1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ተቃውሞ በጀርመን

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2005

«የተለያዩ የአውሮፓ አገሮችን ተመልክቼአለሁ። ጉዞዬ አስጨናቂ ነበር። ግን፤ በህይወቴ የጎበኘሁት እጅግ መጥፎ አገር ቢኖር ጀርመን ነው። ጀርመን ውስጥ የምወደው አንድም ነገር የለም።» ጀርመን የሚኖር ተገኝ ጠያቂ የሰጠው አስተያየት።

https://p.dw.com/p/17vjj
Die Bilder sind am 9. März 2013 im Flüchtlingsheim Oberursel bei Frankfurt am Main entstanden. Anlass war die Protest-Tour von Flüchtlingen durch ganz Deutschland. Die Bilder stammen von Stephanie Höppner
ምስል DW

ጀርመን የሚገኙ ስደተኞች ላለፉት 5 ወራት የሃገሪቱን የስደተኞች አያያዝ መርህ ሲቃወሙ ቆይተዋል ። በቅርቡ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾችም ይህንኑ ተቃውሞ በመደገፍ በመላ ሃገሪቱ በመዘዋወር የጀርመን የስደተኞች መርህ ሰለባ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማንቀሳቀስ ዘመቻ ጀምረዋል ። ተገን ጠያቂዎች በተጠለሉበት ከፍራንክፈርት በስተሰሜን ወደ ሚገኘው ወደ ኦበርኡርሴሉ የስደተኞች መጠለያ የሚሄድ ጎብኚ መጀመሪያ የሚያየው ስፍራው የግል ይዞታ መሆኑን የሚጠቁም ፅሁፍ ነው ። ፅሁፉ ጎብኚዎች መጀመሪያ መመዝገብ እንዳለባቸው ያሳስባል ። የዶቼቬለዋ ሽቴፋኒ ሆፕነር እንደዘገበችው በኢንዱስትሪ አካባቢ ከኮንቴይነሮች የተሰሩ ቤቶች በሚገኙበት በዚህ ስፍራ የሚኖሩት እነማን እንደሆኑ የሚጠቁም ነገር ግን የለም ። ባለፈው ቅዳሜ ነበር ስደተኞችንና የስደተኞች መብት ተሟጋቾችን ያሰፈሩ ሁለት አነስተኛ አውቶብሶች ከዚህ ቦታ የደረሱት ። 15 ስደተኞችንና ጥቂት የማይባሉ የመብት ተሟጋቾችን ያቀፈው ይህ ቡድን መሰል ጉዞ ማድረግ የጀመረው ካለፈው ወር አንስቶ ነው ። የአባላቱ አላማም እስከ የካቲት መጨረሻ 22 ከተሞችን ማዳረስ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ የሄዱባት ኦበርኡርሴሉ 11 ኛው ከተማ ነበረች ።

Die Bilder sind am 9. März 2013 im Flüchtlingsheim Oberursel bei Frankfurt am Main entstanden. Anlass war die Protest-Tour von Flüchtlingen durch ganz Deutschland. Die Bilder stammen von Stephanie Höppner
ምስል DW

በቡድኑ አጠራር « ለስደተኞች አብዮት የአውቶብስ ጉዞ » የሚል ስያሜ የተሰጠው የዚህ ንቅናቄ ዋና አላማም በጀርመን የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ የስደተኞች አያያዝ እንዲሻሻል ተቃውሞ ማሰማት ነው ። እግረ መንገዳቸውን ጉዞው መጋቢት አጋማሽ ላይ ሲጠናቀቅ በርሊን ውስጥ ለማካሄድ የታቀደውን ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍም እያስተዋወቁ ነው ። የቡድኑ አባላት ትልቅ የሚባል ድርጅት ድጋፍ ሳይኖራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር የተሰባሰቡት ። የተቃውሞ እንቅስቃሴው የተጀመረው የዛሬ አመት ገደማ ሲሆን መነሻውም የዛሬ አመት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ተገን ጠያቂው ኢራናዊ መሃመድ

ርሃሰፓር ህይወቱን ማጥፋቱ ነበር ። በደቡብ ጀርመኑ በባቫርያ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር በሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበረው ራህስፓር ከመሞቱ አስቀድሞ እህቱ ወደ ምትገኝበት ወደ ሰሜን ጀርመንዋ ኪል ከተማ ለመዛወር ያስገባው ማመልከቻ ውድቅ ተደርጎበት ነበር ። ይህ የራህስፓር አሳዛኝ አሟሟት በመላ ጀርመን የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችን ልብ ነክቶ ተጨማሪ የመብት ጥያቄዎችን ለማቅርብ በአንድ ላይ ሊያሰባስባቸው በቃ ። ከቱርክ የመጣው ቱርጋይ ከተጓዦቹ መካከል አንዱ ነው ። ማርክሲስት በመሆኑ ቱርክ ውስጥ ለ 15 አመታት ታስሮ ነበር ።የቡድኑ አባላት ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ ያስረዳል ።

« ተፈጻሚነት እንዲያገኙ የምናቀርባቸው ሦስት ጥያቄዎች አሉን። የመኖሪያና መንቀሳቀሻ ገደብ የተደረገበት ደንብ እንዲሻር፤ የውጭ ተወላጆች በአንዳንድ አካባቢዎችም ሆነ ጣቢያዎች እንዲከማቹ የሚደረግበት አሠራር እንዲወገድ፤ እንዲሁም፤ የውጭ ተወላጆችን አስገድዶ ካገር ማስወጣቱ እንዲቀር የመኖሪያና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀሻ ገደብ የሚሠራበት በጀርመን ሀገር ብቻ ነው ። »

Die Bilder sind am 9. März 2013 im Flüchtlingsheim Oberursel bei Frankfurt am Main entstanden. Anlass war die Protest-Tour von Flüchtlingen durch ganz Deutschland. Die Bilder stammen von Stephanie Höppner
ምስል DW

ለተገን ጠያቂዎች የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጠው በገደብ ነው ፤ ከተጠለሉበት የአስተዳደር ክልል መልቀቅ አይፈቀድላቸውም ። ሆኖም አሁን ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍላተ ሃገር በ11 ዱ ህጉ ላልቷል ። አሁን ተገን ጠያቂዎች ቢያንስ ክፍላተ ሃገሮቹን በሚያዋስኑት ግዛቶች ውስጥ መንቀሳቀስ ይችላሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የመዘዋወር ነፃነት እንደ ተገን ጠያቂው ሁኔታ ገደብ ሊጣልበት ይችላል ። ቱርካዊው ቱርጋይ በአጠቃላይ የመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙት በተገለሉ አካባቢዎች በመሆናቸው አይስማማም ። እነዚህን ስፍራዎች ከእስር ቤቶች ጋር ነው የሚያነፃፅራቸው ።

« ሁሉም ተነጣጥለው እንዲኖሩ ተደርጓል። ይመልከቱ! ሰዎች እዚህ እንዴት እንደሚኖሩ--እዚህ የት አለ የማኅበራዊ ኑሮ መንፈስ? ይህ እሥር ቤትነው።»

ተቃውሞአቸውን እየተዘዋወሩ ከሚያሰሙት የቡድኑ አባላት አንዱ ከሱዳን የመጣው የ 28 አመቱ ማሃዲ ነው ። ጀርመን ከመጣ አንድ አመት ሊሞላው ነው ። አውሮፓ የመጣው አባቱ ከአማፅያን ጋር በመተባበራቸው ምክንያት ለህይወቱ ስለሰጋ ነው ። መሃዲ በሃገሩ ባለሥልጣናት ጥርጣሬ ለወራት ታስሮ ነበር ። ምንም እንኳን ከዚያ አስጊ ሁኔታ አምልጦ ጀርመን መምጣት ቢችልም ጀርመን በገጠመው ነገር ግን ደስተኛ አይደለም ።

«እንዳልሁት፣የተለያዩ የአውሮፓ አገሮችን ተመልክቼአለሁ። ጉዞዬ አስጨናቂ ነበር። ግን፤ በህይወቴ የጎበኘሁት እጅግ መጥፎ አገር ቢኖር ጀርመን ነው። ጀርመን ውስጥ የምወደው አንድም ነገር የለም።»

Die Bilder sind am 9. März 2013 im Flüchtlingsheim Oberursel bei Frankfurt am Main entstanden. Anlass war die Protest-Tour von Flüchtlingen durch ganz Deutschland. Die Bilder stammen von Stephanie Höppner
ምስል DW

ከመጠለያው ነዋሪዎች አንዱ የ18 አመቱ አፍጋናዊ ፔካን ነው ። ተገን ለማግኘት ያስገባው ማመልከቻ ተቀባይነት ቢያገኝም ከመጠለያው ግን መውጣት አልተፈቀደለትም ። ከመጠለያው ወጥቶ መኖር የሚችለው ራሱን ማስተዳደር የሚያስችለው በቂ ገቢ ካገኘ ብቻ ነው ። ላለፉት 2 አመታት ጀርመን የኖረው ፔካን አሁን በአንድ የ2 ተኛ ደረጃ የቴክኒክ ትምህርት ቤት እየተማረ ነው ። ፔካን እንደሚለው ተማሪ ሆኖ መጠለያ ካምፕ ውስጥ መኖር ከባድ ነው ። ከምሽቱ 5 ሰአት ፔካን ማረፍ ቢፈልግም ብዙውን ጊዜ በተለይ ጠጪዎች ካሉ እንደሚረበሽ ነው የሚናገረው ። ምርጫ ያጣው የተማሪው ፔካ ህይወት በመጠለያ ጣቢያ ይህን ይመስላል ። ይህን መሰሉን የስደተኞች አያያዝ ሱዳናዊው መሃዲ በእጅጉ ይቃወማል ።

«ማለቴ፣-- የጀርመንን የስደተኞች አያያዝ ሥርዓት ከቶ አልቀበለውም። ሰዎችን በአንድ አካባቢ ወይም ጣቢያ አሳባስበው ለዓመታት የሚያቆዩበት አሠራር የሚያንገሸግሽ ነው። ሰዎችን ከንቱ የሚያደርግ ነው ። በአንድ አካባቢም ሆነ ጣቢያ ሰዎችን ሰብስቦ ፣ በዩንቨርስቲም ሆነ ኮሌጅ እንዳይማሩና እንዳይሠሩ ነው የሚያደርጓቸው።»

ሌላው የንቅናቄው አባል ሃይዳር ኡካር ቡድኑን የተቀላቀለው በዓላማው መስማማቱን ለማሳየት መሆኑን ይናገራል ። በትውልድ ቱርካዊ በዜግነት ጀርመናዊው የ51 አመቱ ኡካር ተገን ጠያቂ ነበር ። ጥቂት ገንዘብ ያለው የቡድኑ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ መታቀድ አለበት ይላል ። የቡድኑ የምግብና የትራንስፖርት ወጪው የሚሸፈነው በእርዳታ ነው ። በየከተማው የሚያድሩት በጓደኞቻቸው ና በሚያውቋቸው ሰዎች ቤት ነው ። የቡድኑ አባላት በሚዘዋወሩባቸው ከተሞች ተገን ጠያቂዎች በተጠሉላባቸው ካምፖች እየተገኙ ስደተኞቹን ያነጋገራሉ ። ስለጀመሩት የተቃውሞ ንቅናቄ ያውቁ እንደሆን ከሚጠይቋቸው ተገን ጠያቂዎች አብዛኛዎቹ ምን እንዳልሰሙ ነው የሚነግሯቸው ።

Die Bilder sind am 9. März 2013 im Flüchtlingsheim Oberursel bei Frankfurt am Main entstanden. Anlass war die Protest-Tour von Flüchtlingen durch ganz Deutschland. Die Bilder stammen von Stephanie Höppner
ምስል DW

በርግጥም አብዛኛዎቹ የኢንተርኔት አገልግሎት አያገኙም ። ቅዳሜ በኦበርኡርሴሉ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ከተገኙት አንዳንድ የንቅናቄው አባላት የተወሰኑት ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹ በመጋቢት መጨረሻ በሚደረገው ሰልፍ ላይ ሊገኙ መቻላቸውን ይጠራጠራሉ ። አንዳንዶቹ ስለ አያያዙ ሲጠየቁ አይከፋም ይላሉ ሌሎች ደግሞ ለመናገር ይፈራሉ ። ይህ አንዱ ችግር መሆኑን አንዳንድ አባላት ጠቁመዋል ። በሄሰን ፌደራዊ ክፈለ ሃገር ውስጥ

ያለው ይህ የተገን ጠያቂዎች መጠለያ ስሙ በመጥፎ የሚነሳ ነው ። የመኖሪያ ክፍሎቹ ጠባብና ፅዳት የሚጎድላቸው መሆናቸውን ፖለቲከኞች ሳይቀር ተናግረዋል ። ፖለቲከኞችና በጎ ፈቃደኞች በዚህ መጠለያ የሚኖሩ ቁጥራቸው 200 የሚጠጋ ሴቶች ወንዶችና ህፃናት የተሻለ መኖሪያ እንዲያገኙ ሲጥሩ ነበር ። በጀርመን የስደተኞች መብት እንዲጠበቅ ንቅናቄ የጀመረው ቡድን አባላት ለ 4 ሰዓታት ያህል በመጠለያው ጣቢያ ከቆዩ በኋላ ወደ ምዕራብ ጀርመንዋ ከተማ ኮሎኝ አቀኑ ። ተመሳሳዩ ጉዞ ሲያበቃ ታላቁ የበርሊኑ ሠላማዊ ሰልፍ ይካሄዳል ። ይሁንና ፔካን ትምሕርት ስላለው በዚያን ቀን ሰልፉ ላይ ሊገኝ አይችልም ። ሌሎች ተገን ጠያቂዎችም በተለያዩ ምክንያቶች በመጋቢቱ ሰልፍ ላይ መገኘታቸው ያጠራጥራል ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ