1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊቢያ የስደተኞች ይዞታ

ዓርብ፣ ጳጉሜን 3 2009

የኤም ኤስ ኤፍ ሃላፊ ሊዩ ሊቢያ በሚሆነው በእጅጉ ተበሳጭተዋል። ለአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ህብረቱ ከሚሊሽያዎች እና ከሰዎች አሻጋሪዎች ጋር ተመሳጥሯል ሲሉ ከሰዋል።

https://p.dw.com/p/2jc75
Libyen Falle für Flüchtlinge
ምስል picture alliance/AP Photo/D. Etter

በሊቢያ የስደተኞች ይዞታ

የአውሮጳ ህብረት ስደተኞች ከሊቢያ ተነስተው በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ የሚሻገሩበትን የጉዞ መስመር በመዘጋት ተወቀሰ። ሊቢያ ለሚገኙ ስደተኞች የህክምና እርዳታ የሚሰጠው ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን በፈረንሳይኛው ምህፃር ኤም ኤስ ኤፍ የአውሮጳ ህብረትን እርምጃ ጭካኔ የተሞላበት ሲል ኮንኗል። በቅርቡ ከሊቢያ የተመለሱት የድርጅቱ ሃላፊ ጆአነ ሉዩትናንት በአውሮጳ ህብረት ጽህፈት ቤት ብራስልስ በሰጡት መግለጫ እርምጃው ስደተኞችን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ነው ብለዋል። 
የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ሃላፊ ጆአነ ሉዊ ከጥቂት ቀናት በፊት ነው ከሊቢያ የተመለሱት። በሊቢያ ቆይታቸውም ስደተኞች የሚታሰሩባቸውን ቦታዎች ጎብኝተዋል። በዚያ የተመለከቱትም ክፉኛ ረብሿቸዋል። ትናንት በአውሮጳ ህብረት ፅህፈት ቤት ብራሰልስ ተገኝተው በሊቢያ ያዩትን የተናገሩት እንባ እየተናነቃቸው ነበር። ጆአነ ሉዊ ፣በሊቢያ መንግሥት ሥር የሚገኙት የስደተኞች ማጎሪያ ስፍራዎች እና በዚያ የሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እስከዛሬ ካይዋቸው እጅግ አስከፊዎቹ  መሆናቸውን  ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በዚያ የሚገኙ ስደተኞች ለሚስ ሊዩ በሹክሹክታ እንደነገሯቸው ስደተኞች እስር ቤት ውስጥ ወደ በር እንዳይጠጉ  በዱላ ይደበደባሉ፤ወንዶች ሴቶች እና ህጻናት በሰዎች በተጣበቡ ጨለማ ክፍሎች ውስጥ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋሉ፤ሴቶች በተለይም ነፍሰ ጡሮች ይደፈራሉ ባሎቻቸውም ይደበደባሉ። ሁሉም ከዚያ እንዲያወጧቸው ጠይቀዋቸዋል። እርሳቸው ግን የሚሉትን ከመስማት ውጭ ምንም ሊያደርጉላቸው አለመቻላቸውን ነው ያስረዱት። የኤም ኤስ ኤፍ ሃላፊዋ በድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሐኪም ቤት ውስጥ የተኛ አንድ ከጋምቢያ የመጣ ወጣት ጎብኝተው ነበር። ሆስፒታል የገባው በነበረበት መጠለያ ተርቦ ለምግብ እጥረት በመዳረጉ ነበር ።
«ታሪኩን ሲነግረን ሊያየኝ አልቻለም። ሲናገርም እንባውን በጉንጮቹ ላይ ይወርዱ ነበር። እናም እዚህ ምን እየሰራን ነው ብዬ ራሴን ደጋግሜ ጠየክኩ። ምግብ ካገኘ እና ደህና ከሆነ በኋላ እንደገና ወደ ሚራብብበት ቦታ መላክ አለበት።»
የድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ባልደረቦች እንደታዘቡት የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከባህር ላይ የሚይዟቸውን ስደተኞች ወደ ማጎሪያ ሰፈሮች ይወስዷቸዋል። ሆኖም ሰዎች ተይዘው እሥር ቤት የሚላኩት ከዚያ ብቻ አይደለም ከትሪፖሊ ጎዳናዎች፣ ከሚኖሩባቸው ቤቶች እና ከመኪናዎችም ነው። እሥር ቤቶቹም ብዙውን ጊዜ የሚጠበቁት በሚሊሽያዎች ነው። ማንም አይመዘገብም። አስተዳደር የለም። ሰዎቹ ላይ ስለሚፈፀመው ማንም አያውቅም። እንደዚህ ዓይነት በይፋ የሚታወቁ 40 የሚሆኑ ማጎሪያዎች ይገኛሉ። በሚሊሽያዎች ስር ያሉት ደግሞ ምን ያህል እንደሆኑ ግልጽ አይደለም ይላሉ የቡድኑ ባልደረባ ጃን ፔተር ስቴልማ። በነዚህ ማጎሪያዎችም ስደተኞች ብዙ በደሎች ይፈፀሙባቸዋል። 
« የሚፈጸመው ዘግናኝ ነው። ስደተኞቹን ያሰቃዩዋቸዋል። በጉልበት ሥራ ለሚያሰማሯቸው የሰዎች አሻጋሪዎች ይሸጡዋቸዋል። እነርሱ በማጎሪያዎቹ ይጠቀማሉ። በእያንዳንዱ ስደተኛ ብዙ ገንዘብ ስለሚያገኙ ነው እሥር ቤቶቹን እንዲኖሩ የሚፈልጉት። »
በሊቢያ ቁጥጥር የሚያደርግ ትክክለኛ መንግሥት የለም። ከዚያ ይልቅ በአውሮጳ ህብረት ሥልጠና የሚሰጣቸው እና የገንዘብ ድጋፍም የሚደረግላቸው የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች በሰዎች ማጎሪያዎች ከሚሊሽያዎች ጋር በትብብር ይሠራሉ። የሮም መንግሥት ደግሞ ስደተኞችን እንዲያስቆሙለት በቀጥታ ለሚሊሽያዎቹ ገንዘብ እንደሚከፍል የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ይዘግባሉ። የኤም ኤስ ኤፍ ሃላፊ ሊዩ ሊቢያ በሚሆነው በእጅጉ ተበሳጭተዋል። ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ህብረቱ ከሚሊሽያዎች እና ከሰዎች አሻጋሪዎች ጋር ተመሳጥሯል ሲሉ ከሰዋል። ለስደተኞች ስቃይ ማብቂያ መፍትሄ ያሉትንም ተናግረዋል ። 
« እያወቁ ሰዎችን ለወንጀለኞች አሳልፎ መስጠት ለነርሱ ስኬት ነው። እናም እስቲ ንገሩኝ እንዴት ነው ይህን እያየን ደህና የምንሆነው? ሰዎች ሊቢያ ውስጥ እንዲቆዩ ከማድረግ ከዚያ ሊወጡ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለብን። ወደ ሊቢያ እንዲመለሱም ማስገደድ የለብንም። »
በሊዩ አስተያየት ስደተኞች አውሮጳ ሊገቢ የሚችሉበት ህጋዊ መንገድ ሊፈለግ ይገባል። በርሳቸው አባባል የሰዎች ማሰቃያ ፋብሪካ የሆነችው ሊቢያ እንደ ትክክለኛ አጋር ልትወሰድም አይገባም ።

Libyen Zentrum für Bekämpfung der illegalen Migration in Tripoli
ምስል Getty Images/AFP/M. Turkia
Dr. Joanne Liu
ምስል DW/B.Riegert

ቤርንት ሪገርት 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ