሚቀሩ የሃገሪቱ መንግሥት የሚያወጣቸው መዘርዝሮች ያሳያሉ። ሌሎች ደግሞ በሚገባ ጥበቃ የማይደረግለትን የሃገሪቱን ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ  ይሻገራሉ። ለድንበር ጠባቂዎችም ጉቦ ሰጥቶ ማለፍም የተለመደ አሰራር ነው።  ሕገ ወጥ ሰዎች አሸጋጋሪዎችም በድንበሩ አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ፣ ምን ያህል ሰዎች እንደሚያስገቡ ግን በውል አይታወቅም።  በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ፣ ደቡብ አፍሪቃ ጥሩ የሚባል የስደተኞች አቀባበል ሕግ አላት። እንዲያውም ሃገራት ለስደተኞች ጥበቃ ከሚሰጡበት የተመድ የዠኔቭ ውል የበለጠ ለዘብተኛ መሆኑን ነው በጆሃንስበርግ የዊትዎተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት እና ህብረተሰብ ማዕከል ባልደረባ ዛሂራ ጂና አመልክተዋል።
« በደቡብ አፍሪቃ ተገን ጠያቂዎች ከመምረጥ እና መመረጥ በስተቀር ፣ ልክ እንደ ሃገሪቱ ዜጎች በነፃ የመዘዋወር። የመስራት ፣ የመማር። የመነገድ፣ ወዘተ መብቶች ሁሉ አሉዋቸው።  በነፃው የህክምና አገልግሎት የመጠቀም እና የተወሰነ የማህበራዊ ኑሮ ድጎማ የማግኘት መብት አላቸው። »
ጀርመን ስደተኞችን በማስተናገዱ ረገድ ሰፊ ተሞክሮ ካላት ደቡብ አፍሪቃ ልትማር እንደምትችል የደቡብ በአፍሪቃ የቀድሞው የጀርመን አምባሳደር ቫልተር ሊንድነር አስታውቀዋል።
«  አንድ የስራ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተናል። በሰው አሸጋጋሪዎች አኳያ፣ የድንበር ጥበቃን ማጠናከርን በተመለከተ ምን ሊደረግ ይገባል? ስደተኞቹን እንዴት ከህብረተሰቡ ጋር ማዋኃድ ይቻላል? የቋንቋ ትምህርት ይሰጥ? ወደመጡበት ይመለሱ? ወዘተ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ኮሚቴው በየጊዜው እየተገናኘ መወያያት ይኖርበታል። በማዋኃዱ ላይ ጀርመን ከደቡብ አፍሪቃ ምን ልትማር ትችላለች? ደቡብ አፍሪቃስ ከጀርመን በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ነው ትምህርት ልትወስድ የምትችለው? »
ይሁን እንጂ፣ በደቡብ አፍሪቃ ስደ,ተኞችን በተመለከተ በወረቀት በሰፈረው ሕግ እና በገሀዱ መካከል ብዙ ልዩነት መኖሩን ነው ስደተኞች የሚናገሩት። ቢሮክራሲያዊው አሰራር ትልቅ እንቅፋት ደቅኗል።  የተገን መጠየቂያ ማመልከቻዎች እስኪታዩ ድረስ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ከ400,000 የሚበልጡ ስደተኞች ፣ አንዳንዶቹ ከብዙ ዓመታት ወዲህ መልስ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። ስደተኞቹ መብት አላቸው ቢባልም፣ ለራሳቸው በራሳቸው ላይ ብቻ ጥገኛ መሆናቸውን እና ለህልውናቸውም ብቻቸውን መታገል እንዳለባቸው ሶማልያዊቷን ስደተኛ ፋጢማን የመሳሰሉ ስደተኞች ገልጸዋል። ፋጢማ እንደምትለው ግን፣  ከሁሉም የከፋው ስደተኞች በተለይ ከትልቆቹ ከተሞች ወጣ ብለው በሚገኙት የጥቁሮች መኖሪያ ከተሞች ውስጥ በሚታየው የውጭ ሃገር ዜጎች ጥላቻ ሰበብ የሚካሄደው የኃይል ርምጃ ሰለባ መሆናቸው ነው። እጎአ ከ2008 እስከ 2015 በታየው የኃይል ርምጃ ቢያንስ 50 አፍሪቃውያን ተገድለዋል። ያም ቢሆን ግን፣ ይላሉ የዊትዎተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት እና ህብረተሰብ ማዕከል ባልደረባ ዛሂራ ጂና፣ ደቡብ አፍሪቃ አሁንም የስደተኞች መስህብ እንደሆነች ትገኛለች። 

Gewalt gegen Ausländer in Südafrika geht weiter
ምስል Reuters/S. Sibeko
Karte Ostafrikanische Flüchtlingsroute

ያን ፊሊፕ ሽሉውተር/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ